Saturday, 07 February 2015 13:32

“ወገቧ ችቦ አይሞላም” - ጤና ያቃውሳል!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

 ከልክ ያለፈ ቅጥነት መሀንነትን ሊያስከትል ይችላል

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ትኬት ቢሮ ውስጥ በትኬት ሽያጭ ባለሙያነት ተቀጥራ መስራት ከጀመረች አምስት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ቀላ ያለ መልክና ረዥም ቁመትን ብትታደልም የሰውነቷ ቅጥነት እህል በልታ የማታውቅ ያስመስላታል፡፡ ሁሌም ቅጥነቷን በአለባበሷ ለመደበቅ ትጥራለች፡፡
ብሔራዊ ቴያትር አካባቢ ከሚገኘው መ/ቤቷ ተነስታ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ እስከምትድረስ ወጪ ወራጅ ወንዶች እንደ ዘበት ጣል በሚያደርጉባት የለከፋ ቃላት ሁሌም ትናደዳለች። በተለይ ከወፍራም  ጓደኞቿ ጋር በምትሄድበት ጊዜ “ከእሷ ላይ ተልጠሽ ነው? ልጣጯ ነሽ?” እያሉ እንደሚያበሽቋት ትናገራለች፡፡ ለከፋው ጓደኛዋን ፈገግ የሚያሰኛት ቢሆን ለእሷ ግን ከእሬት የመረረ ነው፡፡
ወጣቷ ለከፋ የስነ ልቦና ችግር የዳረጋትን ቅጥነቷን ለማስተካከል ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም፡፡ ሰዎች ስታማክር፤ “ውፍረት ምን ያደርግልሻል? በሽታ እኮ ነው” ይሏታል፡፡ እሷ ግን ያልተነካ ግልግል ያውቃል ትላቸዋለች፡፡ የሚያወፍሩ ምግቦችን አብዝቶ ከመመገብ አንስቶ የተለያዩ የቫይታሚንና ሚኒራል ይዘት ያላቸው መድኀኒቶችን በመውሰድ ቅጥነቷን ለማስወገድ ጥራለች፡፡ ግን ለውጥ አላመጣችም፡፡
የ28 አመቷ ወጣት በሰውነቷ ቅጥነት ሳቢያ ከሚደርስባት የሥነ ልቦና ችግር የበለጠ የሚያሳስባት በየጊዜው በቀላል ህመሞች መጠቃቷና ራሷን ከበሽታ የመከላከል አቅሟ ደካማ መሆን ነው፡፡ እንደ ጉንፋን፣ ራስ ምታትና የምግብ አለመስማማት ያሉ ቀላል በሽታዎች ለሶስትና አራት ቀናት ሊያስተኝዋት ይችላሉ፡፡ በየጊዜው ለሚደቋቁሷት ህመሞቿ የምታነጋግራቸው የህክምና ባለሙያዎች፤ሰውነቷ ከጤናማውና ከሚፈለገው የክብደት መጠን በታች በመሆኑ በሽታን የመቋቋም አቅሟ እንደተዳከመና በዚህም ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች በቀላሉ እንደምትጋለጥ ገልጸውላታል፡፡ ከመጠን ያለፈው ቅጥነቷ  መሀንነትን ሊያስከትል እንደሚችልም ነግረዋታል፡፡ ወደ ትክክለኛው የሰውነት ክብደት መጠን ለመግባትም በባለሙያ  የታገዘ የአመጋገብ ሥርዓትን እንድትከተል ምክር ለግሰዋታል፡፡
ወጣቷ የህክምና ባለሙያዎቹ የሰጧትን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ከችግሯ ለመላቀቅ ብትጥርም ምንም ውጤት ለማግኘት ባለመቻሏ ተስፋ መቁረጧን ትናገራለች፡፡ አሁን እሷን ይበልጥ የሚያሳስባት ጉዳይ ግን የበዛው ቅጥነቷ ልጅ ወልዶ መሳምን እንዳይነሳት ነው፡፡  በአሁኑ ወቅት እንደዚህች ወጣት ሁሉ በቅጥነት ሳቢያ ለሚመጡ የጤና ችግሮች በቀላሉ የሚጋለጡ ወጣቶች እየበረከቱ እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ፋሲል ተካልኝ ስለ ሁኔታው ሲያስረዱ፤ “ከሚፈለገው የሰውነት ክብደት መጠን በታች መሆን ለተለያዩ የጤና ችግሮች ሊዳርግ ይችላል፡፡ ትክክለኛ የሰውነት ክብደት መጠንን ለማወቅ የሚቻለው Body mass index በሚባለውና የሰውነት ቁመትን እርስ በርሱ በማባዛት፣ ክብደትን ለቁመት ብዜት በማካፈል ስሌት በሚሰራ ሳይንሳዊ መለኪያ መሰረት ነው። ሰዎች በዚህ ስሌት መሰረት የሚያስፈልጋቸው የክብደት መጠን ተሰርቶ ከዚያ ያነሱ ከሆነ፣ ከክብደት በታች ናቸው ይባላል፡፡ ይህም ቋሚና ዘላቂ ከሆኑ የጤና ችግሮች አንስቶ በቀላሉ ለበሽታዎች መጋለጥን ለሚያስከትለው የበሽታ መከላከል አቋም ማጣት ሊዳርግ ይችላል” ብለዋል፡፡
ጤናማ ሆነው ምግብ በአግባቡ የሚመገቡና የሰውነት ኢነርጂ ማግኛ ስርአታቸው የተሳካ ሆኖ በዘር አፈጣጠራቸው ምክንያት ከሲታ ሆነው የሚታዩ ሰዎች ግን ይህ አይነቱ ችግር ሊያጋጥማቸው እንደማይችል ሃኪሙ ተናግረዋል፡፡ የሰውነት ክብደት በተለያዩ ምክንያቶች ሊቀንስ ይችላል ያሉት ባለሙያው፤ ከእነዚህ መካከል የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ጭንቀትና ውጥረት፣ የአዕምሮ መደበትና የተለያዩ ህመሞች ጥቂቶቹ እንደሆኑ ጠቁመው በቀላሉ በበሽታ መጠቃት፣ መስራት የሚያስችል ኢነርጂ ማጣት፣ ቆዳ መሸብሸብና የጡንቻ መሟሸሽ የዝቅተኛ የሰውነት ክብደት ምልክቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ከክብደት በታች የሆኑ ሰዎች ከሚያጋጥማቸው የጤና ችግሮች መካከል ዋንኛው በሽታን የመከላከል አቅም ማጣትና በተለያዩ በሽታዎች በቀላሉ መጠቃት ነው ይላሉ - ባለሙያው፡፡ በቂ ንጥረ ምግቦች በሰውነታችን ውስጥ ያለመኖር፤ ቆሻሻን ከሰውነታችን ውስጥ የማጣራት ሂደትን የሚያስተጓጉል በመሆኑ ሰውነታችን በመርዛማ ኬሚካሎች እንዲጎዳ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዝቅተኛ ክብደት ኢንፌክሽኖችን የመቋቋም ብቃትን በማዳከም ለበሽታ ይዳርጋል። ከመጠን ያለፈ ድካም፣ የልብ መምታት ችግር፣ የስርዓተ ልመትና የምግብ መፍጨት ችግሮች በዝቅተኛ ክብደት ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እክሎች እንደሆኑም ሃኪሙ ተናግረዋል፡፡
ዝቅተኛ የሰውነት  ክብደት ያላቸው ሴቶች ለመሃንነት የተጋለጡ ናቸው የሚሉት ዶ/ር ፋሲል፤ ምክንያቱን ሲገልጹም በሰውነት ቅባት ውስጥ የሚገኘውንና ለመራቢያ ሆርሞኖች ወሳኝ ግብአት የሚሆነውን ነገር ስለሚያጡ ነው ብለዋል፡፡ “ቀጭን ሴቶች በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኘው ቅባት (ፋት) እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ይህ ቅባት ደግሞ ለመራቢያ ሆርሞኖች መኖሪያ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህም ከሲታ ሴቶች እነዚህን ሆርሞኖች በበቂ መጠን ለማቅረብ ስለማይችሉ የመፀነስ እድላቸው እጅግ የመነመነ ነው፡፡”
እነዚህን ችግሮች አልፎ ፅንሱ ቢፈጠር እንኳን በተለይ በፅንሱ የመጀመሪያ ወራት አካባቢ ውርጃ መከተሉ አይቀሬ ጉዳይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተዛባ የወር አበባ ዑደት፣ የደም ማነስ፣ ደም በበቂ ሁኔታ ኦክስጅንን በሰውነታችን ውስጥ እንዳያዘዋውር የማድረግ ችግር ሁሉ በዝቅተኛ የሰውነት ክብደት ሳቢያ የሚከሰት የጤና ችግር እንደሆነ ሃኪሙ ጠቁመዋል፡፡
ዝቅተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸው ሴቶች፣በባለሙያዎች ምክር የታገዘ የአመጋገብ ሥርዓት በመከተል  ክብደታቸው ወደ ትክክለኛው መጠን እንዲደርስ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ “ወገቧ ችቦ አይሞላም” ሲበዛ ጤና ያቃውሳል ማለት ይኼው አይደለ?!

Read 7572 times