Monday, 16 March 2015 09:37

የአከርካሪ መዛባት ችግር (ሶኮላዮሲስ)

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)

የአከርካሪ አጥንት መዛባት ለአዕምሮ፣ ለሣንባና ለልብ ህመም ሊያጋልጥ ይችላል
ህፃናትም በችግሩ ተጠቂ እየሆኑ ነው

የአከርካሪ አጥንት ከትክክለኛ ሥፍራው አፈንግጦ ወይንም ወደ ጐን ታጥፎ ከመደበኛው የአጥንት አሰላለፍ ከ10 ድግሪ በላይ ተዛብቶ ከቆየ የከፋ የጤና ችግርና የአካል ጉዳት ያስከትላል፡፡ ችግሩ ተባብሶ ከቀጠለ መደበኛ የሰውነት ተግባራትን ከማወክም በላይ በአዕምሮ ነርቮች እንዲሁም በልብና በሳንባ ላይ ጉዳት ማስከተል ይጀምራል፡፡
በሣንይንሳዊ አጠራሩ ስኮላዮሲስ (Scoliosis) የሚባለው ይኸው የአጥንት መዛባት ችግር በጨቅላ ህፃናቶችና በታዳጊዎች ላይ የሚከሰትና ህመም ሣይኖረው ቆይቶ በመካከለኛው ዕድሜ ላይ ለከፋ የጤና ችግርና ለአካል ጉዳት የሚዳርግ ነው፡፡ ችግሩ በአብዛኛው ከ10-14 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎችን የሚያጠቃ ሲሆን ሴት ህፃናት ከወንዶች የበለጠ የችግሩ ተጠቂ ናቸው፡፡
የአለም ጤና ድርጅት የ2012 ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ የአከርካሪ መዛባት ችግር በመላው ዓለም በስፋት የሚታይና በርካቶችን ለከፍተኛ የጤና ችግርና ለአካል ጉዳት የዳረገ ሲሆን ችግሩ ይኼ ነው የሚባል ምልክት የሌለው በመሆኑ አብዛኛዎቹ ተጠቂዎች ችግሩ እንዳለባቸው የሚያውቁት ተባብሶ የአካል ጉዳትና ሌሎች የጤና ችግሮችን ሲያስከትልባቸው ነው፡፡ መረጃው እንደሚያመለክተው፤ 85 በመቶ የሚሆነው የአከርካሪ መዛባት ችግር መነሻ ምን እንደሆነ በውል የማይታወቅ ሲሆን የሆርሞን እና ነርቭ ስርአቶች መዛባት፣ ስርዓት የለሽ አቀማመጥ፣ የተደጋገመና ከአቅም በላይ የሆነ ክብደትን አዘውትሮ መያዝ፣ የአጥንትና ጡንቻ ስርዓት ችግሮችና የቅርብ ቤተሰብ የችግሩ ተጠቂ መሆን እንደ ዋና መነሻነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡  
ዕድሜያቸው ከ10-14 ዓመት የሚሆን ታዳጊ ወጣቶች አዶለሰንት ስኮሊዮሲስ በተባለው የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግር በስፋት የሚጠቁ ሲሆን ከውልደት አንስቶ እስከ 3 ዓመት ድረስ ባለ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚከሰተው (ኢንፋንታይል ስኮሊዮሲስ)፣ እንዲሁም ከ3 ዓመት እስከ 10 ዓመት በሚሆን የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚከሰተው (ጁቬናይል ስኮሊዮሲስ) ህፃናትን በማጥቃት ከሚታወቁት የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በህፃንነትና በታዳጊነት ዕድሜ ዘመናቸው ለገጠማቸው የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግሮች በወቅቱ መፍትሔ ያላገኙ ሰዎች በአዋቂነት የዕድሜ ዘመናቸው አብሮአቸው ለሚዘልቅ ቋሚ የጀርባ ህመም መዳረጋቸው እሙን ነው፡፡
የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግር የሚጀምረው መዛነፉ ከ10 ድግሪ በላይ ሲሆን ነው፡፡ የአጥንት መዛነፉ ጉዳይ እየጨመረ ሲሄድ የችግሩ ስፋትም የሚጨምር ከመሆኑም ሌላ በህክምና ከችግሩ የመላቀቅ ዕድልም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ የአጥንት መዛነፉ እየጨመረ ስለሚቀጥል በችግሩ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና ችግሮችም እየባሱ ይሄዳሉ፡፡
የአከርካሪ አጥንት አቀማመጥ መዛባቱ ከ70 ድግሪ በላይ ከሆነ ችግሩ የጐድን አጥንቶች ሣንባን እንዲጫኑት ስለሚያደርጋቸው የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል፡፡ ይህ ሁኔታ ተባብሶ ከቀጠለ ለአዕምሮ ነርቮች ጉዳት ስለሚዳርግ የአዕምሮ ጤና ችግርን ያመጣል፡፡ መዛባቱ ከ100 ድግሪ በላይ ከሆነ ደግሞ በልብ ላይ የከፋ የጤና ችግር በማስከተል ታማሚውን እስከሞት ሊያደርሰው ይችላል፡፡ ኦሶቲዮፔኒያ የሚባለው የአጥንት ጥንካሬ ማጣት ችግርም የሚከሰተው ህክምና ያላገኘ የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡
የችግሩ ምልክቶችና መፍትሔዎች
የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግር በኤክስሬይ የህክምና ምርመራ ዘዴ ሊታወቅ የሚችል ሲሆን የመዛባቱ መጠን ሰውየውን ጉዳት ላይ የሚጥል መሆን አለመሆኑን ባለሙያው ካመነበትና የመዛባቱ መጠን ከ20-40 ድግሪ የሚደርስ ከሆነ የታካሚው የአከርካሪ አጥንት ወደ ቦታው እንዲመለስ የሚረዳ ብረት በታካሚው ጀርባ ላይ ይታሰራል፡፡ ይህም በሂደት የተዛባው የአጥንት ክፍል ወደ ቦታው እንዲመለስ ይረዳል፡፡ የመዛባቱ መጠን ከ50 ድግሪ በላይ ከሆነ ግን ችግሩን ማስተካከል የሚቻለው በቀዶ ህክምና ብቻ ነው፡፡   

Read 5771 times