Saturday, 31 January 2015 12:28

የመከላከያ ሠራዊት ቀን ከዛሬ ጀምሮ በባህር ዳር ይከበራል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

      የዘንድሮው የኢፌድሪ የመከላከያ ሠራዊት ቀን በብሔራዊ ደረጃ በምዕራብ እዝ ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም የሚከበር ሲሆን የመክፈቻና የማጠቃለያ ስነስርዓቱ በባህር ዳር ይከናወናል ተብሏል፡፡
ለ3ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በእዝ ደረጃ የሚከበር መሆኑን የጠቀሱት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሣ; በዋናነት ከየካቲት 1 እስከ 6 ቀን 2007 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ የሠራዊቱን ተግባራት የሚዘክሩ ኤግዚቢሽኖች በማቅረብ የሚከበር ሲሆን የማጠቃለያ በአሉም የካቲት 7 በድምቀት ይከበራል ብለዋል፡፡  የዘንድሮው በአል “ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን ከዘመኑ ጋር እየታደስን ተመራጭ የሰላም ሃይል ሆነን እንቀጥላለን” በሚል መርህ የሚከበር ሲሆን መሪ ቃሉም ሠራዊቱ የቴክኖሎጂ ለውጥ ማዕከል መሆን ህዝባዊ መሠረት ይዞ በአለማቀፍ ደረጃ በሠላም ማስከበር ያለውን ተመራጭነት አጠናክሮ ይቀጥላል የሚለውን መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ቀንን ማክበር ያስፈለገበትን ምክንያት ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ ሠራዊቱ ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለማስከበር ያለውን ዝግጁነት ለማረጋገጥ፣ ሠራዊቱ እርስበእርሱ ያለውን ዲሞክራሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንዲሁም የሠማዕታትን ክብር ለማስጠበቅና እነሱን ለመዘከር በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ህብረተሰቡ በየአካባቢው ከሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር በጋራ በአሉን በድምቀት እንዲያከብርና ለሠራዊቱ ተገቢውን ክብርና ምስጋና እንዲያቀርብ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

Read 1680 times