Saturday, 31 January 2015 12:34

የማረሚያ ቤት ፖሊሶች በከፍተኛው ፍ/ቤት የመጸዳጃ ቤት የንፅህና ችግር ተማረዋል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

      ዋናው መፀዳጃ ቤት በመፍረሱና በአጠቃቀም ችግር የተከሰተ ነው (የፍ/ቤቱ ፕሬዚዳንት)
      ልደታ አካባቢ የሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመፀዳጃ ቤት የንፅህና ችግር እንዳማረራቸውና ለበሽታ እንደዳረጋቸው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የታራሚ አጃቢ ፖሊሶች ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ ላለፉት ሶስት ዓመታት አቤቱታ አቅርበው እስካሁን መፍትሄ አለመገኘቱ አሳዝኖናል ብለዋል ፖሊሶች፡፡
የከፍተኛው ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ውብሸት ሽፈራው በበኩላቸው፤ በባቡር መንገድ ዝርጋታው ምክንያት ዋናው መፀዳጃ ቤት በመፍረሱ የታራሚዎች ማረፊያ አጠገብ ያለው አነስተኛና ጊዜያዊ መፀዳጃ ቤት መገንባቱን አስታውሰው፣ የተጠቃሚው ቁጥር ከመጸዳጃ ቤቱ ጋር ባለመመጣጠኑና በአጠቃቀም ጉድለት ችግሩ ሊከሰት መቻሉን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ የመጸዳጃ ቤት የፅዳት ችግር ብቻ ሳይሆን እጥረትም እንዳለ በፍ/ቤቱ ግቢ ውስጥ ያነጋገርናቸው ባለጉዳዮች ገልፀውልናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በግቢው ውስጥ ካፍቴሪያ ባለመኖሩ ጠዋት ፍ/ቤት  መጥቶ ለከሰዓት የተቀጠረ ባለጉዳይ አረፍ ብሎ የሚጠብቅበት ስለማያገኝ ለእንግልት እንደሚዳረግ ባለጉዳዮች ይናገራሉ፡፡
 “ላለፉት ሶስት ዓመታት ቢያንስ በሁለት ቀን አንዴ ታራሚዎችን ወደ ፍ/ቤት ይዤ እመጣለሁ” ያለው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ፖሊስ፤ በዚህም ሳቢያ ለአስም በሽታ መዳረጉን ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ ከመፀዳጃ ቤቱ ፊት ለፊት በገንዳ መልክ የተሰራው የወንዶች ሽንት ቤት እስከ አፉ ድረስ በሽንት የተሞላ ሲሆን ሽታው የሚሰነጥፍጥ እንደሆነ በአካል ተገኝተን ታዝበናል፡፡ በሁኔታው የተማረሩት የታራሚዎች አጃቢ ፖሊሶች ችግሩ እንደማይቀረፍ እናውቀዋለን ይላሉ፡፡ ለየትኛውም ሚዲያ ብንናገር ችግሩ እንደማይቀረፍ ብናውቅም ከመናገር ግን ወደ ኋላ አንልም ያሉት ፖሊሶቹ፤ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ታራሚዎችም የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኗል የምትለው የፍ/ቤቱ የፅዳት ሰራተኛ፤ በተለይ የውሃ እጥረት ለፅዳት ሰራተኞችም ሆነ ለተጠቃሚው ትልቅ ፈተና እንደሆነ በመጥቀስ አስቸኳይ እልባት ያሻዋል ብላለች፡፡
የፍ/ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ውብሸት ሽፈራው በበኩላቸው፤ የችግሩን ስፋት ግምት ውስጥ በማስገባት ፍ/ቤቱ ካሉት ቋሚ የፅዳት ሰራተኞች በተጨማሪ ጊዜያዊ ሰራተኞችን በመቅጠር የፅዳት ስራው ሳይቋረጥ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ በአጠቃቀም ችግርና በተጠቃሚው ብዛት የተነሳ መጸዳጃው ቶሎ ቶሎ እንደሚሞላና የውሃ እጥረቱ ተደምሮ ችግሩን እንዳባባሰው ገልፀዋል፡፡ ሆኖም እነዚህ ችግሮች በቅርቡ መፍትሄ ያገኛሉ ይላሉ - ፕሬዚዳንቱ፡፡ በፍ/ቤቱ ዋናው ህንፃ ስር አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ ከ16 በላይ መቀመጫ ያላቸው መፀዳጃ ቤቶች መኖራቸውን  ጠቁመው፤ እነዚህ መፀዳጃ ቤቶች በቀን ከ400 እስከ 500 ሰው ማስተናገድ እንደሚችሉ፣ አስፈላጊው ጥገናም እንደተደረገላቸውና በቅርቡ ስራ ሲጀምሩ ችግሩ እንደሚፈታ አስረድተዋል፡፡ የውሃ እጥረቱንም ለመቅረፍ ሮቶ የውሃ ታንከሮች ግዢ ለመፈጸም ጨረታ እንደወጣ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የካፍቴሪያውን ጉዳይ በተመለከተም ጨረታ ወጥቶ ውል ለመፈራረም በዝግጅት ላይ እንደሆነ የጠቆሙት የፍ/ቤቱ ፕሬዚዳንት፣ ካፍቴሪያው በቅርቡ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ገልፀዋል፡፡

Read 2264 times