Monday, 02 March 2015 08:56

ሜታ ቢራ የማምረት አቅሙን በሶስት እጥፍ ማሳደጉን ገለጸ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ከ2 ቢ. ብር በላይ ፈጅቷል
 ፋብሪካዎቹ በአገር ውስጥ ገበያ መገደብ የለባቸውም ተባለ

የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰራው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሰሞኑን የተመረቀ ሲሆን ማስፋፊያው የፋብሪካውን የማምረት አቅም በሶስት እጥፍ እንደሚያሳድገው ተገለጸ፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት በ225 ሚሊዮን ዶላር ዲያጆ ለተባለ የፈረንሳይ ኩባንያ የተሸጠው  የሜታ አቦ ቦራ ፋብሪካ ከትናንት በስቲያ ያስመረቀው አዲሱ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በዓመት 550 ሺ ሄክቶ ሊትር የነበረውን የፋብሪካውን የማምረት አቅም ወደ 1.7 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ከፍ ያደርገዋል ተብሏል፡፡  
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢንፎርሜሽንና መገናኛ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የተመረቀው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትሩ ዶክተር መብራቱ መለስ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤አገሪቱ በምትከተለው ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋትና የግብርና ኢንዱስትሪን የማስተሳሰር ተግባር ላይ ፋብሪካው ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የኢንፎርሜሽንና መገናኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ ፋብሪካው የተማረውን የሰው ኃይልና በግብርና ስራ ላይ የተሰማራውን ዜጋ በእኩል አገጣጥሞ የስራ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመው በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ሰዎችን ከማሰማራቱም  በላይ ለአርሶ አደሩም ገበያ እንደፈጠረለት ተናግረዋል፡፡  
መንግስት ለፋብሪካ ግብአታቸው የግብርና ውጤቶችን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ እያበረታታና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤በሂደት እየታየ ማበረታቻውና ድጋፉ ሊቀነስና ሊቀር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ የቢራ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን በአገር ውስጥ ብቻ በመሸጥ ተገድበው መቅረት የለባቸውም ያሉት ሚኒስትሩ፤ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ አገር እንዲልኩ ግፊት ይደረጋል ብለዋል፡፡ አብዛኞቹ ቢራ አምራቾች በአገር ውስጥ በቂ ገበያ ስላላቸው ወደ ውጪ መላክ አይፈልጉ ይሆናል፤ነገር ግን ሁኔታው በዚህ መልኩ መቀጠል አይገባውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡  
“ከቢራ በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ አምራች ኩባንያዎች ወደ አገራችን እንዲመጡ እንፈልጋለን፡፡ እነሱን ማበረታታትና መደገፍ በጣም ያስፈልገናል፡፡ በቢራ ምርቶች ላይ ያለውን ጉዳይ ቀስ እያልን ጊዜ ወስደን ማየት ይገባናል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ በቂ ነው ብለን ለማቆም ባንችልም የተወሰኑ አማራጮችን ስናገኝ ድጋፍና ማበረታቻዎቹን እየቀነስን እንሄዳለን” በማለት አስረድተዋል፡፡ በቢራ ምርት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ኩባንያዎች እንዳሉ የጠቆሙት ዶ/ር ደብረፅዮን፤ እነሱም ገፍተው ሲመጡ የምናየው ይሆናል ብለዋል፡
የግማሽ ክ/ዘመን እድሜ ያስቆጠረው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ፣ በ1959 ዓ.ም ተመስርቶ ሥራ ሲጀምር በዓመት 50ሺ ሄክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም የነበረው ሲሆን በቅርቡ ማልታ ጂኒየስና ዘመን ቢራ የተባሉ  አዳዲስ ምርቶቹን ለገበያ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡  

Read 2984 times