Saturday, 31 January 2015 12:34

የእነ አቶ በላይ ፍቃዱ ቡድን በፀጥታ ኃይሎች ከ“አንድነት” ጽ/ቤት እንዲወጣ ተደረገ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

አዲሶቹ የአንድነትና መኢአድ አመራሮች ከቀድሞዎቹ ጋር በጋራ እንሠራለን አሉ
    እውቅና የተነፈገው በእነ አቶ በላይ በፍቃዱ የሚመራው የአንድነት ፓርቲ አመራር ትናንት 8 ሰአት ላይ በፓርቲው ጽ/ቤት መግለጫ ለመስጠት ጋዜጠኞችን ጠርቶ የነበረ ቢሆንም ከመግለጫው በፊት በፀጥታ ሃይሎች ፅ/ቤቱን ለቅቆ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
“የመድብለ ፓርቲ ስርአት እንዳበቃ አረጋግጠናል” በሚል ርዕስ መግለጫ ሊሰጥ እንደነበር የጠቀሱት የቀደሞው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃ፤ መግለጫው የአንድነት አባላት ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን እንዲመራ እውቅና ለሠጠው የእነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ አመራር እውቅናና ድጋፍ እንዳይሰጡ የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡
የአመራር ቡድኑ ሠላማዊ ትግሉን በልዩ ልዩ አቅጣጫዎች ለማከናወን ማቀዱን የገለፁት አቶ አስራት፤ አዲስ ፓርቲ መመስረት አሁን የማይቻል በመሆኑ “ትግሉን ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ መልሰናል” ብለዋል፡፡ አመራሩ ቦርዱ ላይ ክስ እንደሚመሰርትም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ምርጫ ቦርድ ዕውቅና የሰጣቸው አመራሮች፤ ከቀድሞዎቹ ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ “ከእነ አቶ በላይ ጋር አብሮ ለመስራት በኛ በኩል ሙሉ ፍቃደኝነት አለ” ያሉት አቶ ትዕግስቱ፤ የተቀየረው አመራሩ ብቻ በመሆኑ የአንድነት መዋቅሩም ሆነ የአባላቱ አደረጃጀትና ተሣትፎ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ “ፓርቲው ሁለት ቦታ አልተከፈለም” ያሉት አቶ ትዕግስቱ፤ “አንድነትን ማን ይምራ? የሚለው ምላሽ በማግኘቱ ፓርቲው ወደ ምርጫው ለመግባት በተንጠቀቅ ያዘጋጃቸውን እጩዎች ያስመዘግባል ብለዋል፡፡ በእነ አቶ በላይ በፍቃዱ ቡድን ውስጥ ከነበሩት አመራሮች መካከልም በካቢኔያቸው የሚካተቱ የትግሉ ልምድ ያላቸው አመራሮች እንዳሉ አቶ ትዕግስቱ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
“አንድነትን መምራት አይችሉም” ሲል ውሣኔ ያስተላለፈባቸው የእነ አቶ በላይ ካቢኔ አባልና የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ምክትል ሃላፊ የነበሩት አቶ አስራት አብርሃ በበኩላቸው፤ በነገው እለት ሊያከናውኑ አቅደው የነበረው ሠላማዊ ሠልፍ አመራሩ እውቅና በመነፈጉ መሠረዙን ጠቁመው፤ የአቶ በላይ ስራ አስፈፃሚ በፓርቲው ጉዳይ በቀጣይ እንደሚመክር አስታውቀዋል፡፡
የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)ን እንዲመሩ እውቅና የተሠጣቸው አቶ አበባው መሃሪ፤ የፓርቲውን ጽ/ቤት ለማስመለስ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቁመው ወደ ምርጫው በመግባት ጉዳይ ላይ አመራሩና የላዕላይ ምክር ቤት ተሰብስቦ ውሣኔ ይሰጥበታል ብለዋል፡፡
በፓርቲው አመራር መካከል ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ የፓርቲው ህልውና ያሳሰባቸው ግለሰቦች ሁለቱን አካላት ለመሸምገል ጥረት አድርገው እንደነበር የጠቆሙት አቶ አበባው፤ በእነ አቶ ማሙሸት እምቢተኝነት ሊሣካ አልቻለም ብለዋል፡፡
ጥቅምት 27 ቀን 2007 ዓ.ም የተካሄደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ እነ አቶ ማሙሸት ወደ ፓርቲው ሲመለሱ የባህሪ ለውጥ ስለማድረጋቸው ለመገምገም ለሁለት አመት በተራ አባልነት በፓርቲው እንዲቀጥሉ ወስኖ እንደነበርና ኢ/ር ሃይሉ የጉባኤውን ውሣኔ ሽረው ግለሰቦቹን ወደ አመራር እንዳመጧቸው የገለፁት አቶ አበባው፣ በቀጣይ እነ አቶ ማሙሸት በጉባኤው ውሣኔ መሠረት በፓርቲው ያላቸው ተሣትፎ የተራ አባልነት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አቶ ማሙሸት አማረ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ያደረግነው የስልክ ሙከራ ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ፓርቲዎቹ በውስጣቸው ተፈጥሯል የተባለውን የአመራር ክፍፍል ችግር ቀርፈው ወደ ቦርዱ እንዲቀርቡ ለ3 ጊዜያት ያህል የጊዜ ገደብ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፤ ለሁለት ሣምንት የሰጠው የመጨረሻው የጊዜ ገደብ ባለፈው ማክሰኞ መጠናቀቁን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ሁሉም ወገኖች ችግራቸውን ለመፍታት የሄዱበትን ርቀት ገምግሞ ውሣኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡
ቦርዱ አንድነት ፓርቲን በተመለከተ ባሣለፈው ውሣኔ፣ እነ አቶ በላይ ፍቃዱ ፈጽመውታል ያለውን ግድፈት በ7 ነጥቦች ዘርዝሮ አስቀምጧል፡፡ አመራሮቹ በጠቅላላ ጉባኤ መመረጥ ሲገባቸው የምርጫ አዋጁን በመጣስ በብሄራዊ ምክር ቤት መመረጣቸው፣ ፓርቲው ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤ ለ7 ወራት ለቦርዱ ሳያሳውቅ በቦርዱ ጥያቄ ተገዶ ማቅረቡ፣ አስመራጭ ኮሚቴ ሳይሰየምና የእጩ ጥቆማ ሳይቀርብ ሚስጢራዊ ባልሆነ ድምፅ አሰጣጥ የፓርቲው ፕሬዚዳንት መመረጣቸው፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን የለቀቁበት ምክንያት ሳይመረመር ወደ ሌላ ስራ አስፈፃሚ ምርጫ መገባቱ እንዲሁም፣ በፓርቲው ደንብ ላይ ፕሬዚዳንቱ ቢለቁ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የፓርቲውን ስራ እንደሚያስቀጥል የተደነገገው ህግ መጣሱን ቦርዱ አስቀምጧል፡፡ የቦርዱን ትዕዛዝ ያለማክበርም እነ አቶ በላይ ፈፅመውታል ከተባለው ግድፈት አንዱ ነው፡፡
በሌላ በኩል እነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ፤ የምርጫ ቦርድን ትዕዛዝ ተቀብለው ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረጋቸው፣ የተጣሰው ደንብ ይከበር ማለታቸው ህጋዊ አካሄድ በመሆኑ፣ ጥር 16 ቀን 2007 ዓ.ም ያካሄዱት ጠቅላላ ጉባኤ የተሟላና ፕሬዚዳንቱ በሚስጥራዊ ድምፅ አሰጣጥ የተመረጠ በመሆኑ ቡድኑ ከእነ አቶ በላይ በፈቃዱ በተሻለ የምርጫ ቦርድን ትዕዛዝ አክብሮ ለመንቀሳቀስ በመሞከሩ አንድነትን እየመራ ወደ ምርጫው ይግባ ተብሏል፡፡
መኢአድን በተመለከተ ቦርዱ ባሳለፈው ውሳኔ ጥቅምት 28-30 ቀን 2007 ዓ.ም በተከናወነው ጠቅላላ ጉባኤ ተመርጠናል የሚሉት እነ አቶ ማሙሸት አማረ፤ በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት መዋጮ አለማዋጣታቸው፣ ከፓርቲው የተሰረዙ በመሆኑ የኃላፊነት መስፈርት አለማሟላታቸው፣ የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ በህጋዊ  ማህተም አረጋግጠው ለቦርዱ ባለማቅረባቸውና ህገ ወጥ ማህተም ማስቀረፃቸው እንዲሁም የፓርቲው አመራር ማንነት እስኪያስቸግር ድረስ ኢ/ር ኃይሉ ሻወል፣ አቶ አበባው መሃሪ እና አቶ ማሙሸት አማረ ያለ ቦርዱ እውቅና መፈራረቃቸው የህግ ጥሰት ነው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል አቶ አበባው መሃሪ የተመረጡበት የ2005 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ መስፈርቶችን ያሟላ በመሆኑ፣ ቦርዱ አቶ አበባው ፓርቲውን እየመሩ ወደ ምርጫው ይግቡ ሲል ወስኗል፡፡
የቦርዱ ውሳኔ በንባብ ከተሰማ በኋላ አንድ ጋዜጠኛ ብቻ ጥያቄ እንዲያቀርብ እድል የተሰጠ ሲሆን የቪኦኤው ጋዜጠኛ መለስካቸው አመሀ “አቶ ትዕግስቱ የተመረጡበት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተገኙት ጉባኤተኞች የፓርቲው አባላት መሆናቸውን ቦርዱ ሊያረጋግጥልን ይችላል?” የሚል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና፤ “በአጠቃላይ ግድፈቶች በሁለቱም ተፈፅመዋል፡፡ የታዩትን ግድፈቶች ደረጃ ነው ቦርዱ ያመዛዘነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የታየው የፓርቲው ህልውና የሚቀጥልበት ሁኔታ ነው፤ ስለዚህ አነስተኛ ግድፈት የፈፀመውና ከቦርዱ ጋር ጤናማ ግንኙነት ያለው፣ ቦርዱ ትዕዛዝ ሲሰጥ ለቦርዱ ትዕዛዝ የሚገዛ፣ የቦርዱን ገለልተኛነት ተቀብሎ የሚያከብረው ነው እውቅና የተሰጠው እንጂ በሁለቱም በኩል ግድፈቶች የሉም ማለት አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

Read 6886 times