Saturday, 14 January 2012 12:12

ኢራንና ቬኔዝዌላ ወዳጅነታቸው ጠንክሯል

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(0 votes)

የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ አገር” - የብራዚሏ ፕሬዚዳንት

መካከለኛው ምሥራቅ ለዘመናት ከፖለቲካ ቀውስ፣ ከሃይማኖት ውዝግብ፣ ከድንበር ግጭት፣ ከርዕዮተ - ዓለም ልዩነት እና ከጦርነት ተለይቶ አያውቅም፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት የፍልስጤሞች ግዛት የነበረውና ዛሬ እስራኤል የያዘችው ቦታ እ.ኤ.አ በ1947 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት የአይሁዶችና የፍልስጤሞች መኖሪያ እንዲሆን ከወሰነ ከአንድ አመት በኋላ እስራኤል ሉዓላዊ አገር መሆኗን አስታወቀ፡፡ አሜሪካና እንግሊዝ የተባበሩት መንግስታትን ውሳኔ ወዲያው ሲቀበሉ ሁሉም የአረብ አገራት ቦታው የፍልስጤሞች መኖሪያ እንጂ የአይሁዶች አይደለም በማለት ተቃውሞ አቀረቡ፡፡ በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተባብረው በእስራኤል ላይ ጦርነት ከፈቱ፡፡ ነገር ግን በጦርነቱ እስራኤል አሸነፈች፡፡ እ.ኤ.አ በ1967 ዓ.ም በድጋሚ ጦርነት አስነሱ፤ አሁንም እስራኤል አረቦችን አሸነፈች፡፡ የስድስቱ ቀን ጦርነት በመባል በሚጠራው በዚህ ጦርነት እስራኤል ተጨማሪ ግዛቶችን ያዘች፡፡

ከግብጽ የሲና ፔኔንሱላንና የጋዛ ሰርጥን፤ ከዮርዳኖስ፣ ዌስት ባንክንና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን፣ ከሶሪያ የጐላን ተራራ ጠቅልላ የራሷ ግዛት አደረገች፡፡

እስራኤል እ.ኤ.አ በ1979 ዓ.ም ከግብጽ ጋር በካምፕ ዴቪድ የሰላም ስምምነት ካካሄደች በኋላ በአረቦችና በእስራኤል መካከል ያለው ግጭት ጋብ አለ፡፡ ይሁን እንጂ በአካባቢው ላይ የተለኮሰው እሳት መልኩን እየቀያየረ በተለያየ ጊዜያት መቀጣጠሉን አላቆመም፡፡ መካከለኛው ምሥራቅ (Middle East) የሚለውን መጠሪያ ያወጣው የተባበሩት መንግስታት ሲሆን፤ ይኸውም ከሩቅ ምሥራቅና ከፓስፊክ ኢሲያ አገራት ለመለየት ታስቦ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ መካከለኛ ምሥራቅ የሚባለውና በምዕራብ ከግብጽ ጀምሮ በምስራቅ እስከ ኢራን ድረስ፣ እንዲሁም በሰሜን ከቱርክ አንስቶ እስከ ደቡብ የአረቢያን ልሳነ ምድር (Arabian Peninsula) ያለውን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የታሪክ ምሁራን የሰሜን አፍሪካ ሙስሊሞችና አፍጋኒስታንም መካተት አለባቸው ይላሉ፡፡ በዓለም ላይ ዋና ዋና ሃይማኖቶች የሆኑት የሙስሊም፣ የክርስትና እንዲሁም የአይሁድ እምነት ምንጭ የሆነው መካከለኛው ምሥራቅ ከ30 በላይ ቋንቋዎች ይነገሩበታል፡፡ የዓለማችን የሥልጣኔ ምንጭ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላ በአረብ ብሔረተኝነት፣ በሃይማኖት ጽንፈኝነት (Sectarianism) እና በኢምፔሪያሊዝም አመለካከት እርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በተለያየ ጊዜያት ለውጥን ለማምጣት የተንቀሳቀሱ ኃይሎች በአካባቢው ላይ ሰላም ከማምጣት ይልቅ አዲስ አይነት ግጭት አስነስተዋል፡፡ ፀረ ምዕራባዊ ከሆኑት ከግብፃዊው ከጋማል አብዱልናስር እስከ ኢራናዊው አያቶላ ኮሜኒ፣ ከሳዳም ሁሴን እስከ አህመዲን ነጃድ ድረስ በአካባቢው ላይ ሰላምን በማደፍረስ ተንቀሳቅሰዋል፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ ዙሪያ ጥናት ያካሄዱ የታሪክ፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ምሁራን በአካባቢው እጅግ ውስብስብ የሆነው የጂኦ ፖለቲካ ውዝግብ አገራቱን ከማመሱ በተጨማሪ መፍትሔ ወደሌለው ግጭት እንዲያመሩ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ በተለይ አገራቱ ዋነኛ የነዳጅ አምራች መሆናቸው ለግጭቱ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ምሁራኑ ያብራራሉ፡፡

በተለያየ ጊዜያትም ነዳጅን ለፖለቲካ ዓላማ ተጠቅመውበታል፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ በ1973 ዓ.ም በእስራኤል ላይ ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት ከፍተው ሽንፈት ሲገጥማቸው፣ አሜሪካ እስራኤልን ትደግፋለች በሚል የነዳጅ አምራች አገራት (OPEC) የነዳጅ ማዕቀብ በመላው ዓለም ላይ ጥለው ነበር፡፡ የነዳጅ ማዕቀቡን ተከስትሎም በዓለም ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ በወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሄነሪ ኪሲንጀር ከኦፔክ አባል አገራት ጋር በሳል የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት በማድረጋቸው እንዲሁም እስራኤል በአሜሪካ ጥያቄ የሲና ፔኔንሱላን ለቃ ከመውጣቷ ጋር ተጨምሮ ከአንድ አመት በኋላ ማዕቀቡን አንስተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካና ኢራን በኒውክሊየር መሣሪያ ዙሪያ ከጀመሩት እሰጥ አገባ በኋላ አሜሪካ በድጋሚ ማዕቀብ ከጣለች ኢራን የሆርሙዝ የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያን እንደምትዘጋ መግለጿ ይታወሳል፡፡ ይህም የአካባቢውን ውጥረት የበለጠ ሊያባብስ የሚችልና በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዘይት ማሻቀብንና የኢኮኖሚ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጿል፡፡

አለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ኢራን 20 በመቶ ዩራኒየም የተባለውን ንጥረ ነገር ማበልፀጓን ሲገልጽ ይህም የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት ለመሆን ያስችላታል ብሏል፡፡

ኢራን የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት ከሆነች የበለጠ አደገኛ አዝማሚያ ልትፈጥር እንደምትችል የምትገልፀው አሜሪካ፣ በተለይም በእስራኤል ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚል ስጋት እንዳላት ገልፃለች፡፡ ከዚህም በመነሳት አሜሪካና እስራኤል ከኢራን ወደ እስራኤል ሊለቀቅ ይችላል ያሉትን የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳየል (Long Range Ballastic Missile) ለመመከት ኦስቲር ቻሌንጅ የተባለ ፀረ - ሚሳየል ፕሮጀክት በእስራኤል ውስጥ ገንብተዋል፡፡

ኢራንን ከኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ውጪ አድርጐ ማየቱ የማይታሰብ ነው የሚሉ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች፤ አሜሪካም ሆነች ምዕራባዊያን ኢራንን ከኒውክሊየር መሣሪያ ውጭ ማሰብ አቁመው ከእነ ኒውክሊየሯ የዓለምአቀፍ ማህበረሰብ አካል አድርገው ሊቀበሏት ይገባል ይላሉ፡፡ ይህ ግን ለአሜሪካ የሚዋጥላት አይደለም፡፡

ለኢራን የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን ማለት ደግሞ ትልቅ ገፅታን የሚፈጥርና የአገሪቱን ብሔራዊ ማንነት ቀመር የሚያስተካክል፤ እንዲሁም በታሪክ ውስጥ ያላትን የታላቅ አገርነት ስሜትና ፍላጐት ማዕከል ያደረገ ነው፡፡

ከብዙ ሺህ ዘመናት በፊት አሜሪካ የምትባል አገር ገና ሳትወለድ የአህመዲን ነጃድ አገር ኢራን የዓለማችን ኃያል አገር ነበረች፡፡ ከ1935 ዓ.ም በፊት ፐርሺያን በመባል የምትታወቀው ኢራን ከክርስቶስ ልደት በፊት በ550 ዓ.ዓ ቂሮስ በተባለው መሪያቸው መሪነት ባቢሎናዊያንን ድል በማድረግ ኃያልነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ይሁንና በ331 ዓ.ዓ ፐርሺያ በታላቁ እስክንድር ስትሸነፍ ግሪክ የዓለም ኃያልነትን ተረከበች፡፡

ታዲያ አህመዲን ነዳጅ እንደ ጥንቱ የአገራቸው ኃያል እንደ ቂሮስ ወይም እንደ ቅርቡ የኢራን እስላሚክ አብዮት መስራች አያቶላ ኮሚኒ የኢራንን ኃያልነት ለዓለም ለማስተዋወቅ ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ፡፡

ዛሬም በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ራሷን ኃያል አገር አድርጋ የምትቆጥረው ኢራን፤ በአካባቢው ላይ የበለጠ ተጽእኖ ለመፍጠር የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ የአረብ ዝርያ የሌላት ከመሆኑ ሌላ በ16ኛው ክ/ዘመን የሺያት ሙስሊም ሃይማኖታዊ ዶግማን ያስተዋወቀውን ሺአ እስማኤልን ቲኦክራሲያዊ አስተምህሮ የምትከተል ሲሆን፣ ከሶሪያ መንግስት በስተቀር አብዛኛው የመካከለኛው ምስራቅ አገራት መንግስታትም ሆኑ ሕዝቦች የሱኒ ሙስሊሞች በመሆናቸው የኢራኑ ሺያት መንግስት ተቃራኒ ናቸው፡፡ በመሆኑም ኢራን ከብዙዎች የሙስሊም መንግስታት በተለይም ከሳውዲ አረቢያ ጋር ሆድና ጀርባ ነች፡፡ በሶሪያ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽ ኢራን የሶሪያን መንግስት ሲደግፍ ሳውዲ አረቢያ ደግሞ ሕዝባዊ አመጽ አድራጊዎቹን ትደግፋለች፡፡ በተመሳሳይ በባህን በተቀሰቀሰው አመፅ ኢራን ሕዝባዊ አመፅ አድራጊዎችን ስትደግፍ ሳውዲ አረቢያ ደግሞ የባህሬንን መንግሥት ደግፏል፡፡ ኢራን በአካባቢው ላይ የበላይነት በመቀዳጀት የእስራኤልን ኃያልነት ለማዳከም ከሱኒ ሙስሊም መንግስታት ይልቅ መሠረታቸው ሺያት እንደሆኑ የሚነገረውን የሶሪያ አለዊያትስ ሙስሊም መንግስት ይዛ ለመንቀሳቀስ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፡፡

ይሁንና በበሽር አል-አሳድ ላይ የተቀጣጠለው እሳት በመባባሱ ወይ ዛሬ ወይ ነገ ድንገት ከጣላቸው ያለ አጋር ብቻዋን ልትነጠል መሆኑ የገባት ኢራን፤ ፊቷን ወደ ደቡብ አሜሪካ አገራት አዙራለች፡፡

አህመዲን ነጃድ የቁርጥ ቀን ልጅ ወደሚሏቸው የቬኔዙዌላው ፕሬዚዳንት ሁጐ ቻቬዝ ያቀኑትም የጋራ ጠላታቸው ከሆነችው ከአሜሪካ የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት በጋራ ለመመከት ነበር፡፡ የአለማችን “እብድ መሪ” እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቬኔዙዋላው ቻቬዝ፤ አህመዲን ነጃድን በመዲናቸው በካራካስ ሲቀበሏቸው ፍንድቅድቅ ብለው ነበር፡፡

ሁለቱም መሪዎች አሜሪካ በኢራን ላይ የምታደርገውን ዛቻና ማስፈራራት ያወገዙ ሲሆን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ደባ ይከሽፋል በማለትም ገልፀዋል፡፡ ሁጐ ቻቬዝ ባደረጉት ንግግርም “በእኔና በአህመዲን ነጃድ መገናኘት ሰይጣኖች እብድ ይሆናሉ” በማለትም ተሳልቀዋል፡፡ ቬኔዙዌላ የነዳጅ አምራች አገር (OPEC) አባል ስትሆን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከፍተኛ ነዳጅ ማምረት ጀምራለች፡፡

በተጨማሪም በምዕራባዊያን ሲተዳደር የነበረውን የወርቅ ማዕድን በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆን ያደረጉት ቻቬዝ፤ ለምዕራባዊያን ከአህመዲን ነጃድ የበለጠ ጥላቻ አላቸው፡፡ በ2008 የተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤት ውስጥ “መሀከላችን አንድ ሰይጣን አለ” በማለትም ጆርጅ ቡሽን ዘልፈዋቸው ነበር፡፡ አሁንም ሰይጣኖች የሚሉት አሜሪካንና ምዕራባዊያንን ነው፡፡ ቻቬዝ በኢራን ላይ ማዕቀብ በድጋሚ ከተጣለ ኢራን የምትፈልገውን ነገር ሁሉ አገራቸው ልታቀርብ እንደምትችል ለወዳጃቸው ለአህመዲን ነጃድ ቃል ገብተውላቸዋል፡፡ ኢራን ከቬኔዙዌላ ጋር ብቻ ሳይሆን ከብራዚል፣ ከቺሊ፣ ከኡራጋይ፣ ከቦሊቪያ እና ከአርጀንቲና ጋርም ወዳጅነቷን አጠናክራለች፡፡ በተለይም ከብራዚል ጋር የንግድ ግንኙነታቸውን እያሳደጉ የመጡ ሲሆን፣ በ2011 ዓ.ም 2 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የንግድ ልውውጥ ተካሂዷል፡፡ ወደፊትም ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ተስማምተዋል፡፡

አዲሷ የብራዚል ፕሬዝዳንት ኢራንን የ”ዓለማችን ዋነኛ ተጽእኖ ፈጣሪ አገር” በማለት ያሞካሿት ሲሆን፣ ለአህመዲ ነጃድ ጥንካሬም አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን የዋይት ኃውስ ባለስልጣናት ብራዚል ከኢራንና ከአሜሪካ አንዱን እንድትመርጥ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ሆርሙዝ

ለመላው ዓለም ከሚቀርበው የነዳጅ ዘይት ውስጥ መካከለኛ ምሥራቅ አገራት ከፍተኛውን የነዳጅ ዘይት ይሸፍናሉ፡፡ በ2010 ብቻ በቀን ለዓለም ከቀረበው 82.1 ሚሊዮን በርሜል የነዳጅ ዘይት ውስጥ 30 በመቶውን አቅርበዋል፡፡

በዓለም ላይ ከሚሰራጨው የነዳጅ ዘይት ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሚጓጓዘው በባህር ሲሆን፤ ይህም በሶስት የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ ቱቦዎች ይጓጓዛል፡፡ ሁለቱ ያሉት በመካከለኛው ምሥራቅ ሲሆን፣ አንዱ ደግሞ በኦማንና በኢራን መካከል የሚገኘውና 6.4 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሆርሙዝ በመባል የሚጠራው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ነው፡፡

ይህ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ከሳውዲ አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ፣ ከኩዌት፣ ከኢራን፣ ከኢራቅ እና ከኳታር የሚመጣው የነዳጅ ዘይት የሚያልፍበት ሲሆን የዓለማችን 40 በመቶ ነዳጅ ያልፍበታል፡፡

በመሆኑም አሜሪካ በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል ዝግጅት እያደረገች ባለችበት ወቅት፣ ኢራን የሆርሙዝ የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያን ልትዘጋው እንደምትችል መግለጿ በአሜሪካና በምዕራባዊያን ከፍተኛ ድንጋጤን መፍጠሩ አይዘነጋም፡፡

በኢራን ባለሥልጣናት መግለጫ የተደናገጠችው አሜሪካ ለኢራን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እያስተላለፈች ትገኛለች፡፡ በቅርቡ ከዋይት ኃውስ የወጡ መግለጫዎች ደግሞ ኢራን የሆርሙዝ ነዳጅ ማስተላለፊያን ለመዝጋት ከተንቀሳቀሰች የከፋ ችግር ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ከ20 ዓመት በፊት በባህረ ሰላጤው ጦርነት በባህሬን የከተመው የአሜሪካ ጦር በሕንድ ውቅያኖስ፣ የአማንን ባህረሰላጤና ሕንድ ውቅያኖስን ፀጥታና ደህንነት በበላይነት የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት በመግለጽ ኢራን የሆርሙዝ የነዳጅ ማስተላለፊያን ለመዝጋት ካሰበች እርምጃ ለመውሰድ እንደሚንቀሳቀስ በባህሬን የአሜሪካ ጦር አዛዥ ለሮይተር ተናግረዋል፡፡

በኢራንና በምዕራባዊያን መካከል ውጥረት እያየለ በመጣበት በዚህ ጊዜ እስራኤል በኢራን ላይ ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ ወታደራዊ ጥቃት ልትከፍት ትችላለች የሚል ስጋትም ተፈጥሯል፡፡

እስራኤል ከዚህ በፊት ባግዳድን፣ ደማስቆን ሊባኖስን እንዲሁም ቴህራንን ለአሜሪካ መረጃ ሳትሰጥ በሚስጥር ደብድባ የተመለሰች ሲሆን፣ አሁንም ለዋይት ነውስ ፍንጭ ሳትተው ኢራንን ልትደበድብ ትችላለች ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል እስራኤል ኢራን እያካሄደች ያለውን የኒውክሊየር መሣሪያ የሚገኝበትን ቦታ ለማወቅ በአሜሪካና በእንግሊዝ የታገዘ የሳይተላይት ምርመራ እያካሄደች ትገኛለች፡፡

መፍትሔም መቋጫም የማይገኝለት የመካከለኛው ምሥራቅ ውዝግብ የበለጠ እየተባባሰ በመጣበት በዚህ ጊዜ የኢራን የኒውክሊየር ሳይንቲስት መገደል ሁኔታውን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሄድ አድርጐታል፡፡ ኢራን የሳይንቲስቷን መገደል ተከትሎ ግድያውን የፈፀሙት አሜሪካና እስራኤል ናቸው ብትልም የሁለቱም አገራት ባለስልጣናት አስተባብለዋል፡፡ በአሜሪካና በኢራን የተፈጠረውን የኃይል አሰላለፍ ተከትሎ ቻይናና ሩሲያ የኢራን አጋርነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡

 

 

Read 5564 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 12:21