Monday, 16 March 2015 09:40

የውሃ ህክምና ፈውስ

Written by 
Rate this item
(19 votes)

የውሃ ህክምና (ሃይድሮቴራፒ) ጥንታውያን ግሪኮች፣ ግብፆችና ሮማውያን ከበሽታ ለመፈወስ  ሲጠቀሙበት የኖሩት ህክምና ሲሆን በቀላሉ ሊገኝ የሚችልም ነው፡፡ ውሃ በፈሳሽ፣ በበበረዶና በጋዝ መልኩ የተለያዩ ጠቀሜታዎችን ይሰጣል፡፡ ቀዝቃዛ፣ ሙቅና ፍል ውሃም አገልግሎቱ ለየቅል ነው፡፡
ውሃን በመጠጣት የሚገኝ ፈውስ
 ንፁህ ውሃን በመጠጣት ለህመም ፈውስ ማግኘት ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ሲተገበር የቆየ ህክምና ነው። ውሃን መጠጣት የሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅምን                                                                                ያዳብራል፡፡ ውሃን በመጠጣት የኩላሊት፣ የጨጓራ፣ የፊኛ፣ የመገጣጠሚያ አካላት፣ አንጀትና ጣፊያ በሽታዎችን፣ ኪንታሮት፣ የሳንባ ምች፣ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችን፣ የጡንቻና አጥንት ጤና ችግሮችን ማስወገድ ይቻላል፡፡
ሁልጊዜ ጠዋት ቁርስ ከመመገባችን በፊት ከአምስት ብርጭቆ ያላነሰ ውሃ ብንጠጣ ለተለያዩ ውስጣዊ የጤና ችግሮቻችን መፍትሄ እናገኛለን፡፡ ውሃ በተፈጥሮው የአሲድነት ፀባይ የሌለው በመሆኑ ለሰውነታችን ውስጣዊ ኡደት መቀላጠፍ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በአግባቡ ሳይሰለቀጡ ወደ አንጀታችን የሚገቡ ምግቦች በቀላሉ እንዲብላሉና በጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ውሃ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡
ውሃን በመነከር የሚገኝ ፈውስ
በጣም የቀዘቀዘ ውሃ ማይግሪን ለተባለው ራስ ምታት ፍቱን መድኀኒት ነው፡፡ ህመሙ በሚነሳበት ወቅት በጣም የቀዘቀዘ ውሃን ለአምስት ደቂቃዎች ያህል አናት ላይ በመያዝ ህመሙን ማስታገስ ይቻላል፡፡
ቀዝቃዛ ውሃ ለአለርጂ፣ ለጡንቻ መዛል፣ ለአዕምሮ መረበሽ (ለድብርት)፣ ለውጥረት፣ ለትኩሳትና ለሌሎችም በሽታዎች ፍቱን መድኀኒት ነው፡፡ ውሃ በሞቃትና በፍል መልኩ ጥቅም ላይ ሲውል ደግሞ ለመገጣጠሚያ ችግሮች፣ ለጉንፋን፣ ለብርድ፣ ለኢንፍሉዌንዛ ፍቱን መድኀኒት ነው። የሙቀት መጠኑ 750c የሆነ ውሃ ህመም በሚሰማን ቦታ ላይ ማፍሰስ (መነከር) ከህመም እፎይታን ሊያስገኝ ይችላል፡፡
ውሃን በበረዶ መልክ መጠቀም  
በመገጣጠሚያ አካላት ላይ በአደጋ (መውደቅ፣ መጋጨት) ለሚደርስ ጉዳትና በዚህ ሳቢያ በሰውነታችን ላይ ለሚከሰት እብጠት፣ የጡንቻ መሸማቀቅ ወይም ውልቃት በረዶ ፈጣን ፈውስን ያስገኛል፡፡ በረዶ በተጎዳው ሰውነታችን ላይ ሲደረግ ከህመም እፎይታን ከማግኘታችንም በሻገር እብጠቱን ለመቀነስ ያስችላል፡፡
ውሃን በመታጠን መፈወስ
ውሃን አፍልቶ መታጠን (በጋዝ መልኩ) ለጉንፋን፣ ለሳል፣ ለኢንፍሉዌንዛና ለጉሮሮ ህመሞች ፈጣን ፈውስ ይሰጣል፡፡  
የውሃ ህክምና ጥንቃቄዎች
በውሃ ህክምና በመታገዝ ፈውስ ለማግኘት በምንሞክር ወቅት ያሉብንን የጤና ችግሮች በሚያባብስ መልኩ እንዳይሆንብን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ቁስለት ባለባቸው የሰውነት አካላት ላይ ሙቅም ሆነ ቀዝቃዛ ውሃ መጠቀም የለብንም፡፡
እርጉዝ ሴቶች በውሃ ህክምና ከመጠቀማቸው በፊት ከሃኪማቸው ጋር መማከር ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ ህክምናውን በብልት (በማህፀን አካባቢ) ላሉ ችግሮች መጠቀም የሚፈልጉ እርጉዝ ሴቶች ህክምናውን ከመጀመራቸው በፊት ሃኪማቸውን ማማከር ይገባቸዋል፡፡

Read 16139 times