Monday, 02 March 2015 09:15

አሁን ገና ዕድገት መኖሩ ተገለጠልኝ!

Written by  ኢዮብ ምህረተአብ
Rate this item
(12 votes)

(እውነት አንድ)
ኮንዶሚንየም ደረሰኝ
ባለ ሶስት መኝታ ቤት ሰሚት አካባቢ ዕጣ ወጣልኝ፡፡ ቻው ድህነት፣ ቻው መንገላታት፡፡ አሁኑኑ በጂፕሰም አሰማምሬ አከራየዋለሁ፣ በደህና ዋጋ፡፡ ደሞ ሰፈሩ ፀዴ ሰፈር ነው፣ ባቡርም እየገባበት ነው…..
መንግስት ዘንድሮ ከምር ጸደቀብኝ፣ ይመቸው፣ ባሁኑ ምርጫ እመርጣቸዋለሁ፤ ኧረ ለዘላም ይኑሩ!! ያ ቀውጢ ደጋፊ ጀለሴ እኮ የሚናገረው እውነቱን ነው…… ምን ነበር ያለኝ? “…የኛ አገር ተቃዋሚ ማለት ምቀኛ፣ ጨለምተኛና ዘረኛ ነው፡፡ ከላይ ነው አንድነት ምናምን የሚሉት፤ ሲፎግሩ ነው……ሁሉ ነገር ላይ ሲያማርሩ ሲነጫነጩ ይደብራሉ…የቦሌ መንገድ ሲሰራ፣ ባቡር ሲሰራ --- ትራፊክ ጭንቅንቅ በዛ፣ ኡኡ.. ይላሉ…. ባህላቸው ነው፡፡ ትልልቅ የመብራት ፕሮጀክቶች እንዳልተመረቁ ሁሉ መብራት ሲጠፋ ያብዳሉ…” (አሪፍ አንግሊዝኛ ሁላ ተጠቅሟል፡ ‘form እንጂ substance የላቸውም፤ ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ ሲሉ ለይስሙላ ነው፣ ባለፈው የታሪክ ጠባሳችን ምክኒያት ኢትዮጵያዊነት እንዳይሰማቸው የተደረጉ ብዙሃን ህዝቦችንና ብሄረሰቦችን ሆነ ብለው ረስተው ነው፣ በአፋቸው የሚያወሩት ሌላ በተግባራቸው ደግሞ ትምህክተኛና ናቂዎች ናቸው…ይሄ የCentrists መገለጫ ነው…በባዶ ኡኡ ማለትና ማስመሰል ነው እሚወዱት’)
እውነቱን ነው…. ያምሃል እንዴ? ቤት ሰጠኝ እኮ ጸሀዩ መንግስታችን፣ ምን እፈልጋለሁ ሌላ!?... የእድገት ውጤት እኮ ነው፡፡ አዳሜ በየሰበብ አስባቡ ከጎረቤት ጋር እንዳልተጨቃጨቀች ዛሬ አኗኗሯ ተለወጠ፣  ተሻሻለ፡፡ አሁን እንደው ምቀኛ ካልሆንክ “አላደግንም” ብለህ ትገግማለህ?……ሰዉ ጨለምተኛ ነው …አሁን ኢቢሲ ስለ ልማት እና ስለ እድገት ስላወራ ይጠምዱታል፣ …እውነት ስለተናገረ እኮ ነው፣ ሌላ ምንም አይደለም….እኔ ‘ኮ ግርም የሚለኝ በደርግ ጊዜ ወጣት ተገድሎ ለጥይት እንዳልተከፈለ፣ እሱን ሙልጭ አድርገው ክደው ‘የማውራት ነጻነት አሁኑኑ!’ ይላሉ፡፡ ተቃዋሚዎች… ይሄ ክህደት ነው፤ ክፋት እና ጨለምተኝነት እኮ ነው፤ ሌላ ምንም የለም….
በጎ አለመመኘት እኮ በሽታ ነው፣ ስለ ምንም ነገር በጎ አለማውራት እኮ የአእምሮ ችግር ነው፡፡ ለውጥ የለም፣ መሻሻል የለም ብሎ መገገም ክፋት ነው፡፡ አባይ ግድብ ላይ ማሾመር፣ ማጣጣል ክፋት ነው፡፡ አለም የመሰከረለትን የትምህርትና የጤና ሽፋንን እንዳላዩ ማለፍ በገበሬ ቤተሰብ ላይ ማላገጥ ነው፣ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ ቢያንስ አለም ያመነውን  እድገት መካድ፣ ያለውን መሻሻል እንዳላዩ ሆኖ በትናንሽ ስህተቶች መጮህ ክፋት ነው፡፡ ለማንኛውም ኮንዶሚኒየም ደርሶኛል፡፡
መንግስት ይመቸው፤ ለዘላለም ይኑር!
(እውነት ሁለት)
ኮንዶሚንየም አልደረሰኝም
ስፎግራችሁ ነው፣ ኮንዶሚኒየም አልደረሰኝም- ወፍ የለም፡፡ ዕጣውን አፍጥጬ ሰባቴ ሸመደድኩት፣ የለም፤ በቃ የለም፣ ዕድሌ ነው፡፡
ቆጨኝ፣ ከምር ቆጨኝ ያ ጉዳይ ገዳይ እኮ ነግሮኝ ነበር፣ አላምን ብዬ ነው….ለነገሩ ያረጋል አይሸሹም ጋማ ከተባለበት ቢዝነስ (ሙስና) አንዱ ‘ባለ አንድ መኝታ ኮንዶሚኒየም በስሙ አለው፣ ከየት አመጣው?’ ተብሎ ነው (ልክ ድንገት ያወቁበት አስመሰሉት)……እና አሁንስ እጣው እንዳልታፈነ ምን guarantee አለኝ? ምንም…..መንግስት አሁንስ አበዛው፣ ከምር አዝግ ነገር ሆነ! እምልህ የማማረር ሙድ ለማራመድ ሳይሆን ግራ ሆኖብኝ ነው፡፡ መብራት ጠፋ፣ ወይንም እኛ ሰፈር ውሃ ከጠፋ 2 ወር አለፈው ብዬ እሪሪሪ አልልም፡፡ ግን አለ አይደል፣ ዜና ላይ ዝም ብሎ ሰበብና አባባል መዘብዘብ ይመራል፡፡ በዝቶ የሸመደድከው ሰበብ፡
“መብራት የሚጠፋው ትራንስፎርመሩ ከአቅሙ በላይ ስለሆነ ነው”
“ሞባይል የማይሰራው ኔትዎርኩ የZTE ስላልሆነ ነው”
“ዘይት የጠፋው አንዳንድ ሃላፊነት የማይሰማቸው የመሃከለኛው መደብ አመራር አባላት የአመለካከት ጥራት ስለጎደላቸውና እና ካንዳንድ ደላላዎች ጋር ተገቢ ያልሆነ የNetwork ሠንሠለት ስለፈጠሩ ነው፡፡”
እና ምንድነው መላው?
 “….ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየጣርኩኝ ነው….” (አባባሉ ሲሰበሰብ ይኸው ነው)
….ያ ተቃዋሚው ጀለሴ ለካ እውነቱን ነው፡፡ “ዘንድሮም ደርግ ሲሉ ሼም የላቸውም፤ 20 አመት አለፈ እኮ ደርግ ከጫረ…አለም ተገለባብጦ ተቀይሯል እኮ፡፡ …ቆይ አሁን…. ‘ጫማ የለኝም ብለህ አትጨናነቅ እግር የሌለው አለና’ ብሎ ፍልስፍና ምንድን ነው?….ልማት ማለት ምን ማለት ነው?….‘ቡናኔ ወረዳ ውስጥ የህዝብ ሽንት ቤት ተመረቀ’ የሚልን ዜና ምን ትለዋለህ?......ኢቢሲ ሙድ እየያዘብን ነው እንዴ? ለመሆኑስ እስከ ዛሬ የት ነበሩ ? ሁሉ ነገር ከተጀመረ እኮ ቢበዛ 6 አመት ቢሆነው ነው…
 አደግን አላደግን አይደለም እኮ ዋናው ጉዳይ፡፡ እድገቱን እነ ማን ጠርንፈው ወሰዱት ነው ጥያቄው……ግልጽ እኮ ነው…፡፡ 100 ገበሬ ሚሊየነር ሆነ ተባለ፤ እውነት ብለን እንውሰደው፣ ግን ደግሞ 10 ሚሊዮን ገበሬና ልጆቹ ደግሞ የፈረንጅ ስንዴ ይረዳሉ፣ዘንድሮም ማለት ነው፣ እና አስረዳኛ ለውጡን…፡፡ ገበሬውስ ወይ ስንዴ ይረዳል፣ ወይንም በSaftey Net ይታቀፋል…የከተማ ድሃውስ….የአስኮ መንገድ አለቀ አላለቀ ለእትዬ ሽታዬ ምኗ ነው?! በቆሎ በኪሎ አንድ ብር ቢቀንስ ግን ተመስጌን ትላለች….ከተማ እየኖርክ በዚህ ኑሮ ውድነት መውለድ እኮ ትልቅ crime ነው፣ ባንተም ላይ በልጅህም ላይ….. ግፍ እንደሰራህ ቁጠረው…
(ቀጠለ ጀለሴ) “……ትልቁ ችግራቸው እኮ አይሰሙም፤ ማንንም፡፡ ጥሩም ሰርተው ንግግር  አይችሉበትም፤ ሰው አያማክሩም፡፡ አሁን በቀደም እኛ ሰፈር እነ ፋዘርን ጠርተው ‘የመለስን ራዕይ ለማሳካት ምን ማድረግ አለብን?’ ብለው  ውይይት አካሄዱ፡፡ ፋዘር ማታ ላይ ‘ኧረ እነዚህ ሰዎች ምን ሁነው ነው እሚያላግጡት?’ ብሎ ሲያብድ አመሸ፡፡ እሱ ደግሞ ታውቀዋለህ መለስን ይወደዋል፣ ያከብረዋል፡፡ ግን እንዲህ የሰፈር ወረኛ እና ካድሬ በመለስ ስም ሲያላግጥ ይሸማቀቃል፡፡ ታ’ቃለህ እስታሊን፤ “ሌኒን እንዳለው--” እያለ ነው አንቀጥቅጦ ሶቪየትን የመራት… አሁኑም ሙዱ ያው ነው…”
(አሁንም ቀጠለ) “ሰዉ የመናገር ነጻነት ሲል ያስቀኛል፣ ይገርመኛል…እኔ ግን ‘ምመርጠው፣ ‘ያለ ማሰብ፣ ሌላውን አለም ያለማየት፣ የመደደብ መብት ይከበር’ ነው ‘ምለው-- ከምሬ እኮ ነው…ባታይ፣ ባታስብ፣ ባታወዳድር፣ ባ’ታቅ እኮ አትናደድም፣ ኡኡ አትልም፡፡ ጸረ ሙስና ምናምን ሲባል ያስቀኛል…..አሁን የት የት እና እንዴት እንደሚጨረብ ለማወቅ እኮ እድሜ ነው እሚፈልገው፤ ከ18 አመት በላይ ከሆንክ በቂ ነው፡፡ ምን ድብቅ ሚስጥር አለ?...”
“…አበሻ ደግሞ ቀበሮ ነው፤ እያወቀ እንዳላወቀ ያጨበጭብልሃል፣ ልቡን አታውቀውም፣ እንኳን ለመንግስት ለሚስቱም የልቡን አያወራም፤ ላሽ ነው እሚልህ….. ልክ ስትፈርጥ ‘እኔም ብዬ ነበር’ ይልሀል፤ ከዚያ ወዲያው ይረሳሃል..ሙሰኛ ተብለህ ብትታሰር፣ሽብርተኛ ተብለህ ብትታሰር፣ብትፈታ፣ ካገር ብትለቅ፣ ብትመለስ፣ብትሾም፣…ዝም ነው ሚልህ…. እንዳላየ ኳስና ድራማ ያሳድዳል…ነገ መንግስት ቢወድቅ፣ ሰዎቹን ጊዜ ቢጥላቸውም ያው ነው…ሁለት ሳምንት ያወራና ይረሳዋል…እኔ ግን እፈራለሁ፡፡
አንዳንዴ የእነሱም ነገር ደስ አይለኝም--- ከኛ በላይ ላሳር አይነት ነገር ነው!
(እውነት ሶስት)
እውነት  ምንድነው?

Read 5361 times