Saturday, 14 February 2015 15:19

የህንዱ ጠ/ሚ ጣኦት ተሰርቶላቸው እየተመለኩ ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ደጋፊዎቻቸው ገንዘብ አዋጥተው በስማቸው በመሰረቱት ቤተ መቅደስ ውስጥ ባቆሙላቸው ጣኦት አማካይነት እየተመለኩ እንደሆነ የዘገበው ሮይተርስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የደጋፊዎቻቸው ድርጊት እንዳስደነገጣቸውና አፈንጋጭ እንደሆነ መናገራቸውን አስታወቀ፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊዎች፣ ራጅኮት በተባለችው የህንድ ምዕራባዊ ከተማ በሰሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁጭ ብለው የሚያሳይ ጣኦት አቁመው እያመለኩ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
“ነገሩ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ ግለሰቦቹ የሰሩት ስራ ለዘመናት ከዘለቀው ታላቁ የህንድ ባህል ጋርም የሚጋጭ ነው፡፡ ባህላችን እንዲህ አይነት ቤተ መቅደሶችን እንድንሰራ አላስተማረንም” በማለት ድርጊቱን አውግዘውታል፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ የተከፉት የተወሰኑ የቤተ መቅደሱ ፕሮጀክት አስፈጻሚ አባላት በበኩላቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጣኦት በአንድ የሂንዱ ፈጣሪ ሃውልት ለመተካት አቅደዋል፡፡
“ጠቅላይ ሚኒስትራችንን እንወዳቸዋለን፤ እናመልካቸዋለን፡፡ ምክንያቱም እሳቸው እስከዛሬ ከነበሩት መሪዎቻችን ሁሉ የተለዩ ትልቅ ሰው ናቸው!” ብለዋል፤ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የዋለውን መሬት በነጻ ያበረከቱት ፓሬሽ ራዋል የተባሉ ህንዳዊ ባለጠጋ፡፡

Read 4702 times