Saturday, 31 January 2015 12:44

“ለራሷ እግሯ መቅረጫ የተፋው እርሳስ የመሰለ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በቀደም አንድ መዝናኛ ቦታ ስለሆነች ልጅ ያወሩ የነበሩ ወዳጆች በምን ይጣላሉ መሰላችሁ…ቆንጆ ነች፣ ቀንጆ አይደለችም በሚል! በጨዋታና መበሻሸቅ መልክ የተጀመረው ጨዋታ ወደ ስድብ ተለወጠ፡፡ ምን አይነት ዘመን ላይ እንደተደረሰ አያሳዝናችሁም! የምንጣላበት አጣንና ደግሞ “እከሊት ቆንጆ ነች! ቆንጆ አይደለችም! በሚል ‘ጦር እንማዘዝ’! ኮሚክ እኮ ነው…እንቅፋት ‘ከመታን ድንጋይ ጋር ወደምንራበሽበት’ ዘመን እየደረስን ይመስላል፡፡ ከዚህ ይሰውረንማ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የቁንጅናን ነገር ካነሳን አይቀር…እዚህ አገር ቀደም ሲል የነበሩት ‘የውበት መለኪያዎች’ በማን ነው የተለወጡት? አሀ…ግራ ገባና! ድሮ…  “ውይ ይቺ ምስኪን ስታሳዝን! በልታ የምታድር አትመስልም እኮ!” ይባል የነበረው ሁሉ… አሁን ልጄ ‘የጨዋታው ህግ’ ተለውጧል፡፡ በርበሬና ሚጥሚጣ ‘የሚወደው’ የሀበሻ ልጅ የውበት መለኪያ ተለወጠና…አለ አይደል…“እንዴት ስሊም እንደሆነች አይተሀታል! ሞዴል ነው እኮ የምትመስለው!” መባል ተጀምሯል፡፡
በፊት እኮ ውበት ማለት… “ሞላ ያለ ዳሌ፣ ሞንደል ያለ ባት…” ምናምን ነገር ነበር። አለ አይደል… የእንትናዬ ዳሌ እንደ ድሮዎቹ የአሜሪካ ‘ቴክሶች’ በግራና በቀኝ ሁለት ሽጉጥ የታጠቀች ካላስመሰላት ማን ዘወር ብሎ ሲያይ! ያኔ ኮሌስተሮል የለ፣ ቅብጥርስዮ የለ…‘ሞላ’ ማለት የሚያሸልልበት ዘመን ነበር፡፡
እናላችሁ…እንደው ቀጠን ያለች እንትናዬ ከታየች…ከንፈር እየተመጠጠ “ምነው እንዲህ ጭር አልሽ! የሚያምሽ ነገር አለ እንዴ!” እኮ ምናምን ነገር ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ቀጠን ያለች እንትናዬ ከታየች… “ጂም ገባሁ እንዳትይ! ስታምሪ! ለምን ሞዴል አትሆኝም!” ምናምን ይባላል፡፡ ታዲያላችሁ…ዘንድሮ የ‘ስሊምነት’ ዘመን መጣና እንትናዬዎቹ ሁሉ አንድ ይሁኑ! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንዳንድ እንትናዬዎችን ታዩና የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎች ‘ወዴት እንደገቡ’ ሁሉ ይጠፋችኋል (ለልማት ተብሎ ካልተነሱ በስተቀር! ቂ…ቂ…ቂ…) ታዲያላችሁ… ዘንድሮ እንትናዬዎቹን በተርታ ሆነው ራቅ ብላችሁ ስታዩዋቸው አለ አይደል… በሁለት ጦሰኛ አገሮች መሀል የተተከለ የአጠና አጥር ሊመስሉ ይችላላ!
እኔ የምለው እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ስሙኝማ…ነገሬ ብላችሁልኛል…ከተማ ውስጥ ብዙ ቦታ የሆነ ግርግር የሚመሳስል ነገር አታጡም፡፡ ብቻ ትንሽ ነገር ስናይ መክበብ ለመደብንሳ! ጫማ ጠራጊዎች በሆነ ነገር ሲጣሉ እንከባለን፡ መኪኖች ተጋጭተው ሾፌሮች እንካ ስላንትያ ምናምን ሲባባሉ እንከባለን፡፡  ብቻ የሆነ የተበላሸ ነገር አለ፡፡ ለምንድነው ሰዉ ሁሉ ሰከን ብሎ ከመነጋገር… አለ አይደል… “ሦስት ቀን ክፍቱን ያደረ ሊጥ እንዳላስመስልህ!” አይነት ነገር ውስጥ የሚገባው! ለምንድነው በትንሹም፣ በትልቁም ጠብ፣ ጠብ የሚለን! አንዳንዴ … ኑሮ ራሱ የሌለ የጠበኝነት ባህሪይ አምጥቶ የከመረብን አይመስላችሁም!
ጥያቄ አለን…የጂም ቁጥር ይቀንስልን፡፡ ልክ ነዋ…አንድ ሳምንት ብረት ገፍቶ በሁለተኛው ክንዱን የሚነቀስ፣ በሦስተኛው መጋንጭሌ ካላጣመምኩ የሚል በዛብና!
የምር አስቸጋሪ ነው… በጂም ያበጠውም፣ በጂን ያበጠውም…ቡራከረዩ የሚል ሲበዛ አስቸጋሪ ነው፡፡
ምነው መቻቻል አቃተንሳ! ሁሉንም ነገር ለእኛ እንዲስማማ ልናገኘው አንችልም፡፡ ደግሞላችሁ…ከግርግር ጠብ ሌላ የጥላቻ ንግግር በዝቷል፡፡ ሚዲያ ላይ ፊት ለፊት ከሚነገረው ውጪ በተዘዋዋሪም የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮች በዝተዋል፡፡
እናማ…የጥላቻ ንግግሮችን የሚያስወግድ ሶፍትዌር ምናምን አንድዬ ካልፈጠረልን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
ፊት ለፊት የጥላቻ ንግግሮች አሉ፡፡ ገራገር ሀሳብ እየመሰሉ የሚቀርቡ የጥላቻ ንግግሮች አሉ፡፡ እናማ…የጥላቻ ንግግርን ከሌላው መለየት ካልተቻለ የአንዳንዶቻችን አያያዝ ደስ አይልም፡፡
ለምሳሌ የሆነ ሰው ከሆነች እንትናዬ ጋር ….ማለት ፈልጎ ለጓደኛው ያማክረዋል፡፡
“ስማ እንትናን ታውቃት የለ!”
“እንትና…እንትና…ማን ናት እሷ?”
“ይቺ ከወፍጮ ቤቱ በላይ…”
“እ!…እሷንማ አወቃታለሁ፡፡ ምን ሆነች?
“ምንም አልሆነች፡፡ በቃ… ቅዳሜ ‘ዴት አለን። ‘የቁርጥ ቀን ዘመቻ’ ምናምን ታውቅ የለ!”
“እኮ ያቺ ሲንቢሮዋ…”
“አንተ ሁልጊዜ አቃቂር ማውጣት ትወዳለህ። እኔ እኮ እንዴት ‘ሀንድል’ እንደማደርጋት ታማክረኛለህ ብዬ ነው እንጂ…”
አሁን እንግዲህ ጓደኛ ሆዬ የጥላቻና የምክር ንግግርን ካልለየ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
“እሺ ልምከርህ…ቢያንስ፣ ቢያንስ አጫጭር ቀሚስ እንዳትለብስ ንገራት፡፡ አያምርባትም፡፡”  
ይሄ ‘ምክር’ ሊባል ይችላል፡፡
“እሷን! እሷን! እንደው ምን አይተህባት ነው… ለራሷ እግሯ መቅረጫ የተፋው እርሳስ የመሰለ!”  ይሄ ደግሞ ‘ጥላቻ’ ሊባል ይችላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን መቼም ነገረ ሥራችን ሁሉ መላ የጠፋብን ይመስላል፡፡
በ‘ቦተሊካው’ ሆነ፣ በሥራ ግንኙነት ሆነ፣ በማህበራዊ ግንኙነት ሆነ… “ቢያንስ አጭር ቀሚስ እንዳትለብስ ንገራት!” ከሚል ‘ምክር’ ይልቅ… “ለራሷ እግሯ መቅረጫ የተፋው እርሳስ የመሰለ…” ይሄ ‘የጥላቻ’ ንግግር እየበዛ ነው፡፡
በቀደም ዕለት የሆነ ሠርግ ቤት ቅልጥ ያለ ጠብ እንደነበር በሬደዮ ስንሰማ ነበር፡፡ አያስገርምም!  የፈለገ ነገር ይሁን በሰው ሠርግ ሄዶ ረብሻ ማንሳት ምን የሚሉት ነው! ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም የሆነ ነገር እየተበላሸ እንደሆነ ያሳያል፡፡
ደግሞላችሁ…በሰሞኑ በዓላት ላይም አንዳንድ ቦታ ለደስታ ብለው በወጡት መሀል ጠብ ነበር ሲባል ሰምተናል፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ድሮ ብይ፣ ጠጠር ምናምን ስንጫወት…አለ አይደል… ተሸናፊ ሁልጊዜ አሸናፊን ‘እንኮኮ’ ይሸከማል፡፡ (የሰው ልጅ ታሪክ እንዲሁ ነው…የእንኮኮ አድራጊና ተደራጊ ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው…አንድ ጥያቄ አለን፡ ዘንድሮ መቻቻል የሚባለው አንዱ እንኮኮ አድራጊ አንዱ ተፈናጣጭ መሆን ነው እንዴ! አዬ…ግራ ስለገባን ነው፡፡
ስለ ትዳር ካነሳን አይቀር…እንግዲህ የሙሽሪት እናቶች ልጆቻቸው ሲያገቡ ያለቅሱ የለ፡፡ ለምን መሰላችሁ…የሚያለቅሱት… “አምላኬ፣ ብቻ የአባቷን አይነት ባል እንዳትሰጣት!” ብለው እየተላመመኑ ነው የሚያለቅሱት አሉ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ይችኛዋን ኮሚክ ነገር ስሙኝማ…አንዲት ሴት በፍቅር የተሞላ ህይወት የሚያደርጉት አምስቱ ምስጢራት የሚከተሉት ናቸው፡፡
ማብሰል፣ ዕቃዎችን ማጠብና የቤት ሥራዎች የሚሠራ ወንድ ፈልጊ፡፡
የሚያስቅሽ ሰው ፈልጊ፡፡
ታማኝ፣ እምነት የሚጣልበት፣ ጨዋና ልጆችን የሚወድ ወንድ ፈልጊ፡፡
ጥሩ አፈቃሪና የምተፈልጊውን ሁሉ የሚፈጽምልሽ ወንድ ፈልጊ፡፡
እነኚህ አራት ወንዶች በምንም አይነት እንዳይገናኙ አድርጊ፡፡
ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ! እነኚህ ሁሉ ክህሎቶች አንድ ወንድ ላይ ሊገኙ አይችሉም ለማለት ነዋ!
እናላችሁ…በሆነ ባልሆነው ጠብ ያለሽ በዳቦ ስለበዛ አንድዬ ሰከን ያድርገንማ!
“ለራሷ እግሯ መቅረጫ የተፋው እርሳስ የመሰለ…” ከመባባል የጥላቻ አነጋገርና አስተሳሰብ ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5878 times