Saturday, 21 February 2015 14:05

የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች ከባንኮች 1 ቢሊዮን ዶላር ዘረፉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በታሪክ ከፍተኛው ዝርፊያ ነው ተብሏል

የሩስያ፣ ዩክሬን፣ቻይና እና የአውሮፓ አገራት ዜግነት ያላቸው የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች በተለያዩ የአለም አገራት በሚገኙ ከ100 በላይ ባንኮች ላይ በፈጸሙት ስርቆት በድምሩ 1 ቢሊዮን ዶላር መዝረፋቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ በኢንተርኔት ከተፈጸሙ መሰል የባንክ ዝርፊያዎች ከፍተኛው ገንዘብ የተሰረቀበት ነው የተባለው ይህ ዘረፋ፣ አጭበርባሪዎቹ በባንኮቹ ኮምፒውተሮች ላይ በጫኗቸው መረጃን የሚሰርቁ ሶፍትዌሮች አማካይነት የተከናወነ ሲሆን፣ በባንኮቹ ውስጥ የነበረው ገንዘብ አጭበርባሪዎቹ ወደከፈቱት የሃሰት አካውንት እንዲዘዋወር ተደርጓል፡፡
ካስፔርስኪ የተባለውን አለማቀፍ የኢንተርኔት ደህንነት ተቋም ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ አጭበርባሪዎቹ ከእያንዳንዱ ባንክ ከ2.5 ሚሊዮን እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር ዘርፈዋል፡፡ እስከዛሬ ከተከናወኑት የባንክ ዘረፋዎች ሁሉ ፍጹም ውጤታማ እንደሆነ በተነገረለት በዚህ የኢንተርኔት ማጭበርበር ተግባር ሰለባ  የሆኑት ባንኮች ስም በይፋ ባይገለጽም፣ ባንኮቹ አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ 25 የአለማችን አገራት ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ዝርፊያው አሁንም እንደቀጠለ የጠቆመው ኩባንያው፣ ባንኮች የኮምፒውተር ሲስተሞቻቸው በዚህ የአጭበርባሪዎች ሶፍትዌር እንዳልተጠቁ ማረጋገጥና አስፈላጊውን ፍተሻና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል ብሏል፡፡

Read 3500 times