Monday, 16 March 2015 09:32

‘የዲዮጋን ፋኖስ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…የዘንድሮ የወሬ ነገር በጣም አስቸጋሪ አልሆነባችሁም! አለ አይደል…ከአንደበት የወጣውም፣ ከአንደበት ያልወጣውም አንድ ሺህ አንድ ቦታ ‘እየተከተፈ’… “ሁለተኛ አንዲት ነገር እንኳን ትንፍሽ ብል!...” የምንልበት ዘመን እየደረስን ነው፡፡
ስሙኝማ…አንዳንድ ጊዜ ያ ዲዮጋን የሚሉት ፈላስፋ… አለ አይደል… በገበያ መሀል ፋኖስ ይዞ “ሰው እየፈለግሁ ነው…” ያለው ነገር… “ይሄ ሰውዬ ዘንድሮ እኛ መሀል ቢኖር ምን ይለን ነበር!” አያሰኛችሁም?
የእኛው ታላቅ ሰውም…
ዓይኔን ሰው አማረው፣ ዓይኔን ሰው አማረው
የሰው ያለህ የሰው
ብለውን የለ! ሰው በበዛበት “የሰው ያለህ የሰው…” ከማለት ያድነንማ፡፡
ለምሳሌ… አለ አይደል… ሆዳችሁን እንደመቁረጥ ነገር ያደርጋችኋል፡፡ (የምር ግን… ዘንድሮ ወይ ሆዱን ቆረጥ፣ ወይ ራሱን ፈለጥ፣ ወይ ጎኑን ወጋ የማያደርገው ሰው ማግኘት አስቸጋሪ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የከተማችንን ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች ማየት ነው!)
እናላችሁ… ሰዎች “ትንሽ እንቀማመስ እንዴ!” ሲሏችሁ…
“ሆዴን ትንሽ አመም አድርጎኛል…” ትላላችሁ፡፡ ከዛላችሁ አንዱ…
“ምንህን ነው ያመመህ?” ይላችኋል፡፡
“ሆዴን ነው ትንሽ ቆረጥ ያደረገኝ…” ትላላችሁ። እሱዬው…
“ጨጓራ ምናምን አለብህ እንዴ!” ይላል፡፡
“አይ ጨጓራ እንኳን የለብኝም፣” ትላላችሁ፡፡
“ትንሽ አንጀትህ ቆስሎ ይሆናል…” ይላችኋል፡፡ በሆዳችሁ… ‘ሰውየው ምን ነካው…’ ብላችሁ ሳታበቁ… “እንደውም እኮ ሳይህ እዚህ ጉንጭህ አካባቢ ወየብ ሲልብኝ ይሄ ሰው አንጀቱን ሳያመው አልቀረም ብዬ ነበር፣” ይላችኋል፡፡
እንዴት ነው ነገሩ…እኔ የምለው… የአንድ ሰው የጤንነት ሁኔታ እኮ በጣም ግላዊ ነገር ነው፡፡ ምንህን ነው ያመመህ የሚል ነገር ለመደብንና እንለዋለን እንጂ… የሆነ ልክ ያልሆነ ነገር አለው፡፡
ይቺን የሆነ ቦታ ያነበብኳትን ስሙኝማ…ሰውየው ለጓደኞቹ ሲያወራ ነው… “ወንድሜ ታመመና ዶክተር ስሚዝን ጠራነው፡፡ ወንድሜ እሱ ያዘዘለትን መድኃኒት ወሰደና ባሰበት፡፡ እንደገና ዶክተር ጆንስን ጠራነውና ወንድሜ እሱም ያዘዘውን መድኃኒት ወስዶ አሁንም ባሰበት፡፡ አይ፣ ሊያበቃለት ነው አልንና ዶክተር ጆርጅን ጠራነው፡፡ እሱ ሥራ በዝቶበት ስለነበር ሳይመጣ ቀረ፣ ወንድሜም ተሻለው፡፡”
“ዶክተሩ  ባለመምጣቱ ተሻለኝ…” ከማለት ያድነንማ፡፡ አንዳንድ ጊዜ አራት ዶክተር ዘንድ ሄደን የአንዱ የምርመራ ውጤት ከሌላው ጋር አልገጥም ሲለን እንዲህ ብንል አይበዛብንም፡፡
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ችግሩ ምን መሰላችሁ… የሚያማችሁን “ሀኪሙ ጨጓራህ ተልጧል አለኝ…” ብላችሁ ከተናገራችሁ በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ ስለራሳችሁ ህመም ‘አዳዲስ መረጃዎች’ ይደርሷችኋል፡፡
“ተሻለህ? አንጀቱ ቆስሎ እየተሰቃየ ነው ብለውኝ…?”
“አንተ፣ የጨጓራ አልሰር እንዳለብህ ሳትነግረኝ ከሌላ ሰው ልስማ!…”
“የምንድነው ካንሰር ይዞታል ብለውኝ… ምንህን ነው ያመመህ?”
እናላችሁ…የእናንተ ህመም የከተማው ሰበር ወሬ ሆኖ ይከርምላችኋል፡፡
ህመም የዶክተሩና የበሽተኛው ምስጢር መሆኑ ቀርቶ ‘የጋራ አጀንዳ’ ሲሆን…አለ አይደል… የዲዮጋን ፋኖስ የማይመጣባችሁሳ!
የሀኪም ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ…ዶክተሩ ለበሽተኛው… “እየተሻለህ ነው፡፡ ግራ እግርህ አብጧል፣ እኔን ግን አያሳስበኝም…” ይለዋል። በሽተኛው ብሽቅ ብሎ ምን ቢለው ጥሩ ነው… “ዶክተር የአንተም ግራ እግር ቢያብጥ ኖሮ እኔም አያሳስበኝም ነበር፣” ብሎት አረፈ፡፡
ሰው በበዛበት “የሰው ያለህ የሰው…” ከማለት ያድነንማ፡፡
ሰውየው ከሚስቱ ጋር መጠነኛ ግጭት ይገጥመዋል፡፡ አለ አይደል… ‘ጭር ሲል’ ሁለቱ መልሰው የሚስማሙበት አይነት ችግር፡፡ ግንላችሁ… በሆነ መንገድ “ተኳርፈዋል…” የሚል ወሬ አንዳችን ጆሮ ውስጥ ጥልቅ የለ… ምን አለፋችሁ…ልክ እንደ አጭር ልብ ወለድ ውድድር ሁላችንም የየራሳችንን ታሪክ እንጽፍና ለሚሰማ ጆሮ ሁሉ እንነግራለን፡፡ ባልና ሚስቱም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ራሳቸው እንኳን ስለረሱት ግጭት አዳዲስ መረጃዎች ይደርሷቸዋል፡፡
“እናንተ፣ እንዲህ አገር ሰምቶ ጉድ እስኪል ስትጋጩ ምነው ያልነገራችሁን! ጨፍረን ድረን ትደብቁናላችሁ!” (አይደለም አገር ሊሰማ… ጓዳ የነበረችው ሠራተኛቸው እንኳን አልሰማችም እኮ!)
“ስማ፣ በቃ ቆረጣችሁ ማለት ነው! ንብረት ልትካፈሉ ነው ሲሉ ሰማሁ፡፡”
“ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሷል አሉ፡፡ ይሄን ያህል ያጋጫችሁ ምንድነው?”
“የት ይደርስ የተባለ ትዳር እንዲህ ይሁን!”
ምን አለፋችሁ… ማታ ‘እነሆ በረከት’ መፍትሄ የሚበጅላት ኩርፊያ የከተማው መነጋገሪያ አጄንዳ ሆና ትከርምላችኋለች፡፡
የባልና ሚስት የጓዳ ነገር የእነሱ ምስጢር መሆኑ ቀርቶ ‘የጋራ አጀንዳ’ ሲሆን…አለ አይደል…የዲዮጋን ፋኖስ የማይመጣባችሁሳ!
ሰው በበዛበት “የሰው ያለህ የሰው…” ከማለት ያድነንማ፡፡
(ስሙኝማ…እግረ መንገዴን… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እዛ አማሪካን ውስጥ በ‘ቫለንታይን ዴይ’ ሰሞን የፍቺ ጥያቄ አርባ በመቶ ያድጋል የሚል ነገር አነበብን፡፡ የእኛ አገር ‘ጥሬ ሀቅ’ ይነገረንማ፡፡)
እናላችሁ…የተባለውም፣ ያልተባለውም እየተከተፈና እየተመነዘረ ነገሮች ሲጣመሙ ሰዋችን “መታፈር በከንፈር” ቢል አይገርምም፡፡ አንዳንድ ሰዎች… አለ አይደል… በመልስና በቅጣት ምት መካከል ያለውን ልዩነት እንኳን ሳያውቁ ስለ ‘አርሴና ማንቼ’ የሚያወሩት ሌላ ‘ቁም ነገር’ አጥተው አይደለም፡፡ ስለ አርሴና ማንቼ ማውራቱ በምንም መንገድ ለመጠምዘዝ አይመችማ! “ስማ እሱ ሰውዬ እኮ ያለውን ሰማህ! ሩኒን የሚስተካከለው የለም አለ አሉ፡፡ እኔ ከእነ….እንትና ጋር በህቡእ እንደሚሠራ እጠረጥረዋለሁ…” ምናምን አይባልማ፡፡
እሰየው ነው…ቢያንስ፣ ቢያንስ እስካሁን የአርሴና የማንቼ ነገር ከራሳችን ጉዳይ ጋር አያይዞ ለመፈረጅ አያመችማ!
እግረ መንገዴን…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…በቀደም አንዱ ወዳጃችንን ብዙም የማይቀርበው የሰፈር ሰው ሰላም ይለዋል፡፡ የሚሰማውን ከመናገር ወደኋላ የማይለው ወዳጃችን ደንገጥ ቢልም በበኩሉ ሰላም ይላል፡፡ ከዛማ ሰውየው ምን ቢለው ጥሩ ነው…“ማንን ነው የምትመርጠው?” ወዳጃችንም ሰውየው ምን እንደሚያወራ መጀመሪያ ግራ ገብቶት ነበር፡፡ በኋላ ነገሩን ሲረዳ ምን አለው መሰላችሁ…“ምን አገባህ!” አለው፡፡ አሪፍ አይደል! እናላችሁ… “ምን አገባህ!” ልንባል የሚገባን ሰዎች እየበዛን ሳንሆን አንቀርም፡፡
ምንም ነገር የመምረጥና ያለመምረጥ ጉዳይ የራሳችን የግል ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የማያገባው ዘው ሲልበት…አለ አይደል…የዲዮጋን ፋኖስ የማይመጣባችሁሳ!
ሰው በበዛበት “የሰው ያለህ የሰው…” ከማለት ያድነንማ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6027 times