Monday, 02 March 2015 10:35

“እንካችሁ አደራ” ዛሬ፤ “ያልጠራ ደም” ነገ ይመረቃሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

የገጣሚ ራሄል ተሾመ “እንካችሁ አደራ” የግጥም መድበል ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ አምስት ኪሎ ብሄራዊ ሙዚየም ጀርባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መድበሉ 65 ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን ገጣሚዋ በአገር ቤት፣ በጃፓንና በአሜሪካ ቆይታዋ ያካበተቻቸውን የህይወት ተመክሮዎች በሳቅና በቁም ነገር፣ በተግሳፅና በምክር በግጥም መልክ ለአንባብያን በአደራ መስጠቷን በማስታወሻዋ ገልፃለች፡፡ በ110 ገፆች የተቀነበበው መድበሉ፤በ30 ብር ይሸጣል፡፡
በሌላ በኩል በደራሲ እነዬ ሺበሺ የተጻፈው “ያልጠራ ደም” ረጅም ልቦለድ መፅሀፍ ነገ ጠዋት ከ3፡00 ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ይመረቃል፡፡ ዋና ጭብጡን የደም ውርስ ላይ አድርጎ በርካታ ከደም ውርስ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን የሚዳስሰው መፅሀፉ፤ የደራሲዋ ሁለተኛ ስራ ሲሆን ከዚህ ቀደም “የገቦ ፍሬ” የተሰኘ ረጅም ልቦለድ መፅሀፍ ማሳተሟ ይታወቃል፡፡ በ317 ገጾች የተቀነበበው “ያልጠራ ደም”፤ ሰሞኑን በ65 ብር ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡  
በአክመል ተማም የተዘጋጀው “ዩኒቨርሳል” የተሰኘ በሥነ ክዋክብት ምርምር ላይ የሚያጠነጥን መፅሀፍም ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መፅሀፉ በአራት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን ስለ ከዋክብት፣ሚልኪዌይ፣ ጋላክሲ፣ ፀሐይና ሌሎች ፕላኔቶች በስፋት ይዳስሳል፡፡ ቁስ አካልንና ጨረርን እንዲሁም በእነሱ የተያዘውን ቦታ ጭምር ስለሚጠቀልለው ዩኒቨርሰ የሚተነትን ሲሆን በአስትሮኖሚና አስትሮሎጂ ዙሪያ ያለውን ብዥታም ለማጥራት ይሞክራል፡፡ በ123 ገጾች የተቀነበበው መጽሃፉ፤ በ35 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

Read 1452 times