Saturday, 31 January 2015 12:36

የአሜሪካ መንግስት፣ ዘጠኙ ጋዜጠኞችና ፀሐፊዎች በሽብር መከሰሳቸው አሳስቦኛል አለ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

        ባለፈው ሚያዚያ የታሰሩት ሦስት ጋዜጠኞችና ስድስት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበው የሽብር ክስ እንዲቀጥል ሰሞኑን በፍ/ቤት መፈቀዱ እንዳሳሰበው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የገለፀ ሲሆን፤ የክሱ ሂደት በግንቦቱ ምርጫ ተአማኒነትና ዲሞክራሲያዊነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል ሲል ነቀፈ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ እለት ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የፀረ ሽብር ህጉ ላይ ቀጥተኛ ትችት ባይሰነዝርም፤ የህጉ አተገባበር ግን በህገመንግስት የተረጋገጡ የፕሬስ እና የሐሳብ ነፃነቶችን የሚቃረን እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ ከዘጠኙ ጋዜጠኞችና የኢንተርኔት ፀሐፊዎች በተጨማሪ፣ ካሁን ቀደም ሌሎች ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ አንቀሳቃሾችና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችም በፀረ ሽብር ህጉ እንዲከሰሱ መደረጋቸውን የሚኒስቴሩ መግለጫ አስታውሷል፡፡
ይህም፤ የህጉ አተገባበር፣ በህገ መንግስቱ የተረጋገጡ የፕሬስና የሃሳብ ነጻነቶች ላይ ጉልህ ጥያቄዎችን አስነስቷል ብሏል፡፡
የፕሬስ፣ የሃሳብ ነጻነቶች የአንድ ዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መሰረታዊ ባህሪያት ናቸው ያለው መግለጫው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለእነዚህ ነጻነቶች መከበርና ለዲሞክራሲ ግንባታ ቁርጠኝነት እንዲያሳይ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የዘጠኙ ጋዜጠኞችና የኢንተርኔት ፀሐፊዎች የፍርድ ሂደት ፍትሃዊነትና ግልፅነት የተላበሰ፣ እንዲሁም ከአገሪቱ ህገ መንግስቱና ከአለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ጋር በማይጣረስ መልኩ እንዲካሄድም ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠይቋል፡፡ የፍርድ ሂደቱ ከፖለቲካዊ ተጽዕኖ የጸዳና ለህዝብ እይታ ክፍት እንዲሆን ማድረግ ይገባል ብሏል - መግለጫው፡፡

Read 2960 times