Saturday, 14 February 2015 13:37

የካንሰር ገዳይነት ጨምሯል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

      በድሃ አገራት በየ2 ደቂቃው አንዲት ሴት በማህፀን በር ካንሰር ህይወቷ ሲያልፍ፤ በዓመት 230ሺ ሴቶች በበሽታው ይሞታሉ በካንሰር የሚሞተው በኤችአይቪ/ኤድስ ከሚሞተው በእጥፍ ይበልጣልካንሰር ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የህመም አይነቶች ጥቅል መጠሪያ ሲሆን ህመሙ የሚከሰተው የካንሰር ሴሎች ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ አድገው ጤናማ የሆኑትን ሴሎች ሲወሯቸው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ መነሻቸው የሚታወቅና በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰቱም የካንሰር ዓይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በአብዛኛው መነሻ ምክንያቱ ሲጋራ ማጨስ የሆነውን የሳንባ ካንሰርንና በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰቱትን የማህፀን በር እንዲሁም የጉበት ካንሰርን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በመላው ዓለም በየዓመቱ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል ከስምንቱ አንዱ የሞታቸው መንስኤ የካንሰር ህመም ነው፡፡ እንደ ጤና ድርጅቱ መረጃ፤ በየዓመቱ በካንሰር ህመም ሳቢያ ህይወቱን የሚያጣው ሰው በኤችአይቪ/ኤድስ ከሚሞተው በእጥፍ ይበልጣል፡፡ አለም አቀፉ የካንሰር ድርጅት በ2012 ዓ.ም ይፋ ያደረገው መረጃም፤ በዓለም በየዓመቱ 7 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ በካንሰር ህመም ሳቢያ ህይወቱ የሚያልፍ ሲሆን አስራ አንድ ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በየዓመቱ በበሽታው ይያዛል፡፡ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ከአምስት አመት በኋላ (እ.ኤ.አ በ2020) በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ሰዎች በካንሰር ህመም ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን በየዓመቱ በካንሰር በሽታ የሚያዘው ሰው ቁጥር ደግሞ 16 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአለም ካንሰር ቀንን በማስመልከት ባለፈው ረቡዕ በሒልተን ሆቴል የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱና ቀዳማይት እመቤት ሮማን ተስፋዬ በተገኙበት በተከፈተው ሲምፖዚዬም፤ የማህፀን ካንሰር ቅድመ ምርመራና ህክምናን በተመረጡ የጤና ተቋማት ለማስጀመር የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ ተደርጓል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ ንደተናገሩት፤
በአሁኑ ወቅት በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የመጠቃት ዕድላቸው እየጨመረ የመጣ ሲሆን ችግሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የጤናው ዘርፍ ፖሊሲ ክለሳ ተጀምሯል።
በአገራችን ሴቶችን ብቻ ከሚያጠቁት የካንሰር አይነቶች አንዱ የሆነውን የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግና ህክምና መስጠት የሚችሉ በርካታ የጤና ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንና በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በእያንዳንዱ ወረዳ መሰል የጤና ማዕከላትን ለማስፋፋት መታቀዱን ገልፀዋል፡፡ የካንሰር ህመም በአገሪቱ እጅግ ከፍ ያለ ጉዳት እያስከተለ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በቂ የህክምና ባለሙያዎች አለመኖራቸውና ህክምናው የሚሰጥባቸው ተቋማትና መሣሪያዎች በቂ አለመሆን
ችግሩን እንዳባባሰው ጠቁመዋል፡፡ በካንሰር ህመም ስፔሻላይዝድ ያደረጉና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች (oncologist) ሶስት ብቻ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ከሰተብርሃን፤ እነዚህ ባለሙያዎች አንድ ሰው መሥራት ከሚችለው ጊዜ በላይ የራሳቸውን ጤና አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ ያለእረፍት እየሰሩ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡  በቅርቡ የካንሰር ህክምናን ለማገዝ የሚያስችል የኬሞቴራፒ መሣሪያ በ14 ሚሊዮን ዶላር  መገዛቱንና ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለካንሰር ህመም ሕክምና የሚያገለግሉ መድሃኒቶችም ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ መድሃኒቶቹ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ሰዎች በነፃ የሚሰጥ ሲሆን መግዛት ለሚችሉት ደግሞ በ50 በመቶ ቅናሽ እንደሚሸጥ ገልፀዋል፡፡
ከእኛ አያልፍም (“Not Beyond Us”) በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚህ አገር አቀፍ ሲምፖዚየም ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ቀዳማይት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ዋንኞቹ ገዳይ በሽታዎች እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመው አገራችንም የዚህ ችግር ተጠቂ በመሆን ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል፡፡ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል ካንሰር አንዱ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ሮማን፤ በአሁኑ ወቅት በካንሰር ህመም ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱንና በተለይም የማህፀን በር ካንሰርና የመሳሰሉ በቅድሚያ መከላከል በምንችላቸው በሽታዎች ምክንያት ዜጐቻችን እየሞቱ መሆኑ የሚያሣዝን ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራና ህክምና የሚሰጡ የጤና ማዕከላት በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር አዋሣ፣ ጐንደር፣ መቀሌና ጅማ እንደሚገኙ በመጠቆምም ማዕከላቱን ለማስፋፋትና ተደራሽነታቸውን ለማረጋገጥ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ደይሬክተር ዶ/ር ማህሌት ክፍሌ ባቀረቡት ጽሑፍ በአገራችን በየዓመቱ ከሚከሰቱ ሞቶች 40 በመቶው
መንስኤያቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደሆኑ የአለም ጤና ድርጅትን የቅርብ ጊዜ ሪፖርት ዋቢ አድርገው ጠቅሰዋል፡፡ ሴቶችን ብቻ ለይተው ከሚያጠቁና በቀላል ምርመራና ህክምና ልንከላከላቸው እየቻልን እጅግ በርካታ ሴቶቻችንን ለህልፈተ ህይወት ከሚያበቁ የካንሰር አይነቶች አንዱ የሆነውን የማህፀን በር ካንሰር ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ዶ/ር ማህሌት ጠቁመዋል፡፡ International Agency for Research on Cancer (IARC) የተባለ ድርጅት በ2012 በኢትዮጵያ ባደረገው ጥናት፤ በአገሪቱ 60ሺ 749 የካንሰር ህሙማን መኖራቸውን ጠቁሞ ከእነዚህ መካከል 19ሺ654 የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ 41ሺ095 ደግሞ ሴቶች ናቸው ብሏል፡፡ የአንጀት ካንሰር ዋንኛው የወንዶች ገዳይ በሽታ መሆኑን ያመለከተው ጥናቱ፤ የጡትና የማህፀን በር ካንሰር ዋንኛው የሴቶች ገዳይ በሽታ እንደሆነ ጠቁሟል። ከኤችአይቪ/ ኤድስ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሴቶች በማህፀን በር ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከሌለባቸው ሴቶች በአምስት እጥፍ የሚበልጥ መሆኑም በሲምፖዚየሙ ላይ ተገልጿል፡፡ የሴቶች ገዳይ በሽታ እንደሆነ የሚነገርለት የማህፀን በር ካንሰር የሚከሰተው የካንሰሩ አማጭ በሆነው “ሒዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ” አማካኝነት ሲሆን በሽታው ማንኛዋንም የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የጀመረች ሴት ሊይዝ ይችላል፡፡ የአሜሪካ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ማህበር መረጃ፤ አንዲት ሴት አንደኛ ደረጃ በሚባለውና ገና በጀመረው ዓይነት የማህፀን በር ካንሰር ተይዛ ለአምስት አመት በህይወት የመቆየት እድሏ 95 በመቶ ሲሆን ካንሰሩ ካለበት የማህፀን በር አካባቢ ተሰራጭቶ ወደ ሌላ የሰውነቷ ክፍሎች ከተሰራጨ በኋላ ለአምስት አመት በህይወት የመቆየት እድሏ 10 በመቶ ብቻ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ “ፒንክ ኤንድ ሬድ ሪባን” በተባለና በማህፀን በርና ጡት ካንሰር በሽታዎች ሳቢያ የሚሞቱ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ዜጐችን ቁጥር ለመቀነስ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በሲምፖዚየሙ ላይ ፕሮግራሙን በይፋ የጀመረ ሲሆን የተለያዩ አለምአቀፍ ተቋማትም በፕሮግራሙ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡ ድርጅቱ በዕለቱ ይፋ ያደረገው መረጃ ንደሚያመለክተውም፤ በዓለም በየሁለት ደቂቃው አንዲት ሴት በማህፀን በር ካንሰር ሳቢያ ለህልፈት የምትበቃ ሲሆን በየዓመቱ ደግሞ 230 ሺ ሴቶች በዚሁ በሽታ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡

Read 4566 times