Saturday, 07 February 2015 13:33

የግብርና የቀረጥ ሳምንት እየተከበረ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

       የኢትዮጵያ ገቢዎች ባለሥልጣን “ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ!” በሚል መሪ ቃል ለ7ኛ ጊዜ የግብርና ቀረጥ ሳምንት እያከበረ ነው፡፡
ገቢ የህልውናችን መሰረት ስለሆነ ህብረተሰቡ ስለግብር፣ ታክስና ቀረጥ ያለውን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ ርእሰ ጉዳዩ አድርጐ እንዲወያይባቸው ከጥር 23 እስከ የካቲት 1 ቀን የሚቆይ የአንድ ሳምንት መርሐ ግብር ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የባለሥልጣኑ የትምህርትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ገልፀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ ኤፍሬም መኮንን ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የግብርና ታክስ ግንዛቤ ለመፍጠር የአንድ ሳምንት ትምህርት ይበቃል ማለት ሳይሆን ይህች አገር ማደግ ካለባት፣ የታከስ አሰባሰቧ መሻሻል አለበት፤ ህብረተሰቡም በግብር አሰባሰብ ረገድ ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ በመነጋገርና በመመካከር ሁሉም የጋራ ኃላፊቱን እንዲወጣና መነጋገሪያ ርእስ እንዲያደርገው ለማስገንዘብ ነው ብለዋል፡፡
 ባለሥልጣኑ የተለያዩ ፕሮግራሞች ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት አቶ አፍሬም፤ ከሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ከወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀትና አባላት፣ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች፣ ከመካከለኛ ግብር ከፋዮችና ከአነስተኛ ግብር ከፋዮች፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ አንቀሳቃሾችና ከጉምሩክ አስተላላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በግብር አሰባሰብ ረገድ የሰሯቸውን ክንውኖች የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ጥር 27 የተከፈተ ሲሆን  እስከ የካቲት 1 ይቆያል ተብሏል፡፡ በዋና ዋና የመዲናይቱ ጐዳዎች በመኪና ቅስቀሳ ማድረጋቸውንና ስለግብረና ቀረጥ ሳምንት በሚዲያዎች እንዳስተላለፉ፤ ክንውኑ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ክልሎችም ከደንበኞቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
400 ከሚደርሱ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ባለሥልጣን መ/ቤቱ እያደረገ ያለው የለውጥ ሥራዎች ጥሩ ቢሆኑም ይበልጥ መሻሻል እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ የግብር ጉዳይ የሁላችንም ስለሆነ ባለሥልጣኑ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ቅስቀሳ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የስፖርት አዘጋጆች የአየር ሰዓት ገዝተው ስፖርት የሚተነትኑበትና ዲጄዎች ሙዚቃ እያሰሙ የሚውሉባቸው ኤፍኤም ራዲዮች ሞልተው ሳለ፣ ገቢዎች ባለስልጣንን የሚያህል ትልቅ መ/ቤት በሳምንት በቲቪ የ20 ደቂቃ፣ በራዲዮ የ30 ደቂቃ ፕሮግራም ብቻ ማቅረቡ በቂ አይደለም፤ ሰፊ የአየር ሰዓት ሊኖረው ይገባል በማለትም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ከፍተኛ የሠራተኛ ጥሎ መውጣት (Turn over) ከሚታይባቸው መ/ቤቶች አንዱ የገቢዎች ባለሥልጣን መሆኑን የጠቆሙት ከፍተኛ ግብር ከፋዮች፤ ልምድ ያላቸው ሙያተኞች ሲለቁ አዲስ ማሰልጠን ጉዳት ስላለው መ/ቤቱ የሠራተኞቹን አያያዝ (ክፍያ፣ ጥቅማ ጥቅም…) እንዲፈትሽ፤ የሠራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ ተመሳሳይ ስላልሆነ መ/ቤቱ ራሱን እንዲፈትሽ፤ የተመላሽ ገንዘብ ክፍያ መዘግየትም እንዲስተካከል ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
“ወደ ታክስ መረቡ የገባን አለን፤ ብዙ ነጋዴዎች ግን አልገቡም ስለዚህ የንግዱ ሜዳ ፍትሐዊ አይደለም፤ ኦዲት አራት ዓመት ያህል ሰለሚዘገይ ወደኋላ ሄዳችሁ ወለድ ትጠይቁናላችሁ፣ የአገልግሎት አሰጣጡ ተመሳሳይ ስላልሆነ ውስጣችሁን ብታዩ ጥሩ ነው፤ …” በማለት በመ/ቤቱ ያዩትን ድክመቶች መጠቆማቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
አወያዮቹ ለተነሱት አስተያየቶች ከመድረክ በሰጡት ምላሽ፣ በአገልግሎት አሰጣጡ ብዙ መሻሻሎች ቢኖሩም ድክመቶች እንዳሉባቸው አምነዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ለማድረግ የእናንተና የሁሉም ደጋፍ ያስፈልገናል ያሉት አወያዮቹ፤ ማንኛውም ሰው አገልግሎት ፍለጋ ወደ ተቋሙ ሲመጣ ማሟላት የሚገባውን ግዴታዎች አሟልቶ መቅረብ አለበት፤ ያላሟላው ነገር ኖሮ አሟልቶ አንዲመጣ ሲነገረው “አገልግሎት አሰጣጡ ፈጣን አይደለም” ማለት አይችልም፡፡
በመ/ቤቱና በአገልግሎት ፈላጊዎች መካከል ግልፅነት ሊኖር ይገባል ያሉት ኃላፊዎቹ፤ ደንበኛን ያጉላላ፣ የሚለግም… ሠራተኛ ካለ መጠቆምና ማሳወቅ እንዳለባቸው ገልፀዋል። የኦዲት መዘግየትንና ወለድን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ በግብር ሕጉ መሰረት መጀመሪያ የሚደረገው አምንሃለሁ፣ የሠራኸውን ሳትደብቅ ክፈል የሚል ስለሆነ፣ ነጋዴው “እኔ ሰርቼ ያገኘሁት ይሄ ነው” ብሎ የሰጠውን እንደሚቀበሉ ተናግረዋል፡፡ ነጋዴው ያለበትን ግብር በትክክል ካሳወቀ፣ ኦዲት የሚደረገው በፍጥነትም ሆነ ቆይቶ ቢሆን ለውጥ እንደሌለው ጠቅሰው፣ ግብሩን አሳንሶ የከፈለ ሰው በኦዲት ሲደረስበት ግብራቸውን ለሚያሳንሱ ሌሎች ሰዎችም ማስተማሪያ እንዲሆን መቀጫው ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡
ድርጅቱ ኦዲት ለማድረግ  የሚያስጠረጥረው ደግሞ የተጋነነ ትርፍ ወይም የተጋነነ ኪሳራ ነው። የእኛም ሠራተኛ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ግብር ሲያሳንስ ወይም ከፍ ሲያደርግ ሕገ-ወጥነትን መከላከል የምንችለው በጋራ ስለሆነ ለመ/ቤቱ ማሳወቅ ያስፈልጋል በማለት ኃላፊዎች ምላሽ እንደሰጡ ታውቋል፡፡
አንዳንድ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ100ሺ በታች የሆኑ የ“ሐ” ነጋዴዎች፤ አገር ውስጥ ገቢ ግብር እየጫነብን መሥራት አቅቶናል፤ ከዚህ ኑሮ በሰው አገር ተሰድዶ መኖር ይሻላል በማለት የሚኮበልሉ አሉ ወይም አየር በአየር ሕገ ወጥ ንግድ ውስጥ የሚገቡ እየበረከቱ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ ተብለው የተጠየቁት አቶ ኤፍሬም፤ እነዚህ ነጋዴዎች የሂሳብ ባለሙያ መቅጠር ስለማይችሉ የሽያጭ መዝገብ እንዲይዙ አይገደዱም፡፡ ግብራቸው የሚተመነው በግምት ነው፡፡ ግምት ደግሞ ከፍም ዝቅም ሊል ሰለሚችል ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡
ሰለዚህ “ግብር በዛብኝ” እያሉ ከማማረር የየእለት ሽያጫቸውን በደብተር መዝግበው ቢይዙ መ/ቤቱን ከማማረር ይድናሉ፡፡ ያለ አግባብ ግብር ተጣለብኝ የሚል ሰው በ10 ቀናት ወይም በ30 ቀናት ውስጥ ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ቅሬታ ቢያቀርብ ይታይለታል፡፡ ብዙ ሰዎች ቅሬታ አቅርበው እውነታው ታይቶ ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል በማለት አብራርተዋል፡፡    

Read 1745 times