Monday, 02 March 2015 10:20

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

በሁለት ድንጋይ
ልሰህ እንዳትጨርሰኝ -
እጅግ አልጣፈጥኩም
አንቅረህ እንዳትተፋኝ -
እሬት ብቻ አልሆንኩም
ሁሌም እባብ ሆኜ -
በልቤ አልተሳብኩም
እንደእርግብ ታምኜም -
ከታዛ አልበረርኩም
በሁለት ድንጋዮች -
አንዲት ወፍ ልመታ
አነጣጥሬያለሁ -
እየኝ በለዘብታ፡፡

ንገረኝ ሳኩራ
እንደ አገሬ አደይ ቀለመ ደማቁ
እንደ መስኩ ንጣፍ ህብረ ፍልቅልቁ
ደመናው ማለፉን ጉሙ መገፈፉን
የጨቀየው ቀዬ በብራ መግፈፉን
ትተህ ክፉ ክፉን
አውጋኝ ደግ ደጉን፡፡
ይቺ ምስኪን ነፍሴ የምስራች ናፍቃ
በ-ብ ---ዙ ተጨንቃ
ትለምንሃለች ልቧ እየደወለ
ርዳ ተርበድብዳ ሰው እንደገደለ፡፡
ጣቷ ተቆላልፎ
ሆዷ ተንሰፍስፎ
አይኗም የብሶቱን የጨው ውሃ አርግፎ
ት-ማ-ጠ-ን-ሐ-ለ-ች
እያሽቆጠቆጣት የጃፓን ክረምቱ
አል-ገፋ ብሏት ጠንቶባት በብርቱ፡፡
የአገራችን አደይ ክረምትና በጋ
እርቃለችና አትሔድም ፍለጋ
ምላሽ አትንፈጋት እባክህ ሳኩራ
እንደ ቅርንጫፍህ እሷም ተንጨባራ
ክርችው! እንዳትለው በቁሟ በድና
መቼ ነው ንገራት ጥጡስ የሚያባራው የጃፓን ክረምቱ
እንኳንስ ለመጤው ለራሱም አልሳሳ አልተፈታ ፊቱ፡፡
ወይም አስተምራት እንዳንተ ጽናቱን
አረንጓዴ ቅጠል፤ ቅርንጫፍ አርግፎ፤ ሞቶ መነሳቱን፡፡
በራሔል አሸናፊ
“እንካችሁ አደራ” ከተሰኘው የግጥም መድበሏ - የካቲት 2007 ዓ.ም)

Read 3779 times