Saturday, 14 February 2015 15:00

ባለ ሲኒማ ቤቱ “አናት” የገበያ ማዕከል ዛሬ ይመረቃል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

ከ48.5 ሚ. ብር በላይ ፈጅቷል
    ቦሌ አካባቢ “አናት” (አበበ ና ትህትና) በተባሉ ባልና ሚስት ስም ምህፃረ ቃል የተሰየመውና ዘመናዊ ሲኒማ ቤት የያዘው የገበያ ማዕከል ዛሬ ይመረቃል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ የዕድገት ግስጋሴና የቆዳ ስፋቷም በየአቅጣጫው እየሰፋ ያለ ዘመናዊ የአፍሪካ መዲና ለመሆን እየተጋች ስለሆነ፣ ለዕድገቷ የሚመጥን ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ያስፈልጋታል ያሉት ኢንጂነር አበበ አያሌው አሳየኸኝ፤ ሙያቸውን ተጠቅመው ሥርዓትና ውበት ያለው፣ ለከተማዋ ዕድገት የሚመጥን ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ለመስራት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
ቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ፣ ከቦሌ መሰናዶና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ትንሽ ከፍ ብሎ ወደ ጌታሁን በሻህ ሕንፃ በሚወስደው አስፋልት መንገድ ዳር ላይ 540 ካ.ሜ ቦታ ከግለሰብ በውድ ዋጋ  ገዝተው፣ ከ48.5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ፣ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል፣ በመገንባት በቅርቡ  አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉ ሌሎች የገበያ ማዕከላት ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ለየት ያለ ባህሪይ እንዳለው የጠቀሱት ኢንጂነሩ፤ በመደበኛ 332፣ በማዕረግ (ቪአይፒ) እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች ታስበው የተሰሩትን ጨምሮ በአጠቃላይ 412 መቀመጫዎች ያሉት ዘመናዊ ሲኒማ ቤት አለው ብለዋል፡፡
ከህንጻው ግንባታ አንስቶ “ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ ሲኒማ ቤት እከፍትበታለሁ” በማለት ዲዛይን ሲያወጣና ሲሰራ የቆየው ልጄ ልዑል አበበ አያሌው ነው ያሉት ባለሀብቱ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአንድ ሲኒማ ቤት አስፈላጊ ናቸው የተባሉትን የድምፅ መቆጣጠሪያ፣ የድምፅ ማስተላለፊያ፣ የአየር ሙቀትና ቅዝቃዜ መቆጣጠሪያ… የተገጠሙለት፣ ምቹ ወንበሮች፣  ያለውና በዓለም አቀፍ የፊልም አቀማመጥ ደረጃ ዲዛይን የተደረገ ሲኒማ ቤት ተጠናቆ  ካለፉት ሶስት ወራት አንስቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉ የንግድ ሱቅ፣ የቢሮ፣ የሲኒማ፣ የካፍቴሪያ፣ የሬስቶራንትና ባር አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ ምድር ቤቱ ለመኪናና ለትልቅ አውቶማቲክ ጀኔሬተር ማቆሚያነት እያገለገለ እንደሆነ የጠቆሙ፤ ኢንጂነር አበበ፤ ሲሆን የፊት ማስዋቢያ ሕክምና እንደሚሰጥበትም ተናግረዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉን እንዴት “አናት” የሚል ስም እንደሰጡትና ተቃውሞ እንደቀረበባቸው ሲያስረዱ፤ “አናት የእኔና የባለቤቴ ስም (አበበ እና ትህትና) ምህፃረ ቃሉ አናት ይሆናል፡፡ የህንፃውን ግንባታ ስንጀምር፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሄጄ፣ ይኼ ስም ያልተያዘ መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ ይህን ስም ከ18 ዓመት በፊት አንድ የግል ስራ ስንጀምር ነው ለመጠቀም ያሰብነው፡፡ ይህ ህንፃ ከመሰረት ቁፋሮው ጀምሮ “አናት የንግድ ማዕከል” በሚል ነው የሚታወቀው፡፡ አሁን ስራው አልቆ አገልግሎት ስንጀምር ግን ችግር ገጠመን፡፡
“አናት የሚለው ከሁሉም በላይ የመሆን ስሜት ስላለው ለውጡ ተባልን፡፡ ለማስረዳት ብንሞክርም አልተቀበሉንም፡፡ በመሰረቱ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ የንግድ ስም ሲሰጥ ደንብና መመሪያ ያለው አይመስለኝም፡፡
ምክንያቱም በመላ አገሪቱ የወጡትን የንግድ ስሞች ስናይ፣ “እንቁራሪትና እባብ …” ከሚሉት በስተቀር በርካታ ግራ የሚያጋቡ ስሞች እናገኛለን፡፡ ቀደም ሲል የተበላሸውን ማስተካከል ተቀባይነት አለው፡፡ አንዳንዴ ግን ቅጥ ያጣል” ሲሉ ባለሃብቱ ይተቻሉ፡፡
“ስያሜውን ቀይሩ ስንባል፣ በልጆቼ ስም ለማድረግ ሞክሬ ነበር፡፡ ሁለት ሴቶችና ሁለት ወንዶች ልጆች አሉኝ፡፡ የመጀመሪያዋ ልጄ ስሟ ፀደይ ነው፡፡ አናትን በፀደይ ልለውጥ ሞክሬ ነበር፡፡ “ፀደይ የወር ስም ስለሆነ አትችልም” ተባልኩ፡፡ ሌላዋ ልጄ ስሟ ኅሊና ነው፡፡ የንግድ ስሙ “ኅሊና አበበ” በሚል እንዲተካ ጠየቅሁ፡፡ “ኅሊና፣ አዕምሮ ስለሆነ ሌላ የበላይነትን የሚያመለክት ነው” ተብሎ ውድቅ ተደረገብኝ፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ በንግድ ስም አወጣጥ ላይ ያለው መመዘኛ ቅጥ ያጣና ሥርዓት የሌለው፣ የህብረተሰቡንና የመንግስትን ፍላጎት የሚያሟላ አይደለም የሚል አቋም አለኝ፡፡ አሁንም ገና እልባት ስላልተሰጠው መፍትሄ ካላገኘሁ በፍ/ቤት የሚወሰን ይሆናል” በማለት አብራርተዋል፡፡
ኢንጂነር አበበ፤ የህንፃው ግንባታ በ1 ዓመት ከ4 ወር በመጠናቀቁ በአጭር ጊዜ አለቀ የሚባለውን አይቀበሉትም፡፡     “እኔ በአንድ ዓመት ነበር ለመጨረስ ያሰብኩት” ያሉት ባለሀብቱ፤ የመሰረተ ልማት ያለመሟላት ግን ችግር እንደፈጠረባቸውና እንዳዘገያቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይ የስልክ መስመር ማግኘትና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ይጠቅሳሉ፡፡ ሕንፃው በሊፍት ነው የሚሰራው፤ በቀን ቢያንስ ለ4 እና 5 ሰዓት መብራት ይጠፋል፤ በዚህ ጊዜ ስራ ይቆማል፡፡ 130 ያህል ሰራተኛ አሰማርቼ ነበር የማሰራው፡፡
ሰራተኞችን ሌሊቱን ጨምሮ በፈረቃ ለማሰራት ስለተገደድኩ ሶስት እጥፍ ወጪ እንድናወጣ ሆነናል፡፡ ይህ ችግር ያለፈ ብቻ ሳይሆን አሁንም አለ፡፡ መብራት ቢጠፋ ተብሎ የተገዛ ትልቅ ጄኔሬተር አለ፡፡ መብራት የሚጠፋው ሁልጊዜ ስለሆነ ለጄኔሬተር ነዳጅ የምናወጣው ከአቅም በላይ እየሆነብን ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉ አራት ፎቅ ቢሆንም ሊፍት አለው፡፡ ክፍሎቹ ሰፋፊ ከመሆናቸውም በላይ ብርሃናማ ናቸው፡፡ በህንፃው አናት (ሰገነት) ላይ እየተሰራ ያለው ባር አዲስ አበባን በምስራቅ በኩል ለመመልከት ጥሩ እይታ አለው፡፡ ፊልም ተመልካቾች በውጭው በኩል እንዲገቡ ሰፊ አሳንሰር ለማሰራት ዲዛይን እያወጡ መሆኑን ኢንጂነር አበበ አያሌው ተናግረዋል፡፡

Read 1918 times