Saturday, 14 February 2015 14:55

ብቸኛው የአልሙኒየም አምራች ኩባንያ ጥሬ እቃ በቁፋሮ ለማግኘት አቅዷል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

“ያለው ጥሬ ዕቃ ከሦስት ዓመት በላይ አያስኬደንም”

በኢትዮጵያ ብቸኛው የአልሙኒየም አምራች ኩባንያ “ኢንተር አፍሪካ ኤክስትሩዥን”፤የጥሬ እቃ አቅርቦቱን በማዕድን ቁፋሮ ለማግኘት በማቀድ ለማዕድን ሚኒስቴር የፈቃድ ጥያቄ ማቅረቡን ገለጸ፡፡ ቃሊቲ ቁስቋም ማሪያም አካባቢ የሚገኘውና ከ10 ዓመት በፊት በ45 ሚሊዮን ብር የተመሰረተው ኩባንያው፤በአሁኑ ሰዓት የጥሬ እቃ ግብአቱን ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግና ከአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የሚያገኝ ቢሆንም በአገር ውስጥ ያለው አቅርቦት ከሶስት ዓመት በላይ እንደማያስኬድ የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሃይማኖት አባተ ተናግረዋል፡፡ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማምጣት የግድ ጥሬ እቃው ባለበት አካባቢ ቁፋሮ ማካሄድ አስፈላጊ በመሆኑ ፕሮፖዛሉን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆነ ሰሞኑን ኩባንያውን ለጋዜጠኞች ባስጎበኙበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት የአልሙኒየም ፕሮፋይሎችን ከውጭ በማስመጣትና በመገጣጠም ሥራ ላይ ተሰማርቶ እንደነበር የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ ከብዙ ጥናትና ሃሳብ በኋላ ግብአቶቹን  በአገር ውስጥ ለማምረት ኩባንያው መመስረቱንና በቀን 15 ቶን አልሙኒየም የማምረት አቅም ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ “ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት የተለያዩ እድገቶችን እያሳየ በማምጣቱ፣ ካፒታሉም ወደ 60 ሚሊዮን ብር አድጓል” ያሉት አቶ ሃይማኖት፤ 650 ለሚደርሱ ሰራተኞችም የሥራ እድል ፈጥሯል ብሏል፡፡  
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት የሚጠቀማቸው ጥሬ እቃዎች፡ ፓወር ኬብሎች፣ የኮካ ቆርቆሮዎችና መሰል ቁሳቁሶችን ሲሆን ፓወር ኬብሉን ሜቴክ ሲያቀርብ፣ ሌሎቹን አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡ “ይህም ሆኖ የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት አለ” የሚሉት አቶ ሃይማኖት፤ተጨማሪ ጥሬ እቃ እንደ ኬኒያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ሌሎች ጎረቤት አገሮች ለማስመጣት የአጭር ጊዜ እቅድ መያዙን፣ በረጅም ጊዜ እቅዱ ደግሞ ማዕድን ሚኒስቴር ምላሽ ሲሰጥ የማዕድን ቁፋሮውን በመጀመር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት መታሰቡን ተናግረዋል፡፡
“እኛ በወር የምናመርተው የአልሙኒየም መጠን 450 ቶን ነው፤ የአገር ውስጥ ፍላጎቱ ግን በወር 400ሺ ቶን ነው” በማለት ያስረዱት አቶ ሃይማኖት፤ ኩባንያው አሁን ባለበት አቅም የጥሬ እቃ እቅርቦትና የቦታ ጥበት ባይገድበው የአገር ውስጥ ፍላጎቱን የመሸፈን አቅም እንዳለው በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡ አልሙኒየም የማይዝግ፣ በአየር ለውጥ የማይሞቅና የማይቀዘቅዝ፣ ክብደቱም ቀላል እንደሆነና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በአገር ውስጥ አልሙኒየም የሚያመርቱ ኩባንያዎች ቢበራከቱ አገሪቱን ከውጭ ምንዛሬ ከማዳናቸውም በተጨማሪ በርካታ የስራ እድሎችንና  ፉክክርን በመፍጠር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው ከ36 ዓይነት በላይ መጠንና አይነት ያላቸው የአልሙኒየም ምርቶችን የሚያመርት ሲሆን   አንድ ኪሎ ግራም አልሙኒየም በ98 ብር ለገበያ እንደሚያቀርብ፣ ከውጭ የሚገቡት ግን በኪሎ ግራም እስከ 125 ብር እንደሚደርሱ ተጠቁሟል፡፡
ፋብሪካው ወደ ስራ በገባበት ወቅት  በርካታ ፈተናዎች እንደነበሩበት የሚያስታውሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ብዙ ሃይልና ውሃ የሚጠቀም እንደመሆኑ እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት 160 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በመቆፈር፣ የከርሰ ምድር ውሃ ማውጣቱንና ከኩባንያው አልፎ የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የሃይል መቆራረጡን ለማስቀረትም ትልልቅ ጀነሬተሮችን በማስገባት በሶስት ፈረቃ ለ24 ሰዓት ይሰራል ብለዋል፡፡ ሌላው ፈተና ከውጭ ምርት ጋር መፎካከርና የአገር ውስጥ ምርቶቻቸውን ጥራት ማሳመን እንደነበረ ያወሱት አቶ ሃይማኖት፤ አሁን እነዚያን ሁሉ ፈተና በማለፍ ገበያ ውስጥ መግባቱንና የአቅርቦት እንጂ የገበያ እጥረት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት አልሙኒየም ከማምረትም ውጭ በሰንጋ ተራ እና በቃሊቲ አካባቢ የሚገኙ 40/60 የጋራ መኖሪያቤቶችን የማጠናቀቂያ ስራ ከመንግስት ወስዶ የማጠናቀቂያ ስራዎችን እየሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡ “ኢንተር አፍሪካ ኤክስትሩዥን” ኩባንያ፤ በሥራ ጥራትና በሥራ አመራር ብቃት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ለማግኘት እንደቻለ በጉብኝቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

Read 2449 times