Monday, 16 March 2015 10:17

በስደት አገር በለስ የቀናቸው ኢንቬስተር

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

ማንም ቢሆን ስደትን ወዶ አይመርጥም፤ ተገድዶ እንጂ፡፡ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በስደት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከፊሎቹ የፖለቲካ ስደተኞች፣ ከፊሎቹ ደግሞ የኢኮኖሚ ስደተኞች ናቸው፡፡ አንዳንዶች የስደት ህይወት ሳያመቻቸው ቀርቶ ከአገራቸውም ከኑሯቸውም ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ያለሙት ተሳክቶ ከራሳቸውም አልፈው ለአገር ለወገናቸው ይተርፋሉ፡፡
የዛሬው እንግዳችን ከሁለተኛው ምድብ የሚሰለፉ ናቸው፡፡ 32 ዓመት በስደት በኖሩበት አገር ሰርተውና ሁበት አፍርተው ወደ አገራቸው በመመለስ የወርቅ ማዕድን ኩባንያ፣ ትላልቅ የሕክምና መሳሪያዎች አስመጪ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት መርጃ በጎ አድራጎት ተቋም ከማቋቋማቸውም በላይ፣ በአክሲዮን በተመሰረቱ ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ በመግዛት ባለቤት ለመሆን ችለዋል፡፡
በአድዋ ከተማ ተወልደው የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያ ተከታትለው፣ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በወቅቱ የልዑል በዕደማርያም ት/ቤት አካል በነበረው “ኮሌጅ ኦፍ ቲቸርስ ኢጁኬሽን” ክፍል ተምረው በዲግሪ ተመርቀዋል - አቶ ዳዊት ገ/እግዚአብሔር፡፡
አቶ ዳዊት ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በመምህርነትና በሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) ዝግጅት ማገልገላቸውን ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ፣ ሥልጣን ላይ የነበረው የደርግ መንግስት በሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲ የተነሳ እንደፈለጉት ሰርተው ለመኖርና ኑሮአቸውን ለመለወጥ የነበራቸው ዕቅድ ሊሳካ አለመቻሉን ያስታውሳሉ። ምኞቴ ሊሳካ የሚችለው ከአገር ስወጣ ብቻ ነው የሚል ውሳኔ ላይም ይደርሳሉ፡፡ ምኞታቸውን ለማሳካት አላወላወሉም፡፡ በአስመራ በኩል አድርገው ሲገኝ በመኪና ሲጠፋ በእግር እየተጓዙ፣ ብዙም ችግር ሳያጋጥማቸው ድንበር ተሻግረው ሱዳን መግባታቸውን፣ እዚያም ብዙ ሳይቆዩ የተባበሩት አረብ ኢመሬትስ (ዱባይ) መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡
ምንም እንኳን የደርግ ሥርዓትን ለመጣል መሳሪያ አንግተው ጫካ ባይገቡም  የትግሉ አካል ነበርኩ ይላሉ፤ አቶ ዳዊት፡፡ “ትግል በብዙ መልኩ ይካሄድ ነበር፡፡ እኔ ጠብመንጃ ተሸክሜ በረሃ አልወረድኩም። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የነበረውን ስርዓት ለመጣል በተለያየ መንገድ ታግለዋል፡፡ እኔም በዚያ የትግል አካል ነበርኩ” ብለዋል፡፡
አንድ ሰው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከነበረው ኃላፊነት ተሽሮ ዝቅ ወዳለ ደረጃ ሲወረወርና በሄደበት ቦታ ሲቀናው፣ “የልምጭም ገድ አለው” ይባላል፡፡ አቶ ዳዊትም ያጋጠማቸው ነገር ተመሳሳይ ነበር፡፡ ዱባይ አልከፋችባቸውም፡፡ “ከዜጎቼ እኩል ሰርተህ መኖር ትችላለህ” በማለት እጆቿን ዘርግታ ተቀበለቻቸው። ዱባይ ገብተው ትንሽ እንደቆዩ በአንድ ነዳጅ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀመሩ፡፡ የሚገርመው ነገር በዚያ ስራ ላይ ለብዙ ዓመታት አልቆዩም፡፡
“ሜንቴናንስ ኮንስትራክሽን” የተባለ የራሳቸውን ትልቅ ኩባንያ አቋቁመው መስራት ቀጠሉ፡፡ ከዚያም ኢህአዴግ፣ ደርግን ጥሎ ሥልጣን ሲይዝ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁን መኖሪያዬ እዚህም ዱባይም ነው የሚሉት አቶ ዳዊት፤ “እዚህ ያለው ቢዝነሴ ትንሽ ነው፤ እዚያ ያለው ይበልጣል፤ ብዙ ጊዜ የቆየና የለመደም ስለሆነ እንቅስቃሴው በጣም ጥሩ ነው” ይላሉ።
አቶ ዳዊት በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የወርቅ ማዕድን አሰሳና ቁፋሮ ለማካሄድ የተቋቋመ “ዳዊት ጎልድ ማይንኒግ” የተሰኘ ኩባንያ አላቸው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ባደረጉት የማዕድን አሰሳና ፍለጋ (ሰርቨይና ኤክስፕሎሬሽን) በተወሰኑ ቦታዎች ጥሩ ውጤት እንዳገኙባቸው ገልጸዋል፡፡ 15 የውጭና የአገር ውስጥ ሙያተኞች፣ የተለያዩ ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም ወርቅ ያለበትን ስፍራ ለይተዋል፡፡ ምን ዓይነት ውጤት ይኖረዋል? በማለት ናሙናዎች በአገር ውስጥ ተመርምረውና ወደ ውጭ ተልከው ጥሩ ውጤት እንዳላቸው ስለተረጋገጠ፣ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ቁፋሮ ለመጀመር ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የወርቅ ማዕድን ምርት በካፒታልም ሆነ በባለሙያ ትልቅ አቅም የሚጠይቅ እንደሆነ የጠቀሱት ባለሀብቱ፤ አብረዋቸው የሚሰሩ ትላልቅ ኩባንያዎች እያፈላለጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላው አቶ ዳዊት ያቋቋሙት ድርጅት “ሜዲካል ፋርማ” የተባለው ድርጅት ሲሆን ከ8 ዓመት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ መንግሥት ከፍተኛ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት መኖሩን ተገንዝቦ ለመከላከል ባቀደበት ወቅት፣ ከፍተኛ የመመርመር አቅም ያላቸውን ዘመናዊ መሳሪያዎች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ በደንብ አልገቡበትም እንጂ ሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) እና ወባን መከላከልም በእቅዳቸው ውስጥ አለ፡፡
የኤችአይቪ መመርመሪያ መሳሪያዎቹ በጥራትም ሆነ በዋጋ ተመጣጣኝነት በዓለም ጤና ድርጅትና በጤና ጥበቃ ሚ/ር የተረጋገጡ ናቸው ያሉት ባለሀብቱ፤ መሳሪያዎቹን የሚያቀርቡት ለመንግስት፣ በሽታውን በግል በማከም ላይ ላሉ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች፣ በግል መመርመርና መታከም ለሚፈልጉ ግለሰቦችና መንግስታዊ ላልሆኑ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ1.1 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ የገዙት ኢንቨስተሩ፤ በራያ ቢራ ፋብሪካ የ150 ሚሊዮን ብር አክሲዮን በመግዛት ከግለሰቦች ከፍተኛው ባለድርሻ ናቸው፡፡ በናሽናል ኤርዌይስም ከፍተኛው ባለአክሲዮን እሳቸው እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
“ዳዊት ግብረ ሰናይ” በተባለው ድርጅታቸው ወላጅ የሌላቸው ልጆች የሚረዱት ባለሀብቱ፤ ከሜሪ ጆይ ጋር በመተባበር ከ50 በላይ ወላጅ አጥ ልጆችን እንደሚንከባከቡ ገልጸዋል፡፡ የገቢ አቅማቸው ደካማ የሆነ ቤተሰብ ልጆችንም ይደግፋሉ፡፡
በአድዋ፣ በአክሱምና በመቀሌ ወጣቶች በነፃ ባህልና ታሪካቸውን የሚከታተሉበት የቋንቋና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ማዕከል አቋቁመዋል፡፡ በአክሱምና በመቀሌ ግን እንደተፈለገው እየተንቀሳቀሱ አይደለም፤ በእንጥልጥል ላይ ናቸው ብለዋል አቶ ዳዊት፡፡
ባህላችንን (የአክሱም ሃውልቶች፣ አል-ነጃሺ መስጊድ…) ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ከአካባቢው ህዝብ ጋር የተነጋገርንባቸውና በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች አሉ ያሉት ባለሃብቱ፤ ከግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር ት/ቤትና ጤና ጣቢያ በማቋቋም መሳተፋቸውንና አሁንም እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “ሀብትና ገንዘብ የህሊና ደስታ የሚሰጠው ቁምነገር ላይ ሲውል ነው፡፡ እግዚአብሔር ዕድሜና ጤናውን ይስጠኝ እንጂ ገና ለመስራት ያቀድኳቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የምሰራው ለግሌ አይደለም፡፡ እኔ እንደማንኛውም ሰው በቀን የምበላው ሁለት እንጀራ ነው፡፡ ስለዚህ ለህዝብ አገልግሎትና ጥቅም በሚሰጡ ኩባንያዎች ውስጥ እሳተፋለሁ፡፡ በራያ ቢራ ፋብሪካ፣ በናሽናል ኤርዌይስ፣… ምስረታ ተሳትፌያለሁ፡፡ እንዲህ አደረግሁ ማለት ስለማልወድ ነው እንጂ ሌሎችም ይኖራሉ፡፡ ሀብት የሚገኘው አገር ሰላም ሆና፣ እግዜር ጤናና ዕድሜ ሰጥቶ መስራት ሲቻል ነው፡፡ ስለዚህ የእኔ ምኞት እነዚህን የእግዚአብሔር በረከቶች እስካገኘሁ ድረስ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ነገር መስራቴን መቀጠል ነው” ብለዋል አቶ ዳዊት ገ/እግዚአብሔር፡፡  

Read 2521 times