Saturday, 07 February 2015 13:26

‘በሁለቱም ወገን የሚለበስ ጃኬት…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንበልና ከሆነ የምታውቁት ሰው ጋር ከረጅም ጊዜ በኋላ ትገናኛላችሁ፡፡ እናማ…ገና ስታዩት እሱዬው የሆኑ… አለ አይደል…‘የሆኑ’ ለውጥ የሚመስሉ ነገሮች ታዩበታላችሁ፡፡ ገና ሲጨብጣችሁ… “ይሄ ሰውዬ በሦስት ጣቶቹ ብቻ መጨበጥ ጀመረ እንዴ!” ያሰኛችኋል፡፡ ልክ ነዋ… (አምስቱ ጣቶችማ ወይ ‘ፈራንካ’፣ ወይ ‘ወንበር’ ምናምን ለፈቀዱለት ነዋ!)
እናላችሁ…እሱዬው ነገርዬው ሁሉ ግራ፣ ግራ ነገር ይሆንባቸዋል፡፡ ቃላቱን እየቆጠበ… “ደህና ነህ?” ይላችኋል፡፡ የ“ደህና ነህ?”  ቃናዋ…አለ አይደል…“እንደው ቺስታነቱን ችለኸው እስካሁን ቆየህ!” አይነት ነው፡፡ እናላችሁ… “… ድሮ ጋዜጣ ላይ ምናምን ትጽፍ ነበር!…” ይልና አንጠልጥሎ ይተወዋል፡፡ እናንተም የውሸት የ‘ዲፕሎማት’ የሚመስል ፈገግታ ታሳዩና… “አዎ…” ትሉታላችሁ፡፡ ያው ትንሽ ‘ስማርት ፎን’…ምናምን ነገር ብቅ፣ ጥልቅ ያደርግባችሁና በሰላምታ ትለያያላችሁ፡፡
ታዲያላችሁ…ያንኑ ሰው በአሥራ አምስተኛው ቀን ታገኙታላችሁ፡፡ የተለመዱትን ሰላምታ የሚመስሉ ነገሮችን ትለዋወጡና ምን ይል መሰላችሁ… “ሁልጊዜ ጽሁፍህን አነባለሁ…” በእሱ ቤት ‘ጮካ’ መሆኑ ነው!  ዘንድሮ መቼም የማናየው ‘ጉድ፣ የጉድ ጉድ’ የለም አይደል… በሁለት በኩል እየተገለበጠ እንደሚለበስ ጃኬት አንዴ ያወራነውን የሚቀጥለው ጊዜ ገልብጠን የምናወራ የበዛን አይመስላችሁም! ለምን መሰላችሁ…ዘመናዊ ለመምስል! ቂ…ቂ…ቂ… አሪፍ ድራማ ጸሀፊ… “ድንቄም ዘመናዊ ተሆነ!” የምትል ገጸ ባህሪይ ያለችበት ድራማ ይጻፍልንማ!
እኔ የምለው…  አንዳንድ ወዳጆቼ ….ስማ “አሁንም ትጽፋለህ!” የምትሉኝ… እና ጦሜን ልደርላችሁ! ወይስ ‘ሙያ’ ለውጬ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ…” ልሁን! ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አለ አይደል…ገና ሲ.ፒ.ኤ. ምናምን ደረጃ ውስጥ ያልገቡ መአት ሙያዎች የተፈጠሩ ይመስለኛል፡፡
ደግሞ አለላችሁ… እንዲሁ እንደ እኔ በ‘ራጂ’ እንኳን የማትታይ ደረቱን እያሳበጠ… ድምጹን ‘ነጎድጓዳማ’ ለማድረግ እየሞከረ… “ይገርምሀል፣ የዚህ አገር ጋዜጦች ስለማይጥሙኝ ማንበብ ካቆምኩ ብዙ ጊዜ ነው፡፡ በቃ…ያለ ጭቅጭቅ ምንም የለባቸውም፡፡…ምን እንደሚሉም አይገባኝም …” ምናምን ይላል፡፡ በተዘዋዋሪ እኮ… “ከአንተ ጀምሮ ምን እንደምትሉ አትገቡኝም…” ማለቱ ነው፡፡
እግረ መንገዴን… “አማርኛ መጽሐፍ አላነብም…” የሚሉ ሰዎች ገጥመዋችሁ አያውቅም! ለእነሱ አማርኛ መጽሐፍ ማንበብ… አለ አይደል… ‘ቅሽምና’ ምናምን ይመስላቸዋል፡፡ የምር ግን…ወደፊት ልናደርገውም፣ ላናደርገውም በምንችለው ‘የዳሰሳ ጥናት’ የሚደረስበትን ውጤት በቅድሚያ እነግራችኋለሁ…“አማርኛ መጽሐፍ አላነብም…” ከሚሉት ሰዎች አብዛኞቹ ከምግብ ሜኑ ባለፈ ሌላ ነገር አያነቡም፡፡ አሀ…ምልክቶች ስናይስ!
ታዲያላችሁ…ያ “የዚህ አገር ጋዜጦች ስለማይጥሙኝ ማንበብ ካቆምኩ ብዙ ጊዜ ነው…” ያለውን ሰው በሆነ ቅዳሜ ቀን ምናምን ወይ አራት ኪሎ ወይ የሆነ ቦታ አንድ ካፌ ቁጭ ብሎ ፊት ለፊቱ አምስት ጋዜጦችና አራት መጽሔቶች ደርድሮ ሲያገላብጥ ታዩታላችሁ፡፡ በቃ…የሆነ ቀሺም ነገር አይደለም! ሁለት ጋዜጣ በሚገዛበት ፍራንክ ስምንት ጋዜጣና አምስት መጽሔት ሲያገላብጥ እየዋለ…“የዚህ አገር ጋዜጣ አላነብም… ቅብጥርስዮ ምን አመጣው!
እናላችሁ… እንደዚህ ያልሆነውን ነገር በአደባባይ ለመምሰል የምንጥር በዝተናል፡፡ ህዝቤ ሰልፍ ኮንፊደንሱን ሁሉ በወለድ አግድ አስያዘው ማለት ነው! ያሰኛላ… በዚህ የሁላችን ዓይኖችና ጆሮዎች በሥራ በተጠመዱበት ዘመን… “አጎቴ በሄሊኮፕተር ሲያልፍ እንዳያያኝ…” አይነት እንደ ባቡሩ መቶ ዓመት የሞላው አራድነት አይሠራም፡፡ (‘ያኛውን ባቡር’ ማለቴ ነው፡፡ አሀ… ግልጥና ግልጥ መሆን አለበታ!)
ደግሞላችሁ የእኔ ቢጤዎች አለን… “ድራፍት! ደግሞ ድራፍት ልጠጣ!” ምናምን የምንል፡፡
“ድራፍት ብትጠጣ ምን አለበት!”
“ስማ እኔ ገና ሳየው ምን እንደሚመስለኝ ታውቃለህ…ገና ተጣርቶ ያላላቀ ዘይት ነገር፡ ሞቼ ነው ቆሜ ድራፍት የምጠጣው!
እናላችሁ… በሆነ አጋጣሚ እግር ጥሏችሁ በሆነ አካባቢ ስታልፉ… የሆነች ‘አይቅርብኝ፣ እኔስ ከማን አንሼ!’ ቀበሌ ክበብ በረንዳ ላይ እንደ ስዊስ በረዶ መንሸራተቻዎች ያጋደለች አግዳሚ ወንበር ላይ ‘ተጣብቆ’ ድራፍቷን በሁለት እጁ ጨብጦ ታገኛላችሁ፡፡ ፒያሳ ላይ ቢሸውዱ…ጀሞ ላይ ገልጦ የሚያይ አይጠፋም፡፡
ቂ…ቂ…ቂ… እኔ የምለው…ገና እኮ ችስት ያለች አገር ውስጥ ነን ያለነው! ልጄ ድራፍቱስ ተገኝቶ ነው! ልክ ነዋ…ሹሮ ሰማንያና ዘጠና ብር ስትገባ… ሆዳችን ውስጥ ያለውን ‘ክፍት መሬት’ በምን እንሙላው!
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሹሮ ነገር ከተነሳ ይቺን ስሙኝማ… ባለፈው ዓመት ጾም ጊዜ ከአንድ ወዳጄ ጋር ተጋሚኖአችንን ልንበላ የሆነች ቤት ገባን፡፡ እስከዛ ድረስ ‘የተቀለመ ሹሮ’ አይቼ አላውቅም ነበር፡፡ እናላችሁ…ተጋሚኖ የተባለው ነገር ቀረበ፡፡
የምር…በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ሹሮ መልክ ያለው እንጀራና ግራጫ መልክ ያለው ሹሮ ወጥ ያየሁት ያኔ ነው። ድራፍቱ እንኳን ተጣርቶ ያላለቀ ዘይት መሰለ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እንትናዎች…ስሙኝማ… ዊግ የምታደርግ እንትናችሁን ‘ቴምፕሬቸር’ ለመጨመር ስትፈልጉ ‘ጸጉሯ’ን ሰላም ስጡትማ፡፡ (የ‘ሲክስ ታውዘንድ’ ረብጣ ዕቃ የምን ማጨማደድ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…) እናላችሁ… የእናንተ የደም ስርጭት እየጨመረ ሲሄድና መዳበሱ ጠንከር ሲል እሷዬዋ ልትሳቀቅ ትችላላቻ! “ወይኔ ጉዴ! ምን ያንቀዠቅዣዋል! ስንትና ስንት ዓቢይ ጣቢያ እያለለት ጸጉሬን ነቅሎ ሊጥልብኝ ነው እንዴ!” (‘ዓቢይ ጣቢያ’ ተመችታኛለች፡፡)
ሀሳብ አለን… ዊግ የምታደርጉ እንትናዬዎች ቦርሳችሁ ውስጥ “ለሚመለከተው ሁሉ…” በሚል ርዕስ ‘የተግባር መመሪያ’ ምናምን የምትል ብጣሽ ወረቀት መያዝ አትርሱማ! ከሥሩ ‘አክሴፕት’ ‘ሪጀክት’ የሚሉ ሁለት ሳጥኖች ማስቀመጥ ነው። ልክ ነዋ… አንጀታችሁን አስራችሁ የገዛችሁትን ‘የአደባባይ መዋቢያችሁን’… አለ አይደል… “ነቀለብኝ…” “አወረዛብኝ…” (ቃሉን ካወቃችሁት ለማለት ነው…) ምናምን ብሎ ከመሳቀቅ…ከአንገት በላይ የሚደረግ ዳበሳ…ከአሥራ አምስት ሴከንድ በላይ መቆየት የለበትም፡፡ አሀ…አሥራ አምስት ደቂቃ ብዙ ነዋ! (‘ደመ ቀዝቃዛው’ እንትና…አሥራ አምስት ሰዓት ይበቃሀል?” በአንድ ወቅት አንዲት ‘ግልጥ’ የሆነች ወዳጃችን በወቅቱ ስለነበረው እንትናዋ ምን አለችን መሰላችሁ…“ሳሙና ቀብቶኝ እሱን የሚፈትግልኝ ነው የሚመስለው!” ቂ…ቂ…ቂ… ለዚህስ አንድ ቁና የአጃ እህል መስጠት ነበር!
ስሙኝማ…ሌላ ሀሳብ አለን፡፡ ሁኔታዎች እስኪጣሩ… “ዞማ ጸጉርሽ ልቤን ምናምን አድርጎት…” አይነት ግጥሞች ላይ ማዕቀብ ይጣልልን፡፡ የምር ግን…ይሄኔ ግን ስንት ዕድለኛ ‘ዊግ’… “ጸጉሯ ዘንፈል ብሎ ትከሻዋ ላይ…” ምናምን ተብሎ ተዘፍኖለት ይሆናል!
ስሙኝማ…ይሄ ቫለንታይን ምናምን የሚሉት ቀን ደረሰ አይደል… አገር ‘ሊቀላ’ ነዋ! ገና ከአሁኑ ‘ቢዙ’ እየሞቀ ነዋ!
ይቺን ስሙኝማ…እሱዬው ብልጥ ነበር።  እናማ… እሷዬዋን ምን ይላታል…“እንዲች አድርጌ ሳልነካሽ ልስምሽ እችላለሁ፡ በአሥር ብር እንወራረድ፡፡”
“ሳትነካኝ ልትስመኝ አትችልም፣ እንወራራድ።”
ከዚያም ደጋግሞ ይስማታል፡፡ “ይኸው ስትስመኝ ነካኸኝ አይደል፣ ተሸንፈሀል… አለችው። እሱዬው አሥር ብሩን አውጥቶ ምን ቢል ጥሩ ነው…“በውርርድ መሸነፍ አዲስ ነገር አይደለም…” ብሎ ቀዩዋን ብር ሰጣታ፡፡ ለ‘ቫለንታይን ቀን አክባሪዎች’… ይቺ ዘዴ የኮፒራይት ጥያቄ የለባትም።
የመሳም ነገር ካነሳን…ይቺን እንጨምርማ…
“ትናንት ግብዣ ላይ አንዱ ልሳምሽ አይለኝ መሰለሽ!”
“ሰው ባለበት ግብዣ ላይ! የሆነ ጥሬ ነገር መሆን አለበት፡፡”
“ኧረ ጥሬ አይገልጸውም…”
“አታጮይውም ነበር!”
“ስሞኝ እንዳበቃማ አጮልኩት፡፡”
አሁንም ለ‘ቫለንታይን ቀን አክባሪዎች’… ከጥፊውና ከኪሶሎጂው ማን ሚዛን እንደሚደፋ ማስላት ነው፡፡
እናማ…በሁለቱም ወገን እንደሚለበስ ጃኬት ወሬያችንን የምንገለባብጥ… ከ‘ግልበጣ’ ያድነንማ  ቂ…ቂ…ቂ…
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2922 times