Saturday, 21 February 2015 13:18

ድንገተኛው ሞት (Heart Attack)

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 ለዓመታት የዘለቀውን ድብቅ ፍቅራቸውን ይፋ አውጥተው ሶስት ጉልቻ የሚመሰርቱባትን ቀን ሁለቱም በጉጉት ሲጠባበቋት ቆይተዋል፡፡ ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ ላይ የዓለም ይሁን ተብለው ሊዳሩ ደፋ ቀናውን ከርመውበታል፡፡ የሰርግ ድግሱን የሁለቱም ወጣቶች ቤተሰቦች ተያይዘውታል፡፡ የሰርግ አዳራሽና ዲኮሩ፣ የመኪና ኪራዩ፣ የቬሎና የፀጉር ሥራ ዝግጅቱ ሁሉ ተጠናቋል፡፡ “ለህፃናት ቦታ የለንም” የሚለው የሰርግ መጥሪያ ካርድም ታድሎ አልቋል፡፡ ሙሽራውና ሙሽራዋ ከሚዜዎቻቸው ጋር የሰርግ ዝግጅቱን አስመልክቶ ውይይት ለማድረግ እየተሰባሰቡ ማምሸት ከጀመሩም ሰነባብተዋል። ሁለቱ ሙሽሮች በሚዜዎቻቸው ታጅበው አንድነታቸውን የሚያበስሩባት ቀን ደርሳለች፡፡
ከሰርጉ ዕለት ሶስት ቀናት በፊት ግን ያልታሰበ አደጋ ተከሰተ፡፡ የሁለቱን ሙሽሮች ህልምና ምኞት ያጨለመ፣ ቤተሰቦቻቸውንና ዘመድ አዝማድን ሁሉ በእጅጉ ያሳዘነ ነበር፡፡ ዕለተ ሐሙስ ምሽት ሙሽራውና ሙሽራዋ ከሚዜዎቻቸው ጋር ስለሰርጉ ዝግጅት የመጨረሻ ውይይታቸውን ለማድረግ ተገናኙ፡፡ ለሁለት ሰዓታት የቆየው ውይይታቸው ሲጠናቀቅ ሙሽራው፣ ሙሽሪትንና ሁለት ሚዜዎቿን ሃያት ኮንደሚኒየም አካባቢ ወደሚገኘው ቤቷ ሊያደርሳት ጉዞ ተጀመረ፡፡ መንገዱ በትራፊክ ተጨናንቋል። ሙሽራው መኪናውን እያሽከረከረ አልፎ አልፎ ደረቱ ላይ በግራ ጐኑ በኩል የሚሰማውን ውጋቱ ስሜት ያዳምጣል፡፡ ውጋቱ ቀኑን ሙሉ ሲሰማው አንደዋለና ብርድ ሳይመታው እንዳልቀረ ለሙሽራዋ ነገራት፡፡ ሳሚት አደባባዩን እንደዞሩ የተጨናነቀው መንገድ ቀለል እያለ ሄደ፡፡ ሙሽራዋ ከሚዜዎቿ ጋር ጨዋታ ይዛለች፡፡ መኪናቸው ድንገት አቅጣጫዋን ስታ ስትወላውል ሁሉም ግራ በተጋባ ስሜት ወደ ሙሽራው አፈጠጡ፡፡ ሙሽራው የመኪናው መሪ ላይ በግንባሩ ተደፍቷል፡፡ ዘዋሪ ያጣችው ተሽከርካሪ ወዲህና ወዲያ እየተላጋች ሄዳ፣ ከአዲሱ የባቡር ሐዲድ ግንብ ጋር ተላትማ ቆመች፡፡ ተሣፋሪዎቹ እሪታቸውን አቀለጡት፡፡ ሥፍራው በአንድ አፍታ በግርግርና ትርምስ ተሞላ፡፡ ከምሽቱ 3 ሰዓት ከሃያ ነበር፡፡ በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶችና መንገደኞች መሪው ላይ በግንባሩ የተደፋውን ወጣት እንደምንም ተሸክመው አወጡት፡፡
በሌላ መንገደኛ መኪና ወደ ሆስፒታል ይዘውት በረሩ፡፡ ህይወቱን ለማትረፍ ግን እጅግ ዘግይተው ነበር፡፡ በሆስፒታሉ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ወጣቱ ድንገተኛ የልብ ህመም ችግር እንደገጠመው ተረድተው፣ ገና የህክምና እርዳታ ለማድረግ ሲዘጋጁ ህይወቱ አለፈች፡፡
የ34 አመቱ ወጣት ከነብዙ ህልምና ተስፋው ይህችን ዓለም ተሰናበታት፡፡ ሐዘን ልቧን የሰበረው ወጣቷ ሙሽራ የደረሰባትን እጅግ አስከፊ ሐዘን የምትገልጽበት ቃላት የላትም፡፡ የምትወደውንና ነገ የቤቴ አባወራ፣ የምወልደው ልጅ አባት ይሆናል ብላ የምትጠብቀውን ሙሽራዋን በድንገት ተነጥቃ የሁለት ወራት ፅንስ በሆዷ እንደተሸከመች ብቻዋን ቀርታለች፡፡ ሃያት ኮንዶሚኒየም ከሚገኘው የወጣቷ ሙሽሪት ቤት ለቅሶ ደርሼ ስወጣ እንደ ደራሽ ውሃ ድንገት መጥቶ ስለሚወስደው ድንገተኛ የልብ ህመም (Heart Attack) ባለሙያ አነጋግሬ ለአንባቢያን መረጃ ለመስጠት ወሰንኩ፡፡ ለመሆኑ ድንገተኛ የልብ ህመም ምንድነው? መነሻውስ? ችግሩ ሲያጋጥም የሚወሰድ አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ ይኖር ይሆን?
በደም መተላለፊያ ቧንቧዎች ውስጥ አዝጋሚ በሆነ መንገድ የሚፈጠር ቁስለትና እሱን ተከትሎ በሚመጣ የደም ቧንቧዎች ጥበት ምክንያት የደም ቧንቧዎቹ ደም የማመላለስ አቅማቸው ሲዳከም ወይንም ሙሉ በሙሉ ደም ማመላለሳቸውን ሲያቋርጡ ድንገተኛ የልብ ህመም ይከሰታል፡፡
ቁስለቱ ከፍተኛ በሚሆንበት ጊዜ የደም ቧንቧው ሊቆረጥ ወይንም ሙሉ በሙሉ ሊዘጋ ይችላል፡፡ ይሄኔ የልብ ጡንቻዎች ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ያቆማሉ፡፡  ድንገተኛ የልብ ህመም (Heart attack) የሚባለውንም ያስከትላል፡፡
በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሐኪም የሆኑት ዶክተር አብርሃም ተስፋዬ፤ ድንገተኛ የልብ ህመም (Heart Attack) የሚባለው በሽታ በአብዛኛው በወጣትነትና በጐልማሣነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶችን እንደሚያጠቃም ይናገራሉ፡፡ ለችግሩ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የስኳር ህመም፣ ደም ግፊት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት፣ የአልኮል ሱሰኝነትና የዕድሜ መግፋት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡
“አኪዌት ኮርናሪ ሲንድሮም (በልብ ቧንቧ ጥበት ሳቢያ የሚከሰት ድንገተኛና አጣዳፊ ህመም) በተለይ በአደጉ አገራትና በከተሞች አካባቢ ጐልቶ ይታያል። ለዚህም ምክንያቱ ችግሩ ምቾት ከተላበሰ አኗኗር፣ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግና የተስተካከለ የአመጋገብ ሥርዓት አለመኖር ጋር ተያይዞ እየጨመረ ስለሚሄድና ሁኔታው በአደጉት አገራትና በተለይም በከተሞች አካባቢ በስፋት ስለሚታይ ነው” ብለዋል። ድንገተኛ የልብ ህመም በአገራችንም እየተበራከተ መምጣቱን የጠቆሙት ዶ/ር አብርሃም፤ ችግሩ ባለፉት ጥቂት አመታት እየጨመረ ከመሄዱም በላይ በአብዛኛው በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የችግሩ ተጠቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
“በየጊዜው የጤና ምርመራ ማድረግና ራስን ማወቅ፣ በእኛ አገር ህብረተሰብ ዘንድ የተለመደ ነገር ባለመሆኑ በአብዛኛው ችግሮች ተባብሰውና መዳን በማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው መታወቃቸው የችግሩ ሰለባዎች መዳን እየቻሉ እንዲሞቱ እያደረጋቸው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የደም ግፊት ያለበት ሰው በሽታው እንዳለበት ቀደም ብሎ ቢያውቅና አስፈላጊውን ህክምናና ጥንቃቄ ቢያደርግ በደም ግፊት ሣቢያ ሊከሰት ከሚችለው ድንገተኛ የልብ ህመም (Heart Attack) እና እሱን ተከትሎ ከሚመጣው ድንገተኛ ሞት ሊድን ይችላል ያሉት ዶክተሩ፤ በቀላል ወጪና ያለ ችግር ያለንበትን የጤና ሁኔታ ለማወቅ የምንችልባቸው መንገዶች ስለሚኖሩ ሁላችንም ልንጠነቀቅ ይገባል ብለዋል፡፡
ድንገተኛ የልብ ህመም መነሻ ምክንያቱ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በደም ቧንቧዎች ውስጥ በሚፈጠር ቁስለት ሣቢያ የደም ቧንቧዎች ሲጠቡና በውስጣቸው ደም እንደልብ ማስተላለፍ ሲያቅተው ቢሆንም በደም ቧንቧዎች ውስጥ ቁስለት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ነገሮች እነዚህ ናቸው ተብለው ሊገለፁ አይችሉም፡፡ ይሁን እንጂ የደም ግፊት፣ ስኳር፣ ያልተስተካከለ የሰውነት ክብደት ያለባቸውና አብዛኛውን ጊዜ በውጥረትና ጭንቀት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች  ለድንገተኛ የልብ ህመም የተጋለጡ ናቸው፡፡
ድንገተኛ የልብ ህመም እንደስሙ ሁሉ በድንገት የሚከሰትና በአጣዳፊ ሁኔታ ለሞት የሚዳርግ ቢሆንም ችግሩ ከመከሰቱ ከሰዓታት አንዳንድ ጊዜም ከቀናት በፊት ምልክቶችን ሊያሣይ ይችላል። በአብዛኛው የተለመደው የድንገተኛ የልብ ህመም ምልክት:- በደረት ላይ በተለይም በግራው የደረታችን ክፍል ተደጋጋሚ የውጋት ስሜት መከሰት፣ ትንፋሽ ማጠርና ማላብ… ጥቂቶቹ ናቸው። አንድ ሰው ድንገተኛ የልብ ህመም ሲገጥመው በፍጥነት ህክምና ካላገኘ በህይወት የመቆየት ዕድሉ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በተለይም ችግሩ የገጠመው ሰው በእንቅልፍ ላይ እያለ ወይም ተቀምጦ ከሆነ ችግሩ እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቋሚ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ ሰው በደቂቃዎች ጊዜ ውስጥ ህክምና ማግኘት ካልቻለ ህይወቱን የሚያጣበት ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡ ድንገተኛ የልብ ህመም ሁላችንም ልንጠነቀቀው የሚገባ አደገኛ በሽታ እንደሆነም ዶክተር አብርሃ አሳስበዋል፡፡      

Read 8272 times