Saturday, 21 February 2015 12:37

4ኛው የICT ውድድር ምዝገባ ተጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

አሸናፊው 75ሺ ብር ይሸለማል

አራተኛው አገር አቀፍ የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውድድር ምዝገባ መጀመሩን የICT የልቀት ማዕከል ያስታወቀ ሲሆን አንደኛ የሚወጣ አሸናፊ 75 ሺ ብር እንደሚሸለም ተገለፀ፡፡ ማዕከሉ ሰሞኑን በኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል በሰጠው መግለጫ፤ በዘንድሮው ውድድር ለሴቶች ልዩ ትኩረት የተሰጠ ሲሆን በሴቶች ምድብም ሆነ ፆታ በማይለየው ምድብ መወዳደር እንደሚችሉ የልቀት ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ ተናግረዋል፡፡
ለውድድሩ የሚቀርቡ የፈጠራ ሥራዎች በተለይ ሞባይል ላይና የአገሪቱን ልማት የሚደግፉ አፕሊኬሽኖች ላይ ቢያተኩሩ እንደሚመረጥ የተገለጸ ሲሆን ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት የአመልካቾችን መወዳደሪያ መቀበል ጀምሯል ተብሏል፡፡
የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአቅም ግንባታ ዳይሬክተር ዶ/ር ልኡልሰገድ አለሜ፤ “ውድድሩ የፈጠራ ስራዎች ሼልፍ ውስጥ ተደብቀው እንዳይቀሩ ይታደጋቸዋል” ብለዋል፡፡  
የICT የልቀት ማዕከል ተወዳዳሪዎች የስልጠና ቦታ እንዲያገኙ፣ የኔትዎርክና ሌሎች ችግሮች እንዳይገጥሟቸው በዘርፉ ከሚሰሩ ኩባንያዎችና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የማዕከሉ ዳይሬክተር አስታውቀው፤ በተለይም የፈጠራ ውጤቶቹ በአገሪቱ ላይ ትልቅ የገበያ እድል ያላቸው አፕሊኬሽኖች ቢሆኑ ይመረጣል ብለዋል፡፡ ተወዳዳሪዎች በሚያቀርቡት የውድድር ማመልከቻ ላይ የፈጠራ ሥራቸውን ምንነት፣ ጠቀሜታ፣ እንዴት እንደተሰሩና መሰል መረጃዎች በዝርዝር መግለፅ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
የሴቶች ተሳትፎ ለአንድ አገር እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ በውድድሩ ላይ  ሴቶች ይበልጥ እንደሚበረታቱ የተጠቆመ ሲሆን በርካታ ሴቶች በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉም ይጠበቃል፡፡
የአሸናፊዎች ሽልማት በሰኔ ወር እንደሚካሄድና አንደኛ የወጣው የ75ሺህ ብር ሽልማት እንደሚያገኝ የተገለፀ ሲሆን ሁለተኛ የወጣው 50ሺ ብር፣ ሶስተኛው ደግሞ 25ሺ ብር ይሸለማሉ ተብሏል፡፡ ለአሸናፊዎች ከገንዘብ ሽልማት በተጨማሪ በዓመታዊ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች ላይ የመሳተፍና የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት እድል እንደሚመቻችላቸው ተገልጿል፡፡

Read 1602 times