Monday, 02 March 2015 09:27

“ሽልንጌ!” እና ‘የቻይና ሱሪ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(14 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁማ!
ይቺን የሆነ ቦታ ያነበብኳትን አሪፍ ነገር ስሙኝማ…አውሮፕላን ውስጥ ነው፡፡ አንደኛው; ሰውየው የምንም አይነት ኃይማኖት ተከታይ አይደለም፡፡ ከጎኑ ያለው ሰውዬ ግን የኃይማኖት መጽሐፍ እያነበበ ነበር፡፡ ኃይማኖት የለሹ ሰውዬም…ተንጠራርቶ አየውና ምን ይለዋል…“እሱ ላይ ያሉ ታሪኮችን ሁሉ ታምናለህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡  
ያነብ የነበረው ሰውዬም… “አዎን፣ አምናለሁ፣” አለ፡፡
ያኛውም ቀጠለና… “እሺ፣ ዮናስ እንዴት ነው በአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀን በህይወት ሊቆይ የቻለው?” ሲል ይሞግተዋል፡፡
ሰውየውም… “እኔ አላውቅም፣ ግን መንግሥተ ሰማያት ስገባ ዮናስን እጠይቀዋለሁ” ሲል ይመልሳል፡፡
ኃይማኖት የለሹም በቀላሉ አልቀቀውም፡፡ “ዮናስ መንግሥተ ሰማያት ሳይሆን ገሀነም ቢገባስ?” ይለዋል፡፡
ያነብ የነበረው ሰውዬ ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው… “ገሀነም ከገባማ አንተ ትጠይቀዋለህ፡፡” አሪፍ አይደል!
ገሀነም ከመውረድ ይጠብቃችሁማ!
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ምን ሆነ መሰላችሁ … በዛ ሰሞን የፈረደበት ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ነው፡፡ እናላችሁ… ሴትዮዋ ሦስት ብር ከፍላ ሀምሳ ሳንቲም መልስ ስላልተሰጣት ከረዳቱ ጋር ትጨቃጨቃለች፡፡ ይሄኔ ሾፌሩ… “በቃ አትጨቃጨቅ ስጣት…” ይለዋል፡፡ ከዚያ ትንሽ ቆይቶ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ከእኛ ጋር ለስሙኒና ለሽልንግ ከምትጨቃጨቁ የቻይና ሱሪ ሺህ አምስት መቶ ብር ሲገባ መብታችሁን ለምን አላስከበራችሁም!”
(‘የጨሱ ከተሜዎች’ ቢኖሩ ኖሮ “ኧረ ቼ ጉቬራ!” ክፋቱ ሚኒባስ ውስጥ የነበርነው እንኳን ‘የጨስን ከተሜዎች’ ልንሆን… አለ አይደል… አብዛኞቻችን ከተሜነትን ‘በሚያስደንቅ ፍጥነት’ ወደ አሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን እየመለስነው ያለን ነን፡፡ ቂ...ቂ…ቂ…)
እናላችሁ… የሽልንግ ነገር ብዙ ነገር እያሳሰበን ነው፡፡ በየቦታው “ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡ (ስሙኝማ…አንድ ‘ሽልንጌ’ የምትል አሪፍ አጭር ልብ ወለድ አለች አይደል!)
እናላችሁ…ሽልንጌ የብሶታችን መግለጫ እየሆነች ነው፡፡ “ሽልንጌን!” ስንል ምጽዋት እየጠየቅን ወይም ልብህ/ልብሽ ይራራልን እያልን አይደለም፡፡ የምንጠይቀው ‘የራሳችንን ሽልንግ’ ነው፡፡ የእኛ ያልሆነ ስሙኒና ‘ዲናሬ’ ጨምሩልን አላልንም፡፡ የራሳችንን ሽልንግ ስጡን እያልን ነው፡፡ “ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡ መብታችን ነዋ!
“ሽልንጌን!” ለማለት በቻይና ሱሪ ‘ሪቮሉሽን’ ማስነሳት የለብንም!
በአገልግሎት መስጫ ቦታ ሄደን ቅሬታ ሲኖረን የምንፈልገውን ኃላፊ አናገኝም፡፡  ስሙኝማ…ይሄ እኮ ኃላፊ የማግኘት ነገር ኮሚክ ነው፡፡ አሀ…ኃላፊ ማግኘትና የመንግሥተ ሰማያት ‘ግሪን ካርድ’ ምናምን ማግኘት አይነት ነገር ተመሳሳይ እየሆኑ ነዋ!
እናላችሁ…አንዱን ኃላፊ ለማግኘት እኮ መለማመጥ፣ “እንደው በልጆችሽ ይዤሻለሁ፣ ፍቀጂልኝና ሁለት ደቂቃ ላናግራቸው!” ብለን እጥፍ ዘርጋ ማለት የለብንም፡፡ ኃላፊው እኮ አነስተኛ መንደርን ኮብል ስቶን ለማስነጠፍ ደሞዝ ‘የሚነጨው’ እኛን ለማገልገል ነው፡፡ “የቤንዚን አነሰኝ…”፣ “ውሎ አበሉ አንሷል…” ምናምን እያለ የደብዳቤ መአት የሚያጎርፈው እኛን በማገልገል ስም ነው፡፡ እና ጉዳያችንን ወደ ኃላፊ መውሰድ ‘ሽልንጋችን’ ነው፡፡ መብታችን ነዋ!
“ሽልንጌን!” ለማለት በቻይና ሱሪ ‘ሪቮሉሽን’ ማስነሳት የለብንም!
(ይቺ የኃላፊዎችን ነገር መስመሮች የጨማመርንባት በተገልጋይና በኃላፊዎች መካከል ያለው አጥር… አለ አይደል… ከሰንሰል ወደ እንጨት፣ ከእንጨት ወደ ቆርቆሮ፣ ከቆርቆሮ ወደ ብሎኬት ምናምን እያለ አሁን ጭራሹኑ…ላዩ ላይ ‘አደገኛ አጥር’ የሚል ሊሰቀልበት ምንም ስላልቀረው ነው፡፡ አለቆች ሆይ… ወደ ላይ እየራቃችሁ በሄዳችሁ ቁጥር ታች ያለነው በደንብ ስለማንታያችሁ… አሪፍ አይደለም፡፡ አሀ…ለእናንተ ብዬ ነዋ!)
እናማ…የአለቆች ነገር “ሳይጾሙ ይጸድቃሉ፣ ሳይታመሙ ይጠየቃሉ፣” አይነት እየሆነ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ኃላፊነታቸውን በቅጡ ሳይወጡ ሁሉም ነገር ለእነሱ ብቻ በሚመቻቸው ሲሆን ያው ‘ሳይጾሙ መጽደቅ’ ማለት አይደል! (እግረ መንገዴን… የሆነ ነገር ትዝ አለኝ…‘ኪሲሎጂ’ ለምንድነው ጾም የማይሆነው?…ያው እሱም ሥጋ አይደል እንዴ!)
በየቦታው ለፊርማ ደርሰው እየተጉላሉ ያሉ ሰነዶቻችንን “ኧረ ፈርማችሁ ስጡን!” ስንል “ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡ በየዝግጅቱ “ሰዓት ይከበር አታጉላሉን…” ስንል…አለ አይደል…“ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡
“ውሀ አታቋርጡብን…” “መብራት አታጥፉብን…” “ስልክ አታቋርጡብን…” ስንል… አለ አይደል…“ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡ መብታችን ነዋ!
“ሽልንጌን!” ለማለት በቻይና ሱሪ ‘ሪቮሉሽን’ ማስነሳት የለብንም!
ይቺን ስሙኝማ…ትንሽዬ ልጅ ነው፡፡ የሆነ ሰበካ ያለበት ስፍራ አባቱ ይዞት ሄዶ ልጁ የሚባለው ሁሉ ስላልገባው ስልችት ብሎታል፡፡ ራቅ እንኳን እንዳይል ደግሞ አባቱ እጁን ግጥም አድርጎ ይዞታል፡፡ ታዲያላችሁ…ልጅዬው ቀና ብሎ ሲያይ ከሰባኪው ጐን ብልጭ ድርግም የሚል ቀይ መብራት አለ፡፡ ይሄኔ አባቱን ምን ብሎ ጠየቀው መሰላችሁ… “አባዬ፣ መብራቱ አረንጓዴ ሲሆን መሄድ እንችላለን!”
በብዙ ነገር መብራቱ አረንጓዴ የሚሆንልን መቼ እንደሆነ ይነገረን፡፡
“ሽልንጌን!” ሳንል ሽልንጋችንን የምናገኝበት መቼ እንደሆነ ‘ሮድ ማፑ’ ይነገረንማ!
“ሽልንጌን!” ለማለት በቻይና ሱሪ ‘ሪቮሉሽን’ ማስነሳት የለብንም!
እናላችሁ… የ“ሽልንጌን!” ጉዳይ የሚኒባስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመብት ጉዳይ ነው፡፡ ሚኒባሶችን ከጠቀስን አይቀር ከታሪፍ በላይ እያስከፈሉን ነው፣ ተቆጣጣሪ የለም ወይ!”…ስንል አንድ ሁልጊዜ የምንሰማት ነገር አለች፡፡ “ህዝቡ ራሱ መብቱን ማስከበር አለበት፣” ይባላል፡፡ ነገርዬዋ አሪፍ ብትሆንም አሁን፣ አሁን ከ‘ወርክሾፕ ወረቀት ማሳመሪያነት’ የማታልፍ ነገር እየሆነች ነው፡፡ ልክ ነዋ… ከአንዳንድ ሚኒባስ ሾፌሮችና ረዳቶች የምንሰማቸው ዘለፋዎችና ስድቦች… አይደለም ሽልንጋችንን ኪሳችንን ውስጥ ያለውን ሁሉ ወስደው አፋቸውን በያዙልን የሚያሰኝ ነው፡፡
አሁንማ በአንዳንድ ጥቅሶችም ልክ ልካችንን እየነገሩን ነው፡፡ የምር እኮ ኮሚክ ነው…‘ፍሪ ስፒች’ በደንብ ያለበት ቦታ… አለ አይደል…ሚኒባስ የሆነ ነው የሚመስለው፡፡ በቀደም አንዱ ሚኒባስ ውስጥ ምን የምትል ጽሁፍ ተለጥፋ አየሁ መሰላችሁ… “የዓባይ ተልእኮ ስላለብን እባካችሁ ጠጋ፣ ጠጋ በሉ፡፡” እናላችሁ… “ነገ ደግሞ ምን ተብሎ ይጻፍ ይሆን!” የሚያሰኝ ነው፡፡
(ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ስላለኝ ነው… ሚኒባስ ውስጥ አንዱ ተሳፋሪ እንደው እንደ ‘ቦተሊካ’ የሚመስል ነገር ሲናገር የሌሎች ተሳፋሪዎችን ገጽታ አይታችሁልኛል! አለ አይደል…“ምን ያህል ቢከፋው ነው…” አይነት ሳይሆን… “ሂድና የሞንጎሊያ ቱሪስት ብላ!” አይነት ነገር ነው፡፡)
እናማ… በሚኒባስ ብቻ ሳይሆን በብዙ ነገሮች “ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡
“ሽልንጌን!” ለማለት በቻይና ሱሪ ‘ሪቮሉሽን’ ማስነሳት የለብንም! መብታችን ነዋ!
እንደገና እንኳን ለአድዋ የድል በዓል በሰላም አደረሳችሁማ፡፡ ሬይሞንድ ጆናስ የተባለ ጸሀፊ ‘The Battle of Adwa, African Victory in the Age of Empire’ በሚለው መጽሐፉ፤ እ.ኤ.አ. ‘በ1898 አሜሪካ ስፓኒሾችን ስታሸንፍና እ.ኤ.አ. በ1905 ሩስያ በጃፓኖች ስትሸነፍ፣ ስለ ግዛት ማስፋፋት ቀደም ብለው እንደ እውነታ ሲወሰዱ የነበሩ አመለካከቶችን ያናጉ ክስተቶች ናቸው ተብሎ ይወሰዳሉ፣’ የሚል ስሜት ያለው ነገር ጽፏል፡፡ ይኸው ጸሀፊ መጽሐፉን የዘጋበትን የመጨረሻ ዓረፍተ ነገር አንብቡልኝማ፡፡ (ዘንድሮ በዚቹ በእኛዋ አገር የ‘እንግሊዝ አፍ’… አለ አይደል… “እንደ ፈቺው…” ሆኗልና እንደ አፈታታችሁ ፍቷትማ! ቂ…ቂ…ቂ…)
“The signal moment for our times, the event that reopened previously settled questions for a new century, occurred not in 1905 or even in 1898. It took place in 1896 at a place called Adwa.”
የአድዋ ድል እንዲህ ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3207 times