Monday, 02 March 2015 09:59

ፎርጅድ መድሃኒቶች - የአለማችን ቀጣይ የጤና ቀውስ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

ፎርጅድ መድሃኒቶችን ከትክክለኞቹ ለመለየት አስቸጋሪ ሆኗል

እንደ አለም ጤና ድርጅት (WHO) ትርጓሜ፡- መድሃኒቶች በሽታን ለማከም፣ ለማስወገድና ከመፈጠራቸውም በፊት ለመከላከል እንዲያስችሉ ተደርገውና ለህመምተኞች በሚስማማ መልኩ ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች ናቸው፡፡ አንድ መድሃኒት ሊያስብለው የሚያስችለውን ንጥረ ነገር በተገቢው መጠን አሟልቶ መያዝ ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን መድሃኒቱን ፈዋሽነቱንና ደህንነቱን አጥቷል ይባላል፡፡
አንድ መድሃኒት የቤተሙከራ ዘመኑን ጨርሶ እስኪመረትና ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ከ10-15 ዓመት ሊፈጅ ይችላል፡፡ የመድሃኒቱ ፈጣሪ ኩባንያ መድሃኒቱን እራሱ እያመረተ ሊያሰራጭ አሊያም ደግሞ ከሌሎች የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋር በሚያደርገው ስምምነት መሠረት ኩባንያዎቹ የመድሃኒቱን ደረጃ ጠብቀው እንዲያመርቱ ሊያደርግ ይችላል፡፡ መድሃኒቱ በየትኛውም ካምፓኒ ቢመረት የመድሃኒቶች የአመራረት ሂደት ጥራቱ አለማቀፋዊ መመዘኛ ያሟላ እንዲሆን የሚያስችል ስርዓት መከተል ግድ ይለዋል፡፡ ይህንን ስርዓት የያዘ መፅሃፍ “ፋርማ ኮፒያ” ይባላል፡፡ በየትኛውም የመድሃኒት ማምረት ሥራ ላይ የተሰማራ ኩባንያ መድሃኒቱን ያመረተው የየትኛውን አገር “ፋርማ ኮፒያ” ተጠቅሞ እንደሆነ መግለፅ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ሁኔታ መድሃኒቶቹ የመድሃኒት አመራረት ሂደቱን ተከትለው መመረት አለመመረታቸውን ለመመዘንና አለማቀፋዊ ደረጃውን የጠበቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡
እነዚህን በአለማችን ባሉ የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች እየተመረቱ የሚሰራጩና በጥቅም ላይ የሚውሉ መድሃኒቶች በህገወጥ መንገድ በፎርጅድ ተመሳስለው እየተፈበረኩ ገበያ ውስጥ መግባታቸው አዲስ ጉዳይ ባይሆንም ሁኔታው ዛሬ ዛሬ የአለም አገራትን ስጋት ላይ የጣለ ጉዳይ ሆኗል፡፡ እነዚህን መድሃኒቶች በህገወጥ መንገድ እያመረቱ ወደ ገበያ ውስጥ የሚያስገቡ ህገወጥ አምራቾች ቀደም ሲል አላማቸው ገንዘብ ማካበትና ዶላር መዛቅ ሆኖ የቆየ ቢሆንም ይህ አላማና ግባቸው አሁን አሁን ለአሸባሪዎች መጠቀሚያነት እንዲውሉ ያደርጋቸዋል የሚል ሥጋት ማጥላቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የአሜሪካው የመድሃኒት ጥራት ቁጥጥር ቢሮ በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በህገወጥ መንገድ እየተፈበረኩ ወደተለያዩ አገራት የሚሰራጩና ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረጉ ፎርጅድ መድሃኒቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ አገራት ከውጪ አገር ወደየአገራቸው የሚያስገቧቸውን መድሃኒቶች ጥራትና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የፍተሻ አሠራር የሌላቸው በመሆኑ መድሃኒቶች በህገወጥ መንገድ ወደ አገራቸው እንዲገቡ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁኔታም አሸባሪዎች ለሚፈልጉት የሽብር ተግባር ለመጠቀም ከሚመርጧቸው መንገዶች አንዱ ህገወጥ የመድሃኒት ምርትና ስርጭት ይሆናል የሚል ከፍተኛ ሥጋት አሣድሯል ብሏል፡፡ እንደ አሜሪካው የመድሃኒት ጥራት ቢሮ ገለፃ፤ በህገወጥ መንገድ ተመርተው የሚሰራጩት መድሃኒቶች የሚመረቱት ከህጋዊውና ትክክለኛውን የአመራረት ሂደት ተከትለው ከሚመረቱና ከሚሰራጩት መድሃኒቶች ጋር ፍፁም ተመሣሣይ እንዲሆኑ ተደርገው ነው፡፡ እነዚህን ህገወጥ መድሃኒቶች እንኳንስ ስለመድሃኒቶች አይነትና አሠራር በቂ ዕውቀት የሌለውን ተጠቃሚ ቀርቶ በሙያው ውስጥ ያሉና ዕውቀት አላቸው የሚባሉ ሰዎችን የሚያሣስቱና በማየት ብቻ ለመለየት የሚያስቸግሩ ፍፁም ተመሳሳይ ናቸው፡፡
ታዲያ እነዚህ መድሃኒቶች በተጠቃሚዎቻቸው ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከከፋ የአካልና የአዕምሮ ጤና ችግር እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ነው፡፡
እንደ አሜሪካው የመድሃኒት ጥራት ቁጥጥር ቢሮ የ2013 ሪፖርት፤ ፎርጅድ መድሃኒቶች የድሃ አገራት ብቻ ሣይሆን የበለፀጉት አገራትም ፈተና እየሆነ መጥቷል፡፡ በአሜሪካ በ2013 በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻና ቁጥጥር 10 ሚሊዮን የሚደርሱ ተመሳስለው የተሰሩና ለጤና እጅግ አደገኛ የሆኑ መድሃኒቶች ተገኝተዋል፡፡ በተመሣሣይ ሁኔታ በእንግሊዝ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ፣ በአገሪቱ ተመርተው ገበያ ውስጥ ከተሠራጩ መድሃኒቶች መካከል ከ15 ሚሊዮን በላይ ተመሳስለው የተሠሩ ፎርጅድ መድሃኒቶች ተገኝተዋል፡፡
አገራቱ እነዚህን ህገወጥ መድሃኒቶች በመሰብሰብ ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ የእነዚህ አገራት ትልቁ የራስ ምታት ፎርጅድ መድሃኒቶቹ ከሌሎቹ ትክከለኛ መድሃኒቶች ጋር ተቀላቅለው በሰፊው ገበያ ውስጥ መግባታቸውና ህብረተሰቡ መድሃኒቶችን በቀላሉ ለመለየት አለመቻሉ ነው፡፡ አሜሪካና አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገራት ይህንን ችግር ለመቅረፍም በመድሃኒቶች ትዕዛዝና ሽያጭ ላይ ጥብቅ ቁጥጥርን የሚከተል አሠራር ተግባራዊ በማድረግ ህሙማን ከሃኪማቸው የሚታዘዝላቸውን ትክክለኛ መድሃኒቶች ለመግዛት የሚችሉበትን መንገድ አመቻችተዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜም መድሃኒቶቹ በሃኪሞቻቸው በኩል እንዲደርሳቸው የሚደረጉበት አሠራር መኖሩን የፋርማሲ ባለሙያው አቶ ተስፋዬ ታረቀኝ ይገልፃሉ፡፡ ህገወጥ መድሃኒቶች እንኳንስ እንደ እኛ ባሉ ድሃ አገራት ይቅርና በበለፀጉት አገራትም ትልቅ ችግር ሆኖ የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ እኛ ባሉና መድሃኒቶች ከየሱቁና ከየገበያው ላይ እንደ ልብ እየተገዙ ጥቅም ላይ በሚውሉባቸው አገራት ደግሞ ችግሩ የከፋ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
የተለያዩ አይነት መድሃኒቶች ከአደጉት አገራት ወደ ድሃ አገራት ሲገቡ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር እምብዛም አጥጋቢ አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ተመሳስለው በፎርጅድ መንገድ የሚመረቱ መድሃኒቶች እንዲበራከቱና በስፋት ገበያ ውስጥ እንዲሰራጩ አድርጓል፡፡ በዚህ ምክንያትም ህሙማን ከሐኪማቸው በሚታዘዝላቸው መድሃኒት ከበሽታቸው መፈወሳቸው ቀርቶ እጅግ አደገኛ ለሆነ የጤና ችግርና ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ውድ ዋጋ ያላቸውን መድሃኒቶች ገዝቶ መጠቀም ሲያቅት ተመሳስለው የተሠሩ ፎርጅድ መድሃኒቶችን በአነስተኛ ዋጋ እየገዙ መጠቀም የበርካታ ድሃ አገራት ዜጐች ምርጫ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ህሙማኑን ከያዛቸው ህመም ከመፈወስ ይልቅ ለከፋ የጤና ችግርና ለሞት የሚዳርግበት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡
ስለዚህም መንግስት በመድሃኒት ምርትና ከውጪ አገር በማስገባት ሥራ ላይ በተሰማሩ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በመድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ተግባር ላይ የተሰማራው አካል መድሃኒቶች ከውጪ አገር ወደ አገር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት ደህንነታቸውንና ጥራታቸውን በመፈተሽና በማረጋገጥ እንዲገቡ ማድረግ፣ ከገቡም በኋላ በድንገት ከገበያ ውስጥ ናሙናዎችን በመውሰድ ተገቢውን ምርመራና ቁጥጥር ማድረግ የሚቻልበት አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ በበለፀጉት አገራት አቅም ያልተቻለው የፎርጅድ መድሃኒቶች ስርጭት እንደ እኛ ላሉ ድሃ አገራት የብዙ ዜጐችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ችግር መሆኑ አይቀሬ ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንዳመለከተው፤ የፎርጅድ መድሃኒቶች ምርትና ስርጭት አለምን ስጋት ላይ የጣለ አንድ ጉዳይ ሆኖ ሌላው ደግሞ የስም ልዩነት ያላቸው መድሃኒቶችን በህገወጥ መንገድ እያመረቱ ገበያ ላይ የማዋሉ ጉዳይ ነው፡፡
የተለያዩ ስምና መጠሪያ ያላቸውን መድሃኒቶች በህገወጥ መንገድ እያመረቱ የቀድሞው መድሃኒት የአገልግሎት ጊዜውን በማጠናቀቁ ምክንያት ከጥቅም ውጪ እንዲሆን ተደርጐ በአዲስ ምርት ተተክቶ ነው ወይንም ደግሞ የቀድሞው መድሃኒት በርካታ የጐንዮሽ ጉዳቶች ስላሉት ጥቅም ላይ እንዳይውል ተደርጓል እየተባለ ፎርጅድ መድሃኒቶች ገበያ ላይ እንዲውሉ እንደሚደረግም አትቷል፡፡ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍም በመድሃኒት ምርትና ስርጭት ላይ የተሰማሩ አገራትና መድሃኒቶችን ወደ አገራቸው የሚያስገቡ አገራት በመድሃኒት አመራረትና ስርጭት ላይ ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር እንዲደረግ መምከር ከጀመሩ ሠነባብተዋል፡፡
ይህ ጥረት ከተሣካ ፎርጅድ መድሃኒቶች የአሸባሪዎች ቀጣይ መጠቀሚያ ይሆናሉ የሚለውን ሥጋት በእጅጉ ሊቀንስ ይችላል፡፡

Read 3084 times