Monday, 02 March 2015 10:49

12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ይጀመራል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና  በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት  በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል፡፡ ሻምፒዮናውን በብቃት ለማካሄድ አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታድዬም በ5 ሚሊዮን ብር  ወጭ ሙሉ እድሳት ተደርጎለታል፡፡ እድሳቱ የስታዲየሙ አጥር፣ የመጸዳጃ ቤቶች ማስፋፋት፣ የመብራት፣ የተመልካቾች መቀመጫዎች፣ የትንሿን ስታዲየም የአስፓልት ንጣፍ፣ የፖውዛ መብራቶች ያካተተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናውን በማስተናገድ ወደፊት ትልልቅ ውድድሮችን የማዘጋጀት ፍላጎቷን ታነቃቃለች፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት በሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ እና 12 ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማንቀሳቀስ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ስታድዬም ሙሉ እድሳትና ለውድድሩ አጠቃላይ መስተንግዶ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ  ለበጀት እንደተመደበም ታውቋል፡፡
በሻምፒዮናው ላይ ለመሳተፍ  33 የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን አባል አገራት ማረጋገጫ ልከዋል፤ 618 የአፍሪካ ወጣት አትሌቶች በሜዳ እና በትራክ ላይ በሚካሄዱ 40 የስፖርት ውድድሮች ይሳተፋሉ፡፡ በመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ውድድሮች የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በተለይ የኢትዮጵያ እና የኬንያ በፍፁም የበላይነት ፉክክር እንደሚገቡ  ሲጠበቅ፤ የምእራብ አፍሪካ አገራት አትሌቶች በአጭር ርቀት ውድድሮች እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ በሜዳ ላይ ስፖርቶች ብልጫ እንደሚኖራቸው በመገለፅ ላይ ነው፡፡ በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ኢትዮጵያ 100፣ ናይጀሪያ 97 ፣ ሴራሊዮን 37፣ ሞሮኮ 35፣ ሱዳን 33፣ዚምባቡዌ 31፣ ካሜሮን 28፣ ቱኒዚያ 26፣ ቡርኪናፋሶ 23፣ ኮንጎ ብራዛቢል 19፣ ኡጋንዳ 19፣ ሴኔጋል 16፣ዛምቢያ 14፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ 13፣ ሩዋንዳ 7 ፣ ሲሼልስ 17፣አንጎላ 14  ፣ሶማሊያ 13፣ ኬንያ 12፣ ማሊ 11፣ ማዳጋስካር 8፣ አልጀሪያ 8፣ናምቢያ 8 ፣  ጋቦን 6 ግብፅ 6፣  ሌሴቶ 5፣፣ኮትዲቯር 5፣  ኬቬርዴ አይስላንድ 3፣ ፣ ስዋዚላንድ 3 እና  ጊኒ ቢሳው 1፣  ስፖርተኞችን አስመዝግበዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ሞሪሽዬስ፤ ባምቦስ በተባለች ከተማዋ ባስተናገደችው 11ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ29 አገራት የተውጣጡ 223 አትሌቶች በ40 የስፖርት ውድድሮች ተሳትፈው ነበር፡፡  15 አገራትአንድና ከዚያም በላይ ሜዳልያ በማግኘት የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተው 119  ሜዳልያዎችን ሰብስበዋል፡፡ ናይጄርያ በ19 ሜዳልያዎች (9 የወርቅ፤ 7 የብርና 3 የነሐስ) አንደኛ ደረጃ ነበራት፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ24 ሜዳልያዎች  (7 የወርቅ፤ 9 የብርና 8 የነሐስ) ሁለተኛ ደረጃ ስትወስድ 41 አትሌቶችን አሳትፋ የነበረችው ኢትዮጵያ በ22 ሜዳልያዎች (7 የወርቅ፤ 7 የብርና 8 የነሐስ) ሶስተኛ ደረጃ አግኝታ ነበር፡፡ ግብፅ በ11 ሜዳልያዎች (5 የወርቅ፤ 4 የብርና 2 የነሐስ)፤ ኬንያ በ17 ሜዳልያዎች፤(4 የወርቅ፤ 9 የብርና 4 የነሐስ) እንዲሁም ኡጋንዳ በ4 ሜዳልያዎች (2 የወርቅ፤ 1 የብርና 1 የነሐስ) እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ አከታትለው ወስደዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በ11ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው 7 የወርቅ ሜዳልያዎች 6 ስድስቱን ያስመዘገቡት ሴቶች ሲሆን በወንዶች የተገኘው 1 የወርቅ ሜዳልያ ብቻ ነበር፡፡ እነሱም በ800 ሜትር ወንዶች በረከት ካህሳይ አዳነ፤ በ800 ሜትር ሴቶች አለም ገብረእግዚአብሄር፤ በ1500 ሜትር ሴቶች ዳዊት ስዩም፤ በ3000 ሜትር ሴቶች ሃፍታምነሽ ተስፋዬ ሃይሉ፤ በ5000 ሜትር ሴቶች ሩቲ አጋ ሶራ፤ በ3ሺሜትር መሰናክል ወየንሸት አንሳ ወልደፃዲቅ እንዲሁም በ5000ሜትር የርምጃ ውድድር አስካለ ቲካሳ በንቲ ናቸው፡፡

Read 2250 times