Monday, 02 March 2015 09:09

ፓርቲዎች የመጀመሪያ ክርክራቸውን በዩኒቨርሲቲ ያካሂዳሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

ኢህአዴግ፣ ኢዴፓና መድረክ ርዕዮተ ዓለማቸውን ያቀርባሉ

      ዛሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ቤት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ  ኢህአዴግ፣ መድረክ እና ኢዴፓ በርዕዮተ ዓለማቸው ላይ መነሻ ፅሁፍ በማቅረብ ይከራከራሉ፡
ከሁለት ወር በኋላ ለሚካሄደው የግንቦቱ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው የፓርቲዎች ክርክር ላይ ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲን፣ ኢዴፓ የሊበራል ዲሞክራሲን እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የሶሻል ዲሞክራሲን ፅንሰ ሃሳቦችና መርሆዎች የተመለከቱ ፅሁፎች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ት/ቤት ዲን ዶ/ር አብዲሣ ዘርአይ፤ ሶስቱ የፖለቲካ ርዕዮተ አለሞች ለክርክር የተመረጡት አብዛኞቹ የሀገራችን ፓርቲዎች የእነዚህ ርዕዮተ ዓለም አራማጅ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
በዛሬው ክርክር በሊበራል ዲሞክራሲ ላይ መነሻ ሃሣብ እንዲያቀርቡ የተጋበዙት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ እንዲህ ያሉ የሃሣብ ማንሸራሸሪያ መድረኮች የፓርቲዎችን የፖለቲካ አማራጭ ለህዝብ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ፓርቲያቸው የሚከተለውን የሊበራል ዲሞክራሲ ርዕዮተ አለም ከኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድምታው አንፃር ለማብራራት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ምህዳር ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ቢኖርም ያገኙትን ራስን የማስተዋወቂያ አማራጭ ሁሉ አሟጠው መጠቀም ይገባቸዋል ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ ኢዴፓም አማራጭ ሃሣቦቹን ለህዝብ ለማድረስ ያገኛቸውን ዕድሎች በሙሉ ይጠቀማል ብለዋል፡፡
መድረክን ወክለው የሶሻል ዲሞክራሲን ርዕዮተ አለም በተመለከተ የመነሻ ሃሣብ የሚያቀርቡት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ እንዲህ አይነቱ መድረክ መዘጋጀቱ ለፓርቲዎች ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው በክርክር መድረኩ ላይ የሶሻል ዲሞክራሲ መርሆዎችን እንደሚያቀርቡና ከክርክሩ መልካም ነገር ይገኝበታል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
የኢህአዴግ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ደስታ ተስፋሁ በሰጡት አስተያየት፤ መራጩ ህዝብ በፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ እንዲረዳ መሰል መድረኮች አስፈላጊ መሆናቸው ገልጸዋል፡፡
በክርክሩ ላይ በተጋባዥነት ከተጠሩት ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ሠማያዊ ፓርቲ በርዕዮተ አለም ላይ ክርክር ከመደረጉ በፊት ምርጫው የሚካሄድበት ምህዳር መስፋት አለበት ብሏል፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ “በዚህ ሰአት መነጋገር የነበረብን የመድብለ ፓርቲ ስርአት አደጋ እየተጋረጠበት ስለመሆኑና የፖለቲካ ምህዳሩ ስለመጥበቡ እንዲሁም በፀረ ሽብር ህጉ ላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

Read 3954 times