Monday, 16 March 2015 09:42

ካፌይን እና መዘዞቹ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ካፌይን አዕምሮን ለማነቃቃት የሚረዳና በተለይ በቡና፣ በሻይና በተለያዩ የለስላሣ መጠጦች ውስጥ በስፋት የሚገኝ ኬሚካል ነው፡፡ ካፌይን ከእነዚህ መጠጦች በተጨማሪ በቸኮሌቶች፣ በብስኩቶችና በተለያዩ የህመም ማስታገሻና የራስ ምታት መድሃኒቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ኬሚካል ሱስ የማስያዝ ባህርይው ከፍተኛ ነው፡፡ የተጠቀሱት መጠጦችና ምግቦች እንዲሁም መድሃኒቶች ካፌይን የመያዝ አቅማቸው እንደየሁኔታው የተለያየ ሲሆን በቡና ውስጥ የሚገኘው የካፌይን መጠን ከፍ ያለ ነው፡፡ አንድ ስኒ ቡና ከ100-150 ሚሊ ግራም ካፌይን በውስጡ ይይዛል፡፡ አንድ ሰው በቀን በአማካይ 80 ሚሊ ግራም ካፌይን ይወስዳል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከመጠን ያለፈ ካፌይንን መጠቀም ለከፋ የጤና ችግር ይዳርጋል፡፡ በካፌይን ሳቢያ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል የካፌይን ስካር (ኢንቶክሲኬሽን)፣ ሱሰኝነት፣ የእንቅልፍ ማጣትና ጭንቀት ይጠቀሳሉ፡፡  
የካፌይን ስካር (ኢንቶክሲኬሽን)
ከ250 ሚሊ ግራም በላይ የሆነ ካፌይን ከተወሰደ የካፌይን ስካር ይጀምራል፡፡ የዚህ ችግር ምልክቶች ጭንቀት፣ መቅበጥበጥ፣ የህሊና መረበሽ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማላብ፣ የሽንት መብዛት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ እጅና እግርን የመውረር ስሜት መኖርና መነጫነጭ ናቸው፡፡ የካፌይን መጠኑ እየጨመረ ከሄደ እና 1000 ሚሊ ግራም ከደረሰ የአፍ መኮላተፍ፣ የሃሳብ መደነጋገርና የልብ ትርታ መዛባት ሊከተል ይችላል፡፡ መጠኑ ከዚህ እየጨመረ ከሄደም ድንገተኛ የልብ ምት መቆም (ሞትን) ሊያስከትል ይችላል፡፡
የካፌይን ሱሰኝነት
ራስ ምታት፣ ድብርት፣ ጭንቀት፣ ድካም፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ የማለት ስሜት--- በካፌይን ሱሰኝነት ምክንያት የሚከሰቱ የጤና ችግሮች ናቸው፡፡
ይህ ችግር ካፌይኑ ከቀረ ከ10-12 ሰዓታት ውስጥ የሚጀምር ሲሆን ከጥቂት ቀናት ተደጋጋሚ ስሜት በኋላ ሊጠፋ የሚችል ነው፡፡
የእንቅልፍ ማጣትና ጭንቀት
መረበሽ፣ መነጫነጭ፣ በአንድ ቦታ ተረጋግቶ አለመቀመጥ፣ መርበትበትና መጨነቅ በካፌይን ሰበብ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ካፌይን ለእንቅልፍ ማጣት ሰበብ ከመሆኑም በተጨማሪ  ለድብርት፣ ለጭንቀትና ለውጥረት ዋንኛ ምክንያትም ነው፡፡
የመፍትሔ እርምጃዎች
የሚወሰደውን የካፌይን መጠን በአንድ ጊዜ ለመቀነስ መሞከር አይመከርም፡፡ ይልቁንም ዕለት በዕለት ቀስ እያሉ የሚወስዱትን የካፌይን መጠን በመቀነስ በሂደትም ማቆም በካፌይን ሰበብ ከሚደርሱ የጤና ችግሮች ሊታደገን ይችላል። ካፌይን የሌለባቸውን ምግቦችና መጠጦች ለይቶ በማወቅ እነሱ ላይ ትኩረት በማድረግ መጠቀም፣ ራስን በሌሎች ነገሮች ለማዝናናት መሞከርና ውሃን አብዝቶ መጠጣት በካፌይን ሳቢያ የሚከሰቱትን የጤና ችግሮች ለማስወገድ ይረዳል፡፡

Read 6325 times