Saturday, 31 January 2015 12:32

ጋዜጠኞችና ጦማሪያኑ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ማክሰኞ መስጠት ይጀምራሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ከሚያዚያ ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ሶስቱ ጋዜጠኞችና ስድስቱ ጦማሪያን የፊታችን ማክሰኞ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት ይጀምራሉ፡፡ ፍ/ቤቱ ከዚህ ቀደም አቃቤ ህግ እንዲያሻሽል ካዘዘው አራት ክሶች ውስጥ ባለፈው ረቡዕ ሶስቱን ሲቀበል፣ የተጠርጣሪዎቹን የስራ ክፍፍል በተመለከተ አቃቤ ህግ አሻሽሎ ያቀረበውን ክስ ፍ/ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት፤ አቃቤ ህግ አሻሽል የተባለውን አራት ክሶች ያሻሻለው በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለባለፈው ረቡዕ ቀጠሮ መያዙ የሚታወስ ሲሆን የአቃቤ ህግን የክስ ማሻሻል ሂደት መርምሮ ሶስቱን ሲቀበል አንዱን ውድቅ ማድረጉን ፍ/ቤቱ ገልፆ፤ ተከሳሾች በእለቱ የእምነት ክህደት ቃል መስጠት ይችሉ እንደሆነ ጠይቋል፡፡
የፍ/ቤቱ ጥያቄ ድንገተኛ የሆነባቸው ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው በጉዳዩ መክረንበት ከሰዓት በኋላ እንገናኝ በማለት ለፍ/ቤቱ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ሆኖም ከሰዓት በኋላ የተከሳሽ ጠበቆች ጉዳዩን በውል ለማጤን በቂ ጊዜና ምቹ ቦታ አለማግኘታቸውን፣ የ9ኛ ተከሳሽ የጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ ጠበቃ ችሎት የቀረቡት በዚያን ሰዓት በመሆኑ ዝግጁ አለመሆናቸውን፣ ሌላ አንድ ጠበቃም በደረሰባቸው የመኪና አደጋ የተነሳ በችሎት ባለመገኘታቸውና በተያያዥ ምክንያቶች ከደንበኞቻቸው ጋር መመካከር ባለመቻላቸው ፍ/ቤቱ አጭር ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍ/ቤቱም ጠበቆችና ተከሳሾች ያቀረቡትን ምክንያት ካደመጠ በኋላ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ለፊታችን ማክሰኞ ሶስት ሰዓት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 1579 times