Saturday, 21 February 2015 12:53

“የሚያባርረኝ ጣሊያን እንቅፋት መቶት በሞተ ጀግና ነህ ብለው አሠሩኝ እንጂ እኔስ ዓርበኛ አይደለሁም!” ዓርበኛው ደምበል (እናት ዓለም ጠኑ)

Written by 
Rate this item
(12 votes)

      ከዕለታት አንድ ቀን ጦርነት አለ ተብሎ ጐበዝ ሁሉ ክተት ሠራዊት ተባለና ዝግጅት ተጀመረ፡፡
ከአንድ መንደር ወደጦርነቱ የሚሄድ ጐበዝ ሚስቱ ነብሰጡር ነበረችና፤
“ድንገት ጦርነቱ ረዥም ጊዜ ከፈጀ፣ አሊያም አንዳች አደጋ ከገጠመኝ የልጄን ነገር አደራ” ብሏት ተሰናብቶ ወጣ፡፡
ጦርነቱ ከሁለት ዓመት በላይ ፈጀ፡፡ ያ ጀግናም በሰላም ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡
እንደደረሰ “ደህና ከረማችሁ?” አለ፡፡
“ደህና ነህ? እንኳን ደህና መጣህ የኔ ጌታ!” አለች ባለቤቱ፡፡
“ብዙ ሰው ተጐዳባችሁ?”
“ብዙም አይደል፡፡ እኛ ደህና ቦታ ላይ መሽገን ስለነበር ለጠላት አልተመቸንም ነበር፡፡”
ባለቤቱ ወደ ጓዳ ጉድ ጉድ ማለቷን ቀጠለች፡፡
ባልየው አንድ ነገር ግር ብሎታል፡፡ ምንም ዓይነት የህፃን ልጅ ድምፅ አይሰማውም፡፡
“ልጄ የት አለ?” “፣ “ምን ሆነ?” “ወደ እናቴ ልካው ሊሆን ይችላል?” ብዙ ጥያቄዎች ተመላለሱበት፡፡
ሚስቲቱ ምግብ ሠርታ በሉ፡፡ የሚጠጣም ተጠጣና ባል ወደማይቀረው ጥያቄ ሄደ፡፡
“የልጄ ነገር ምን ሆነ?” አለ፡፡
“ልጃችን መወለዱን ደህና ተወልዶ ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ዓመት ተኩል ያህል እንደሆነው በድንገት የብርድ በሽታ አጣደፈው፡፡  በዚያው ህይወቱ አለፈ፡፡”
ባል አዘነ፡፡ ጥቂት ጊዜ ካለፈም በኋላ፤
“ለመሆኑ ስሙን ማን አላችሁት?” አለና ጠየቀ፡፡
“በታወቀው የአካባቢያችን ጀግና ስም ነበር የሰየምነው” አለችው፡፡
“አይ በቃ፤ ልጄ በምን እንደሞተ አወቅሁት” አለ፡፡
“እንዴት? በምንድነው የሞተው?”
“ስሙ ከብዶት ነው!!” አለ፡፡
*   *   *
ስማቸው የከበዳቸው አያሌ ናቸው፡፡ ግማሾቹ ድርጅት ናቸው፡፡ ግማሾቹ ፓርቲ ናቸው፡፡ ግማሾቹ ግንባር ናቸው፡፡ በቅጡ ሳይወለዱ የሞቱ አሉ፡፡ የጨነገፉ እንደማለት፡፡ ተወልደው ብዙም ሳይቆዩ የሞቱ አሉ፡፡ ገና እሚኖሩና ገና እሚሞቱ አሉ፡፡
በተለይ በፖለቲካ ትግል ጉዞ ውስጥ የሆነውን ለምን ሆነ ብሎ ወደኋላ መጨናነቅ እርባና የለውም፡፡ ለትምህርቱና ለተመክሮነቱ ካልሆነ ያዙኝ ልቀቁኝ ቢባል ፍሬ የለውም፡፡ ይልቁንም የተሻለ መንገድን ማቀድና መቀየስ ነው የሚያዋጣው፡፡
“አንዴ ቮልካኖው [አሳተ - ገሞራው] ከፈነዳ በኋላ ላቫውን (ብታኙን) እንደገና መልሶ ወደ እሳቱ ሆድቃ መክተት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ማድረግ ያለብን አትክልት መትከል፣ ሣሩን ማጨድና በጐቹን ለግጦሽ ማሰማራት ነው” ይሉናል ፀሐፍት፡፡ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ላስተዋለ የረዥም ጊዜ ሙሾ - አውራጅነት ይበዛዋል፡፡ ውሃ ወቀጣ ነው፡፡ ልብ አላልን ይሆናል እንጂ ከቶም ውሃ - ቅዳ ውሃ መልሱና ድግግሞሹ የትም አላደረሰንም፡፡ ታሪኩና ወቅታዊ ድርጊቱ ተሰምሮ አይለይም፡፡ ሲወድቁ ተስፋ አለመቁረጥና በአጭር ጊዜ የድል ባለቤት ለመሆን መጣደፍ ረብ ያለው ውጤት አያመጡም፡፡ ጥፋትና ጥቃት ደረሰብኝ ብሎ ባንዴ መበታተንም የማለዳ ኢላማን መዘንጋት ነው፡፡
“እያንዳንዱ ወንጀል ፍርሃት መቀፍቀፉ አይቀርም”፡፡ ይሄ ደግሞ ፍርሃትን ለማስወገድ በሚወሰድ የኃይል እርምጃ ይተካና ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴን ያጨልማል፡፡ አለመዘንጋት ያለብን ዲሞክራሲ አዳጊ ሂደት እንደሆነ ሁሉ አምባገነናዊ ሥርዓትም አዳጊ ሂደት እንጂ ያንድ ጀንበር ጉዳይ አለመሆኑን ነው፡፡ ድንገት የበቀለ አገር እንደሌለ ሁሉ ድንገት ዱብ - ዕዳ የሚሆን ሥርዓት አይኖርም፡፡ የብራ - መብረቅ የሆነ (a Bolt from the blue) ዲሞክራሲ የለም፡፡ በልክ የተሰፋ ዲሞክራሲም ባንድ አፍታ ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ሁሉ ነገር በተዛማጅነት ነው ወደ ዕድገት የሚያመራው፡፡ ያ ማለት ግን ሲያመች በእጅ ሲያቃጥል በማንኪያ በማድረግ ለራስ እንደሚጣፍጥ አርጐ መዋጥ አይደለም፡፡ ሁሌም ማዕከሉ የሀገርና የህዝብ ጥቅም መሆን አለበት!
በኢትዮጵያ ምድር ፖለቲካ ከውሸት ጋር መያያዙ የጥንት የጠዋት ጉዳይ ነው፡፡ “መቦልተክ”፣ መዋሸት የሚል ትርጉም ይዞ ነው የኖረው፡፡ “እገሌ ቦለቲከኛ ነው” ከተባለ ይዋሻል ነው፡፡ ሁሉም ወደወንበር ያመራ ሁሉ ጠዋት ስለህዝብ፤ ማታ ስለራሱ ማውራቱ ነው አስቸጋሪው፡፡ በሀቅ ስለሀቅ በመጓዝ አለመዝለቁ ነው አበሳው፡፡ የየሥርዓቱ ጣጣ መፈክሩ፤ መሸጫው ይሁን መሳቢያው፣ አለመለየቱ ነው፡፡ የሚባለው ሁሉ በሥራ መተርጐም አለመተርጐሙን ለማረጋገጥ ሙስናዊ ግብዓቶቹ እንቅፋት መሆናቸው ነው፡፡ ሙስናው በሙስና መሸፈኑ የባሰ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ እየከተተን መምጣቱ ነው፡፡ ህግ ሽፋን የሚሰጠው ለማን ነው? በሙስና ውስጥ አንበሳው ድርሻ የማነው? የሚለው ጥያቄ እንጂ ሙስናው ራሱን መፈተሽ የቀረ ይመስላል፡፡ ራሳቸው በወንጀል ተጠያቂ የሆኑት በወንጀል ጠያቂ ከሆኑ ወንጀሉ እንዴት መፍትሔ ያገኛል? “የሚያባርረኝ ጣሊያን እንቅፋት መቶት በሞተ ጀግና ነህ ብለው አሠሩኝ እንጂ እኔስ ዓርበኛ አይደለሁም” የሚለው የዓርበኛው ደምበል ንግግር የየዘመኑ ፖለቲካና ፖለቲከኛ መልክ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡  

Read 4952 times