Monday, 02 March 2015 10:46

ደደቢትና ጊዮርጊስ በባህርዳር ስታድዬም ይፋለማሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በ2015 የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ቅድመ ማጣርያ ደደቢትና ቅዱስ ጊዮርጊስ   ዛሬ እና ነገ በባህርዳር ስታድዬም የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ከ2 ሳምንት በፊት የመጀመርያ ጨዋታቸውን ከሜዳ ውጭ ያደረጉት ሁለቱ ክለቦች ወደ 1ኛ  ዙር ማጣርያ ለመግባት  እድል አላቸው፡፡ 50 ሺህ ተመልካች የማስተናገድ አቅም ያለው የባህርዳር ስታድዬም   ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲያስተናግድ ከአፍሪካ እግር ኳስ  ኮንፌዴሬሽን እውቅና አግኝቷል፡፡ስታዲየሙ  የእግር ኳስ  ሜዳን ጨምሮ ሌሎች ሁለገብ ሩጫ፣ውርወራን፣ዝላይን ያካተተ የስፖርት ማዘውተሪያ እንዲኖረው ተደርጎ ተሰርቷል፡፡ 21 ሜትር ከፍታ ያለው ይህ ግዙፍ ስታዲየም በ2ኛ የግንባታ ምእራፉ 27ሄክታር ቦታ ላይ የሚያርፍ ግዙፍ የስፖርት መንደር  ይሰራለታል፡፡ አጠቃላይ ወጪው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች ከቅደመ ማጣርያ አንስቶ በ1ኛ እና በሁለተኛ ዙር ማጣርያዎች ውጤታማ በመሆን ወደ የምድብ ማጣርያዎች ለመግባት ከባድ ፈተና ገጥሟቸው ቆይቷል፡፡በተለይ በቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቻቸውን ማለፍ ከቻሉ በኋላ ወደ አንደኛ ዙር የማጣርያ ውድድር ሲሸጋገሩ ከሰሜን  እና ምዕራብ አፍሪካ ክለቦች በጥሎማለፍ ለደርሶ መልስ ጨዋታዎች እየተደለደሉ በዚህ ምእራፍ የሚገጥማቸውን ፉክክር ማለፍ ይከብዳቸዋል፡፡ ደደቢት በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ሲሳተፍ ዘንድሮ አራተኛው ነው፡፡
በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ብቸኛውን ተሳትፎ በ2014 እኤአ ላይ እንዲሁም ለሁለት ጊዜያት ደግሞ በ2011 እና በ2013 እኤአ ላይ በኮንፌደሬሽን ካፕ በመሳተፍ ውጤቱ በ1ኛው ዙር ማጣርያ ላይ በመሰናበት ተወስኖ ቆይቷል፡፡ አንጋፋው የኢትዮጵያ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ከ20 በላይ የውድድር ዘመናትን ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በአዲስ መዋቅር መካሄድ ጀምሮ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ዘንድሮ ሲሳተፍ 10ኛው ተሳትፎ ይሆናል፡፡ ባለፉት 9 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው ለ3 የውድድር ዘመናት ተሳትፎው በቅድመመማጣርያ ላይ ሲወሰን በ6 የውድድር ዘመናት እስከ 1ኛ ዙር ማጣርያ ብቻ ተጉዟል፡፡
በ8ኛው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ደደቢት ከሜዳው ውጭ የሲሸልሱን ኮት ዲ ኦርን በስታደ ደ አሚቴ 3ለ2 በሆነ ውጤት አሸንፎ ነበር፡፡ ዛሬ በባህርዳር በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ  በማንኛውም ውጤት አቻ መለያየት እና ማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፈዋል፡፡ ደደቢት በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የሚመራ ሲሆን የሲሸልሱን ክለብ ኮትዲኦር ባሻነፈበት ጨዋታ ሁለት ጎሎችን ዳዊት ፍቃዱ ከመረብ ሲያሳርፍ ናይጄሪያዊው 3ተኛውንና የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል፡፡  ዛሬ ደደቢት የሲሸልሱን ኮት ዲኦር ጥሎ ካለፈ ከቡርኪናፋሶው አርሲ ሮቦ ወይም ከናይጄርያው ዋሪ ዎልቭስ አሸናፊ ጋር በ1ኛ ዙር ማጣርያ የሚገናኝ ይሆናል፡፡በሁለቱ ክለቦች የቅድመ ማጣርያ  ጨዋታ የናይጄርያው ክለብ በሜዳው 1ለ0 እንዳሸነፈ ታውቋል፡፡
በ19ኛው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ በኤምሲ ኤል ኡልማ የተሸነፈው 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት ነበር፡፡ ነገ በባህርዳር በሚያደርገው የመልስ ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2 ንፁህ ጎሎች ካሸነፈ ወደ ቀጣዩ የአንደኛ ዙር ማጣርያ ያልፋል፡፡ በአንደኛ ዙር ማጣርያ ከጋናው አሻንቲ ኮቶኮ ጋር ሊገናኝ እንደሚችልም ታውቋል፡፡ የጋናው ክለብ በቅድመማጣርያው ከኢስት ላንድስ ጋር ተደልድሎ የነበረ ቢሆንም የሴራልዮኑ ክለብ ከውድድሩ በመውጣቱ በፎርፌ ሊያልፍ ችሏል፡፡
የፖርኩፒን ጦረኞች ተብሎ የሚጠራው የጋናው ክልብ አሻንቲ ኮቶኮ፤ ከተመሰረተ ከ82 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ አሻንቲ ኮቶኮ በጋና ፕሪሚዬር ሊግ ለ24 ጊዜያ ሻምፒዮን በመሆን የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን ያስመዘገበ ሲሆን ከአፍሪካ የኛው ክፍለዘመን ምርጥ ክለቦች አንዱ ሆኖ የተመዘገበ እንዲሁም በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ለሁለት ጊዚያት አሸናፊ በመሆን በውድድሩ  የከፍተኛ ውጤት ታሪክ በ7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

Read 1813 times