Monday, 02 March 2015 10:53

23ኛ/ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጉባኤ.. February 9-10...ጅማ/

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በሀገራችን ያለው የሙያ ማህበራት ቁጥር ከጊዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ እነዚህ የሙያ ማህበራት ከአባላቱ ባሻገር ለሙያ ዘርፉ ብሎም ለሀገር እድገት የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በህክምናው ዘርፍ ከተቋቋሙ የሙያ ማህበራት መካከል የኢትዮፕያ ፅንስና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር አንዱ ነው፡፡ ማህበሩ ባለፈው ሳምንት ሀያ ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ደረጃውን የጠበቀ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስልጠናን ማሳደግ በሚል መሪ ቃል በጅማ ዩንቨርሲቲ አካሂዷል፡፡
ዶክተር ደረጄ ንጉሴ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ናቸው። የዚህ አመት ጉባኤ ደረጃውን የጠበቀ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስልጠናን ማሳደግ የሚለው መሪ ቃል የተመረጠበትን ምክንያት ሲናገሩ፡-
“የዚህን አመት ጉባኤ ደረጃውን የጠበቀ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስልጠናን ማሳደግ በሚል አካሂደናል። ይህን መሪ ቃል የመረጥንበት ዋናው ምክንያት የያዝነው አመትየምእተ አመቱ     የልማትግቦች ማብቂያ እንደመሆኑ በጤናውም ዘርፍ እየተሰራ ያለውን ስራ ለማስቀጠል የባለሙያውን አቅም መገንባት አስፈላጊ ነው ብለን ስለምናምን ነው፡፡
የምእተአመቱ ግብ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚኖረው የጤና አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ደረጃቸውን     የጠበቁ ባለሙያዎች ማፍራት አስፈላጊ ስለሆነ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ምክክር ለማድረግ ይህን መሪ ቃል መርጠን የዚህን አመት ስብሰባ አካሂደናል ነው፡፡
ለሶስት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ላይ አስራ ሁለት ያህል ጥናታዊ ፀሁፎች የቀረቡ ሲሆን ፅሁፎቹ በተለያዩ የስነተዋልዶ ጤና ችግሮች እንዲሁም ከማህፀንና ፅንስ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በገራችን ያለውን ሁኔታ መሰረት በማድረግ የተሰሩ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ፅሁፎች ከቀረቡ በኋላም አባላቱና ለሌሎች የስብሰባው ተሳታፊዎች ተወያይተውበታል፡፡   
በጉባኤው ላይ የክብር እንግዳ ነበሩት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ዳይሪክተር የሆኑት ዶክተር ወንድምአገኝ እምቢ አለ፣፣ ‘’Ministry of  Health’s plans and issues in light of scaling up quality Obstetrics and Gynecology training’’ በሚል እርእስ ደረጃውን የጠበቀ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስልጠናን ለማሳደግ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል የተያዘውን እቅድ ለተሰብሳቢዎች አቅርበዋል፡፡
ማህበሩ ከጤና ጥበቃ ጋር በመተባበር በእናቶች ጤና ላይ በተለይ በእርግዝናና በወሊድ ግዜ የሚከሰትን የእናቶች ሞት ለመቀነስ በትብብር እየሰራ እንደሆነና እንዲህ አይነት የሙያ ማህበራት በጤናው ዘርፍ የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከማህበሩ ጋር ያለውን ግንኙነት ከምንግዜውም በላይ አጠንክሮ እንደሚሰራ ዶ/ር ወንድማገኝ ገልፀዋል። ከጽንስና ማህጠን ሐኪሞች ማህር ጋር ባለው የስራ ግንኙነትም የሚከተሰለውን ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ፅንስና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር ከተመሰረተበት ከፈረንጆቹ 1992/ አመተ ምህረት ጀምሮ የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እየሰራ ያለ ማህበር ነው፡፡ ከጤና ጥበቃም ጋር በመተባበር የሚሰራቸው የተለያዩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ በቅርቡም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በጤናው ዘርፍ ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለእናቶች ሞት ትልቅ ምክንያት የሆነውን የክህሎት ችግር ለመቅረፍ የድንገተኛ የፅንስ ህክምና ባለሙያዎችን እያሰለጠንን ነው፡፡ ይህን ስልጠና ከጀመርን አምስት አመት ቢሆንም በበቂ ሁኔታ እየተተገበረ አይደለም። ስለዚህ ይህን ስልጠና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ከእነዚህ ባለሙያዎች ጋር በትትብር እየሰራን ነው፡፡”



የያዝነው የፈረንጆቹ 2015 የምእተ አመቱ የልማት ግቦች ወይም millennium development goals ማብቂያ አመት እንደ መሆኑ በጤናው ዘርፍ እስከአሁን የታዩት እመርታዎች ምን ይመስላሉ ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር ወንድማገኝ ምላሽ ሲሰጡም፡-
የምእተ አመቱን የልማት ግቦችን በማሳካት እረገድ የጤናው ዘርፍ ትልቅ እመርታ አሳይቷል ማለት ያቻላል። የዛሬ ሁለት አመት የህፃናትን ሞት በመቀነስ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ተሰጥቷታል፡፡ የእናቶችን ሞት በተመለከተም ለውጡ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ለእናቶች ሞት ትልቁ ምክንያት የሆነው የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ የጤና አገልግሎቱ ተጠናክሮ እያንዳንዷ እናት አገልግሎቱን ፈላጊ እንድትሆንና በጤና ተቋም እንድትወልድ ማድረግ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እየተሰራ ያለ ስራ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከዛሬ አምስት አመት በፊት 6% የነበረው በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር አሁን ወደ 20% አድጓል፡፡ ስለዚህ በበቂ ሁኔታም ባይሆን የምእተ አመቱን ግብ ማሳካት ችለናል።” ብለዋል፡፡ በጉባኤው ከነበሩ ክንውኖች መካከል የደም ልገሳ ፕሮግራም አንዱ ነበር፡፡ የስብሰባው ተሳታፊዎች በበጎፈቃደኝነት ደም ለግሰዋል፡፡ የደም ልገሳ ፕሮግራሙ ባለሙያዎቹ ከህክምና ስራቸው በተጓዳኝ ለህብረተሱ አለኝታ መሆናቸውን ለማሳየት ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ ይገልፃሉ፡፡
“ይህ የደም ልገሳ ፕሮግራም የተዘጋጀው ባለሙያዎች ከህክምና ስራው ባሻግር ለህብረተሰቡ አለኝታ መሆናቸውን ለማሳየት ሲባል ነው፡፡ ህብረተሰቡም ይህንን በማየት የደምን አስፈላጊነት ተረድቶ ህይወትን ለማዳን ሲባል ደም መስጠት እንዳለበት ለማስተማር ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡”
ዶክተር ሙኸዲን አብዶ የማህፀንና ፅንስ ሀክምና እስፔሻሊስትና የማህበሩ የቦርድ አባል ናቸው፡፡ የህክምና ባለሙያዎች በእንዲህ አይነቱ የደም ልገሳ ፕሮችራሞች ላይ መሳተፋቸው ለሌላው የህብረተሰብ ክፍል የሚሰጠው የተለየ ትርጉም እንዳለ ይገልፃሉ?፡፡
“ባለሙያ እንደዚህ አይነት የደም ልገሳ ፕሮግራም ላይ መሳተፍ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ከእኛ ከባለሙያዎች የበለጠ የደም እጦት የሚያደርሰውን ጉዳት የሚያውቅ የለም፡፡ ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል የደም መፈሰስ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ስለዚህ በተለይ እንደኛ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ላይ ያሉ ባለሙያዎች በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ ደም መለገስ ከምንም በላይ አስደሳችና ሊዘወተር የሚገባው ነው፡፡”
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ባላካቸው ንጋቱም የዶክተር ሙኸዲንን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡“እንደሚታወቀው የማህፀንና ፅንስ ሀኪሞች በአብዛኛው ከደም ጋር የተያያዘ ስራ ላይ ነው ያለነው። እናቶች በተለያየ ምክንያት ደም ይፈሳቸዋል ለዚህም ከየደም ባንኩ ብዙ ደም እንጠይቃለን፡፡ የምንጠይቀውን ደም እራሳችንም በተወሰነ መልኩ አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለብን ሁልግዜም አስብ ነበር፡፡ ስለዚህ ዛሬ እድሉን አግኝቼ ደም በመስጠቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ከምንሰጠው የህክምና አገልግሎች በተጨማሪም ማህበራዊ ግዴታችን ነው ብዬ አስባለሁ ተምሳሌትነቱም ለማህበራችን አባላት ብቻ ሳይሆን ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡”


Read 3756 times