Saturday, 21 February 2015 12:36

ንግድ ባንክ የ6 ወር የሥራ አፈጻጸሙ አመርቂ መሆኑን ገለፀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘንድሮ (2014/15) የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የሥራ ክንውን አመርቂ እንደሆነ የጠቆመው የባንኩ ሪፖርት፤ በታህሳስ ወር መጨረሻ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ 30,2014 ከነበረበት 193.3 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 209.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን አመልክቷል፡፡
በግማሽ ዓመቱ ከተለያዩ ምንጮች ከ2.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡንና በተለያዩ መስኮች ለተሰማሩ የመንግሥትና የግል ተቋማት 3,529 ሚሊዮን ዶላር ክፍያዎች መፈጸሙን፣ እንዲሁም በዚሁ ጊዜ 31.8 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱንና ቀደም ብለው ከተሰጡ ብድሮች ውስጥ 19.7 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጿል፡
ሁሉንም የባንኩን ቅርንጫፎች በT-24 የኮር ባንኪንግ ሶሉሽን ሲስተም ውስጥ በማስገባት ለደንበኞቹ ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ በያዝነው ግማሽ ዓመት 132 ቅርንጫፎችን ሲስተም ውስጥ በማስገባት በሲስተም የተገናኙ ቅርንጫፎችን ቁጥር 762 እንዲሁም የዋናው መ/ቤት የሥራ ክፍሎችን አራት ማድረሱን አመልክቷል፡፡
የካርድ ባንክ፣ የሞባይልና የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎቶችን ለኅብረተሰቡ በስፋት ለማሰራጨት በያዘው ዕቅድ መሠረት 597 ኤቲኤምና 1,265 pos (Point of sales) ተጨማሪ ማሽኖችን ወደ ክፍያ ስርዓቱ ማስገባቱን አስታውቋል፡፡
በመላ ሀገሪቱ ቅርንጫፎችን በመክፈት የባንክ አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ባደረገው ጥረት፣ በግማሽ ዓመቱ 77 አዳዲስ ቅርንጫፎችን መክፈቱንና አጠቃላይ የቅርንጫፎቹ ቁጥርም 909 መድረሱን፣ በዚሁ ጊዜ ውስጥ 1.3 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች ሂሳብ መክፈታቸውንና አጠቃላይ የደንበኞቹ ቁጥር በታኅሳስ 2007 9.5 ሚሊዮን መድረሱን ገልጿል፡፡
የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያልነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ባንኩ ለማምጣት ባደረገው ጥረት ከወለድ ነፃ ሂሳብ የከፈቱ ደንበኞች ከ38ሺ በላይ ሲሆን 491.4 ሚሊዮን ብር ማስቀመጣቸውን፣ ከ208ሺህ በላይ ሴቶች በልዩ የቁጠባ ሂሳብ ተመዝግበው 1.95 ቢሊዮን ብር ተቀማጭና ከ201ሺህ ወጣቶችና ታዳጊዎች 234.2 ሚሊዮን ብር ማስቀመጣቸውን አስታውቋል፡፡
ባንኩ፣ በግማሽ ዓመቱ 4,058 አዳዲስ ሠራተኞችን የቀጠረ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ የባንኩ ሠራተኞች ቁጥር ከ22ሺህ በላይ መድረሱን ገልጿል፡፡

Read 1955 times