Saturday, 31 January 2015 12:39

ሁሉም ፈረስ ላይ ከወጣ ማን ገደል ያሳያል?!

Written by 
Rate this item
(19 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አይጥ ሁሌ እንደጉድ የሚጠላው ድመት ነበር አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ህይወቱ ይረበሻል፡፡ መንፈሱ እረፍት ያጣል፡
አንድ ቀን ድንገተኛ አውሎ ንፋስ መጣ - በሀገሩ!
የትም መሄጃ ያጣው አይጥ፣ ለድመቶች ጥቃት ተጋለጠ፡፡
አይጥ እንግዲህ ወደ ከተማው ታዋቂ ጠንቋይ ሄደ፡፡ ችግሩንም አዋየው፡፡
ታላቁ ጠንቋይ ሁኔታውን በመገንዘብ፤ አይጡን ከአይጥነት ይልቅ ድመት ቢሆን ይሻለዋል፤ በሚል እሳቤ ወደ ድመት ለወጠው፡፡
ሆኖም አይጡ ወደ ድመት መለወጡ፣ ብዙ አልለወጠውም! የእንስሳት ባህሪ ሆኖበት ውሻን ክፉኛ መፍራት ጀመረ!
ይሄን ያስተዋለው አዋቂ ድመቱን ወደ ውሻ ለወጠው፡፡
ቀጠለና ያ ከድመትነት ወደ ውሻነት የተለወጠው እንስሳ፤ አሁን ደግሞ ነብርን መፍራት ተማረ!
ያ ታጋሽ አዋቂም፤ አስቦ አስተውሎ የድመቱን የመጨረሻ ደረጃ በመገንዘብና ትዕግሥት የበዛው በመሆኑ ነብር ላድርገው ብሎ ወሰነና ነብር አደረገው!
ያም ሆኖ ያ ነብር አዳኝ ቢመጣብኝስ? ብሎ ሥጋት በሥጋት ሆነ!
ይህንን ሁሉ ዕድል ሰጥቼው ካልተለወጠ የራሱ ጉዳይ ነው አለ፡፡ ከዚያም መልሶ ወደ አይጥነቱ መመለስ ዋናው ጉዳይ ነው! አለ!
ከዚያም አይጡ ወደ አይጥነት መመለሱ ግድ ሆነና ዛሬ አምነን ወደተቀበልነው አይጥ ተመለሰ!!
*   *   *
ማንነትን በማናቸውም አጋጣሚና አስገዳጅ ሁኔታ መለወጥ፣ የመርገምት ሁሉ መርገምት ነው! የትኛውንም ዓይነት ፍጡር እንሁን ብለን መከራን እናሳልፍ ብንል፤ ከተፈጥሮአችን ውጪ የረባ ፍሬ አናገኝም ወይም ልዩ ፍሬ አናተርፍም፡፡
አንድ ግብ ጋ ለመድረስ የግድ ሁለት የፍሬ ምንትነት መኖር የለበትም፤ በዚህም ሆነ በዚያ ዘመን፤ በዚህም ሆነ በዚያ ቦታና ወቅት ልናገኝ የምንችለውን ነገር በዛሬ ሽኩቻ አናክሽፈው! ከህብረት ውጩ መከፋፈል ፋይዳ የለውም፡፡
ሙግታችንና ክርክራችን ተሰብስቦ ሲታሰብ ጥቅሙ “በግልፅም መረጃ” መንፈስ ታላቅ ነው ሊባል ቢችልም፤ “ለማን እየጠቀመ ነው?” የሚባለውን አንድምታ አለማሰብ ከንቱ ቦታ ይጥለናል! የፓርቲዎች ሁሉ ውክቢያና “ጫጫታ” ስለምን በአሁኑ ወቅት ሆነ? ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ ስለማንስ ጥቅም? “ምርጫ አያስፈልግም!” ከሚል አስተሳሰብ እስከ “ምርጫ ከተሳተፍን ግልፅ አቋም፣ ግልፅ ማንነት፣ ግልፅ ውክልና ሊኖረን ይገባል!” እስከሚለው ድረስ መወያየት አለብን ማለት አገራዊ ጥያቄ ነው! ስንተዋወቅ - አንተናነቅ ድረስ ማሰብ ቢቻል ግን መልካም ነው!
የምረጡና ካርድ ውሰዱ ውትወታ ስሜት፣ የወጣት እንቅስቃሴ (በድሮው አባባል የአኢወማ ግዳጅ)፣ የሴቶች ጥያቄ፣ ድህነት ቅነሳና ልማት… ወዘተ፡፡ የእስከ ዛሬው እያንዳንዱ መንግስት ተደጋጋሚ (Replica) ነገሮች ቢመስሉም፣ ዲሞክራሲ ሂደት እንጂ ቁርጥ ክፍያ ስላልሆነ “ባመጣህበት ውሰደው” የሚለው የነጋዴ ቋንቋ የግሎባላይዜሽን አንዱ ገፅታ ነው እንለዋለን!
መተቸትንና መተቻቸትን ለማይቀበል ሥርዓት፤ ይሄን ተቀበል፣ ይሄንን አትሻ ለማለት ብዙ እንግልት እንዳለበት፣ ስለ ዲሞክራሲ ብለህ ይሄን እሻ፣ ይሄን አትሻ ብሎ አጉል እሰጣ ገባ ውስጥ መግባት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ስለዲሞክራሲ፣ ስለፍትህ፣ ስለሰብዓዊነና ህዝባዊ መብት፣ ስለሙስና አደጋ ለማውራት የተገፋው፣ የተበደለውና መብት አጣሁ የሚለው ወገን ተናጋሪ፣ ካልሆነና ብሶቱን ካላስረዳ፣ በገዢው ፓርቲስ፣ በተቃዋሚስ ወገን ማን አቤት ይላል? “ሁሉም ፈረስ ላይ ከወጣ ማን ገደል ያሳያል?” የሚለው ተረት ቁምነገሩ ይሄው ነው ጎበዝ!


Read 6759 times