Saturday, 07 February 2015 13:34

ዛሬ አዲስ ቴሌቪዥን የ18 ሰዓት ቀጥታ ስርጭት ይጀምራል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ከ100ሚ ብር በላይ ወጪ ተደርጐበታል

    የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት ዓለምና ትላልቅ (ሜትሮ ፖሊታንት) ከተሞች የሚጠቀሙበትን ኤክስ ፒ (XP) የተባለ የመጨረሻ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ትራንስሚተር ዛሬ በ11 ሰዓት በማዘጋጃ ቤት ግቢ በይፋ በማስመረቅ የ18 ሰዓት ቀጥታ ስርጭት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የአዲስ ቴሌቪዥን ስርጭት፣ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባና አካባቢዋ ፋይዳቸው የጎላ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የ18 ሰዓት ስርጭት እንደሚጀምር የኤጀንሲው የትምህርታዊና ዶክመንተሪ ዘርፍ ዳይሬክተርና የምረቃው ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ያረጋል ገልጸዋል፡፡
አቶ አበበ፣ በሂደት ወደ መካከለኛ ምስራቅ አገሮችና ለዚች አገር ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች ስርጭቱ እንዲዳረስ ይደረጋል ብለዋል፡፡
መረጃ የሚገኘው ከህዝብ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የምንሰራው ከህዝቡ ጋር ስለሆነ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ነን ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከሕዝቡ የሚያገኙትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እየተነተኑ ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው መረጃ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲው፣ የ18 ሰዓቱን ስርጭት ለመሸፈን በርካታ ዝግጅት በመደረጉ በኢኮኖሚ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች፣ ህብረተሰቡን እያዝናኑ የሚያስተምሩ ጉዳዮች እንደሚቀርቡ ጠቅሰው፣ በርካታ የአየር ሰዓት ለመዝናኛው ክፍል መሰጠቱን፣ በትምህርት ክፍል ዶክመንተሪና የምርመራ (ኢንቨስቲጌቲቭ) ጋዜጠኝነት ሥራ፣ እንዲሁም የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እንደሚቀርቡ፣ በማህበራዊ ዘርፍ (በትምህርት፣ በጤና፣ በወጣቶች፣ በሴቶች፣ በሕፃናት ..) ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ዘገባዎች ስራዎች እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
በኢኮኖሚው ዘርፍ ልማትን ማስተዋወቅና የከተማዋን ገጽታ መገንባት፣ … እንዲሁም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በምርመራ ጋዜጠኝነት ካሜራቸውን ደግነውና ብዕራቸውን አሹለው እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸው፣ ህዝቡ በየትኛውም ክፍል የሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን (ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ጉቦ፣ ሙሰኝነት፣ …) እንዲሁም ከህዝብ አፍና ከመንግስት ነጥቀው ለግል ጥቅምና ብልጽግና የሚያውሉ ሰዎችን እንዲያጋልጡ ተማፅነዋል፡፡
ፖለቲካ፣ በህዝብና በመንግስት መካከል በምርጫ የሚደረግ ስምምነት በመሆኑና የህዝብና የመንግስት ሚዲያ በመሆናቸው፣ ህዝብ የመረጠውን መንግስት እንደሚያገለግሉ ጠቅሰው የዚያን መንግስት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ … በማስተዋወቅ ህዝቡ እንዲፈጽማቸው ማድረግ ግዴታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህም ሲባል እኛ የምንሰራው ከገዢው ፓርቲ ጋር ብቻ ነው ማለት አይደለም ያሉት አቶ አበበ፤ አሁን የምንገኝበት ወቅት የምርጫ ቅስቀሳ የሚከናወንበት ጊዜ ስለሆነ፣ ማንኛውም ፓርቲ፣ ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ፖሊሲውን፣ ስትራቴጂውን፣ ሐሳቡን፣ … ማቅረብ ስለሚችል የማናስተናግድበት ምክንያት አይኖርም ብለዋል፡፡
አዲስ ቲቪ፣ ቀጥታ ስርጭት መጀመሩን ምክንያት በማድረግ፣ ከትናንት በስቲያ በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ፣ “የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ተቋማት በብሔራዊ መግባባት ስራ ላይ ያላቸው ፋይዳ” በሚል ርዕስ ሲምፖዚየም መካሄዱንና ከልዩ ልዩ የህዝብ አደረጃጀቶች  የተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን አቶ አበበ ያረጋል አስረድተዋል፡፡

Read 4865 times