Saturday, 21 February 2015 12:33

የሐዘን መግለጫ - በእንተ እቱ ገረመው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአደረባት ድንገተኛ ሕመም ሕይወቷ ያለፈው  ደራሲና ጋዜጠኛ እቱ ገረመው የቀብር ሥነ ሥርዓት የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም በትውልድ ሀገሯ አርባ ምንጭ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ በርካታ ወዳጅ ዘመዶቿና የከተማው ነዋሪዎች በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡
የአንዲት ሴት ልጅ እናት የነበረችው ጋዜጠኛ እቱ ገረመው፥ በአዲስ አድማስ፣ በኔሽንና በኢትዮ- ቻናል ጋዜጦች፣ በእፎይታና በቢዝነስ ታይምስ መጽሔቶች፤ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በዛሚ ሬዲዮ ላይ በጋዜጠኝነት ሞያዋ ሠርታለች፡፡
ጋዜጠኛዋ ባለፉት ሦስት ዓመታት “ማሺሪያ” (በወላይትኛ ሴትዮዋ ማለት ነው) የተሰኘና በሴቶች ላይ ትኩረት አድርጐ የሚታተም መጽሔት ስታዘጋጅ የቆየች ሲሆን፤ በዚህ መጽሔት በአርባ ምንጭና በአካባቢው የሚታዩ የሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በማጋለጥ፣ የክልሉ ሴቶችን ጭቆና በመታገልና መብታቸው እንዲከበር የበኩሏን ጥረት አበርክታለች፡፡ ጋዜጠኛዋ እቱ  “የጭን መነባንብ” የተሰኘ ልብወለድ መጽሐፍም ለኅትመት አብቅታለች፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፥ በእቱ ገረመው ድንገተኛ ህልፈት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እየገለፅን፤ ለልጇ፣ ለቤተሰቦቿና ለወዳጅ ዘመዶችዋ መጽናናትን እንዲሰጣቸው እንመኛለን፡፡

Read 2960 times