Saturday, 07 February 2015 13:23

“በፖለቲካ ትግሉ ውስጥ እንደ አሉባልታ ከባድ ነገር የለም”

Written by 
Rate this item
(12 votes)
  • አቶ ልደቱ ከ15 ዓመት በፊት የትጥቅ ትግል አስበው ነበር
  • ኢህአዴግ እያዳከመን ነው ማለት፣ የራስን ድክመት መናገር ነው
  • ህብረት መፍጠር የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አልጠቀመም    

የፖለቲካ ተሳትፎ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በተለይ ከ97 ምርጫ በኋላ በተፈጠሩ አሉባልታዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን “ቴአትረ ቦለቲካ፤ አሉባልታና የአገራችን የፖለቲካ ገመና” በሚል ርዕስ አዲስ መጽሐፍ ያወጡት የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው፤ በመፅሐፋቸው ጭብጥና በአጠቃላይ በአገሪቱ ፖለቲካ ዙሪያ ከጋዜጠኛ ኤልሳቤት ዕቁባይ ጋር አውግተዋል፡፡

ከፖለቲካው ብዙ ርቀዋል -- አሁን ምን እየሰሩ ነው?
በፖለቲካው ያለኝ ሚና ቢቀንስም አልራቅሁም። አሁን የስራ አስፈፃሚ አባል ስላልሆንኩ የእለት ተእለት ስራ ውስጥ የለሁም፡፡ በዚህ ምክንያት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር አልገናኝም፡፡ የኢዴፓ የላዕላይ ምክር ቤት አባል ነኝ፡፡ በፓርቲው ውስጥ ባለኝ የኃላፊነት መጠን መስራት ያለብኝን እየሰራሁ ነው፡፡ በሚዲያ ስለማልቀርብ ከፖለቲካው መራቅ ብቻ ሳይሆን የተውኩ ሁሉ የሚመስላቸው አሉ፤ እውነታው ግን ያ አይደለም፡፡ በእርግጥ ሙሉ ጊዜዬን ለፖለቲካው ስለማላውል ሌሎች ስራዎችን እሰራለሁ፡፡
“ቴአትረ ቦለቲካ” የተሰኘው አዲሱ መፅሃፍህ በዋናነት በአሉባልታ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ነው--
እዚህ መፅሀፍ ላይ ማስቀመጥ የፈለግሁት በአብዛኛው ሂደት ውስጥ የነበረውን ነገር ነው፤ አልፎ አልፎ የራሴን ጉዳይ ባስቀምጥም፡፡ ብዙ ጊዜ “ፖለቲካል ኮሬክትነስ” የምንለው ነገር አለ፡፡ ጉዳዩ እሱ አይደለም፤ ያለፍኩበትን ሂደት በነበረበት ሁኔታ አስቀምጬ፣ ሰዎች ሌላ ጊዜ እንደ እኔ ፖለቲካ ውስጥ ሲገቡ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ፈተና አስቀድመው እንዲያውቁት ነው፡፡ ሳያውቁት ገብተው በኋላ ላይ ችግር ከሚገጥማቸው… ምናልባትም ወደ ተስፋ መቁረጥ ከሚገቡ፣ ራሳቸውን አዘጋጅተው መቋቋም እንዲችሉ ለማድረግ ትንሽ አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይችላል ብዬ ነው የፃፍኩት። መፅሀፉ ላይ እንደገለጽኩት፤ መጀመሪያ ላይ አሉባልታ ብዙም አያስጨንቀኝም ነበር፤ “የሆነው ሆኗል፤ ያመንኩበትን አድርጌያለሁ፤ ሌላው ሰው የፈለገውን ቢል የኔ ችግር አይደለም፤ ነገሩ እየታወቀ ሲመጣ ሰዎች ሁኔታውንም እኔንም ይረዱኛል” የሚል አስተሳሰብ ስለነበረኝ፣ በጣም ጠንካራ በሆነ ሁኔታ ነው ተቋቁሜው የሄድኩት። ነገር ግን አንድ ቦታ ላይ ከዚያ አስተሳሰብ የተለየ፣ ምናልባትም ሰው መሆኔን በደንብ የሚነግረኝ ስሜት ተፈጠረ፡፡
ይህ በህይወቴ ላይ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶኛል። ሁላችንም ሰዎች እስከሆንን ድረስ የሚወጣ የሚወርድ፣ የሚፈራረቅ ስሜት አለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሳታውቂው በውስጥሽ የተከማቸ ነገር እንደዚያ አይነት ሁኔታ ሲያገኝ ሊወጣ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ይህንን ማስቀመጡ ተገቢ ነው በሚል እንጂ ያለፈ ነገር ነው፡፡  በዚህ ስሜት ውስጥ ማለፍ ምን ማለት ነው የሚለውን ለመረዳት እድል የሰጠኝ አጋጣሚ ነው፡፡ በፖለቲካ ትግሉ ያለኝን ተሳትፎ እንዳቆም ወይም እንዳለዝብ አሊያም ወደ ተስፋ መቁረጥ እንድሄድ ያደረገ ነገር አይደለም፡፡ በትግሉ እቀጥላለሁ፡፡ በእርግጥ የእድሜም ጉዳይ አለ፤ ለአዲሱ ትውልድ ቦታ መልቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ግን ይህን ምክንያት አድርጎ ከትግል መራቅ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ፖለቲካ ፈቅጄ፣ ወድጄ፣ አምኜ የገባሁበት ስለሆነ፣ ያሳለፍኩት ሂደት በጣም ከባድ ቢሆንም ወደፊትም የምርቀው ነገር አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ አሉባልታን በመኮትኮት ተሰሚነት እንዲያገኝ ያደረጉት ራሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙኃን ናቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎስ በዚህ ይስማማሉ?
ለእኔ አንዱ ለሌላው ያቀበለው ባህል አይመስለኝም፡፡ ችግሩ ሁሉም ላይ የነበረና ያለ በመሆኑ ተመጋጋቢ ነው፡፡ ሁላችንም የዚህ ህብረተሰብ ውጤቶች ነን፡፡ በእኔ እምነት አሉባልታ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ወይም የፕሬሱ ብቻ አይደለም፤ በአጠቃላይ እንደ ህብረተሰብ ያለብን ችግር ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን  የአሉባልታ ሰለባ ቢሆን ወይም አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የአሉባልታ አራማጅ ቢሆን የጉዳቱ መጠን ብዙ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ህብረተሰብን ለማስተማር፣ የህብረተሰብን አስተሳሰብ ለመቅረፅ የተቋቋመ መገናኛ ብዙኃን የአሉባልታ ሰለባ ሲሆን ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ ነው የፕሬሱን ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት በመጽሃፌ የጠቃቀስኩት። በጋዜጣ የተፃፈ፣ በራዲዮ ወይም በቴሌቪዥን የተነገረ ነገር ሁሉ እውነት መስሎ የሚታየው የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ በአፍሽ ስትነግሪው ውሸት የሚመስለው ነገር፣ በመገናኛ ብዙኃን ሲገለጽ፣ እውነት የሚመስለው ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ ችግሩ ፕሬሱ ውስጥ አለ፣ ፓርቲዎቹ ውስጥ አለ፣ ህብረተሰቡ ውስጥ አለ፡፡ አሉባልታውን የማቀባበሉ ሚና፣ ከአንዱ ወደ አንዱ ይሄዳል፡፡ ነገር ግን የመገናኛ ብዙኃን ከዚህ ካልፀዱ፣ አንድ አገር ትልቅ አደጋ ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡
 በአገሪቱ ያለውን ፕሬስ እንዴት ያዩታል?
እንግዲህ ሁሉ ነገር እኛ አገር ላይ ገና ነው፡፡ ያለን የፖለቲካ ባህል በጣም ኋላቀር ነው፡፡ በዚህ ኋላቀር ባህል ውስጥ ሆነን ሚዲያው ለብቻው ተለይቶ፣ ከችግር ነፃ ሆኖ ሊያድግ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሚዲያ ከችግር የፀዳ ሆኖ እንዲወጣ አልጠብቅም፡፡ ቁጥሩ አነሰም በዛም በሚጠበቀው ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ ይህን ስል ሁሉም ፕሬሶች ተመሳሳይ ድክመትና ችግር ነበረባቸው ማለት አይደለም፡፡ በአንፃራዊነት የተሻለ የሚሰሩ ነበሩ፤አሁንም አሉ፡፡  
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዳይሸጋገር፣ የፖለቲካ ባህላችን እንዳያድግ በማድረግ ረገድ መገናኛ ብዙኃን፣ በተለይ ነፃው ፕሬስ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የፕሬሱ ሚና መረጃ ማቀበልና መቀበል ብቻ አልነበረም፤አጀንዳ ቀርፆ ለፖለቲካ ሀይሎች የማቀበልም ሚና ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡
አሁን የፕሬስ ውጤቶችን  ያነባሉ?
አልፎ አልፎ አነባለሁ፡፡ ግን አንዳንድ ጊዜ ጓደኞቼ ወይም በፖለቲካ ፓርቲ ዙሪያ ያሉ ሰዎች እንዲህ አይነት ፅሁፍ ወጥቷል አንብብ ቢሉኝ እመርጣለሁ፡፡ እንደ በፊቱ ሰፊ ጊዜ ወስጄ አላነብም፡፡ መፅሀፌ ላይ እንደገለፅኩት፣ እኔን ጨምሮ አብዛኞቻችን፣የፖለቲካ አስተሳሰባችን የተቀረፀው ኢህአዴግ እንደገባ በነበሩት የግል ፕሬሶች ነው፡፡ ያኔ ሁሉንም ትክክል ነው ብሎ የመውሰድ አዝማሚያ ነበረኝ፤  ትክክል እንዳልሆነ የተማርኩት በሂደት ነው፡፡
 በፖለቲካ እንቅስቃሴው ውስጥ “ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?” ያስባልዎት የተለየ ክስተት ምንድነው?
አሉባልታ በዚህ መጠን ችግርና ተፅዕኖ ይፈጥራል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ የተወሩብኝ ነገሮች እውነት እንዳልሆኑ እየታወቀና እየታየ እንኳን አልቆመም  ነበር፡፡ የተወራው ነገር ውሸት ለመሆኑ አንደኛ ምስክር ቅንጅት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ናቸው። አንዳቸውም ግን ምንም አላሉም፡፡ ህብረተሰቡም ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል አለማለቱ ይገርመኝና ያስደነግጠኝ ነበር። አሉባልታ አገር እንደሚያፈርስ ሩዋንዳ ላይ አይተናል፡፡ አሉባልታ አሁንም  በአገር ደረጃ የሚያሳስበኝ ነገር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ወደ ፖለቲካ ሲገቡ የሚያስቡት ችግር የመታሰር፣ ከስራ የመባረር ወይ የሞት ጉዳይ ነው፤አሉባልታን እንደ ችግር ብዙም አይቆጥሩትም፡፡ እኔ 22 አመት በትግሉ አሳልፌያለሁ፤ እንደ አሉባልታ በትግሉ ውስጥ ከባድ ነገር የለም፡፡ ትግሉንም በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳው አሉባልታ ነው፡፡    
ኢዴፓ የፓርቲዎች ህብረት፣ ውህደት---- የመሳሰሉ ስብስቦችን ለምንድን ነው ላለመቀላቀል የወሰነው?
በማንኛውም ጉዳይ በተናጠል ከመሄድ መተባባር ይሻላል የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ ችግሩ ምንድን ነው-- ይሄ አስተሳሰብ በተለይ ወደ ፖለቲካ ስንመጣ፣ሊሰራ እንደማይችል፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ጥያቄ ማንሳት አይፈለግም። በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ወይም ትችት ማቅረብም ከፍተኛ የፖለቲካ ስህተት ተደርጎ ነው የሚታየው። መተባበር ጥሩ ሀሳብ ነው፣ ግን በተጨባጭ ጉዳዩን እንለካው ከተባለ በተቃዋሚው ውስጥ የህብረት ጥያቄ፣ ትግሉን የጠቀመ ሳይሆን በጣም የጎዳ ነው ብዬ አስባለሁ፤ ባይኖር ይሻል ነበር፡፡ የህብረት ጥያቄ ባይኖር ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን ሁለት ወይ ሶስት ጠንካራ ፓርቲዎች ተፈጥረው እናይ ነበር። የህብረት ጥያቄ ትግሉን ለማጠናከር ከፈየደው በላይ በህብረት ስም አንዳንድ ግለሰቦች የራሳቸውን የፖለቲካ ተሰሚነት ወይም ተቀባይነት ለማግኘት የሚጠቀሙበት አጀንዳ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ ህብረቱ ወይ የሚፈለግበትን አላሳካ ወይ በተናጠል የሚታገሉ ፓርቲዎች ራሳቸውን አጠናክረው እንዲያወጡ እድል አልሰጠም፡፡ እንዲያውም አንድ ጠንካራ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚችል ፓርቲ ሲፈጠር፣ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉት ነባር ፓርቲዎች፣ የዚያን ፓርቲ እንቅስቃሴ ማፈን የሚችሉበት ስልት ነው የታየው፡፡ ጉዳዩ መዘጋት የሌለበት ቢሆንም በደንብ መጤን ያለበት ነው፡፡ የእንተባበር ጥያቄ የድክመት መሸፈኛ ነው፡፡ ጠንካራ ህብረት ለመፍጠር መጀመሪያ ጠንካራ ፓርቲዎች መኖር አለባቸው፡፡ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል አንድ ላይ መቆም የሚለው አስተሳሰብም የተሳሳተ ነው፡፡ ለመተባበር የሚፈልጉ ቢያንስ መሰረታዊ ነገሮች ላይ መስማማት አለባቸው፡፡ ውህደት መፍጠር በራሱ ግብ አይደለም፡፡
ተቃዋሚዎች እርስበርሳቸው፣ እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ጋር ያላቸውን ውዝግብ እንዴት ያዩታል?
በኔ እምነት ትግሉን በጣም የሚያዳክመው በራሱ በተቃዋሚው ጎራ ያለው ችግር ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ  ስልጣኑን መልቀቅ አይፈልግም፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሩ አመለካከት የለውም፤ስለዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲዳከሙ የቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ እንደዚህ አይነት ባህርይ ያለው ገዢ ፓርቲ እንዳለ እናውቃለን፡፡ የኛ ጥንካሬ የሚለካው ይህንን ተፅዕኖ ተቋቁመን በመውጣት ነው፡፡ ልንፈትነው እንዳንችል ያደረገን የውስጥ ችግራችን ነው፡፡ ክፋቱ ግን አብዛኛው ተቃዋሚ ይህንን አያምንም፤ ሁልጊዜ በውስጡ ያለውን ችግር ውጫዊ አድርጎ ነው የሚያቀርበው፡፡ ከምንሰራው ድርጅታዊ ስራ ይልቅ ትኩረት የምንሰጠው ለፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ራሳችንን የመገምገም ባህርይ የለንም፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አሰራር ነው የምንከተለው፡፡ ገዢው ፓርቲ ለኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲን አላመጣም እንጂ ራሱን በደንብ የሚገመግምበት ዲሞክራሲያዊ አሰራር አለው፡፡ ኢህአዴግ እያዳከመን ነው ሲባል ዞሮ ዞሮ የራስን ድክመት መናገር ነው፡፡ ችግሩ ከውጫዊው ይልቅ ውስጣዊ ነው፡፡ ራሳችንን እንገምግም ስትይ፣ ለኢህአዴግ ጥቅም እየሰራሽ እንደሆነ ይቆጠራል፡፡
በዘንድሮ ምርጫ ይወዳደራሉ?
ፓርቲዬ ይወዳደራል፣እኔ አልወዳደርም፡፡
 ከግንቦቱ አገራዊ ምርጫ ምን ይጠብቃሉ?
ተቃዋሚው ያለበትን ሁኔታና የኢህአዴግን አካሄድ ሳየው፣ ካለፈው ምርጫ የተለየ ውጤት ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ምርጫውን በራሱ ቁጥጥር ስር አድሮጎ እንደቀጠለ ነው፣ ተቃዋሚው ጎራም ካለፉት ስህተቶቹና ችግሮቹ ተምሮ ራሱን አጠናክሮ የተሻለ ውጤት ለመያዝ የሚያደርገው ነገር ብዙም የለም፡፡ ድፍረት አይሁንብኝና ተቃዋሚው ጎራ ያለችውን አንድ መቀመጫ አስጠብቆ ይቀጥላል ወይ የሚለው ያሳስበኛል፡፡ ሂደቱ መቀጠል ስላለበት ተሳትፎ ማድረጉ አስፈላጊ ቢሆንም በዚህ ምርጫ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ አንድ የተሻለ ደረጃ ላይ የሚያደርስ ውጤት አልጠብቅም፡፡ ይህ የግል ግምቴ ነው፣ ውጤቱን እናያለን፡፡
በመጀመሪያዎቹ የትግል አመታት በጎጃምና ወሎ አዋሳኝ ቦታ ላይ ተጀምሯል የተባለ የትጥቅ ትግል ለማየት ወደ ገጠር ሄደው እንደነበር በመጽሃፉ ገልጸዋል፡፡ የትጥቅ ትግል ለመጀመር አስበው ነበር?
ብዙ ሰዎች ባለፈ ታሪካቸውና አስተሳሰባቸው ያፍሩ ይሆናል፤ እኔ በግልፅ ነው ያስቀመጥኩት። በወቅቱ ያን አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲኖረኝ የቀረፀኝ ሁኔታ ነበር፡፡
ትግሉን በተቀላቀልኩ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወይም አራት አመታት የነበረኝ አስተሳሰብ በጣም አውዳሚ ነበር፡፡ በስልት ደረጃ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በማንኛውም መንገድ መወገድ አለበት ብዬ ነበር የማምነው፡፡ ይህን መንግስት ከስልጣን ለማውረድ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነበርኩ፡፡
የወጣቶች ካውንስል አባል በነበርኩበት ወቅት ራስን አቃጥሎ በስርአቱ ላይ ያለውን ብሶት በማሳየት፣ ህዝቡን ማነሳሳት ይቻላል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡
ከነፍሰገዳይ ጋር የትጥቅ ትግል አለ በሚል የሄድኩትም በዚያ ምክንያት ነበር፡፡ አሁን ላይ ሳየው ስህተት ቢሆንም ተምሬበት ያለፍኩበት ነው፤ እኔ ይህን ያደረግሁት ከአስራ አምስት አመት በፊት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰላሳ እና አርባ አመት አሳልፈው፣እኔ ከዛሬ 15 አመት በፊት የነበረኝ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ይህ በጣም የሚያስገርም ነው፡፡  

Read 8472 times