Saturday, 31 January 2015 12:28

የ“ዳሽን አርት አዋርድ” 500ሺ ብር ገደማ ለአሸናፊዎች ያከፋፍላል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)
  • የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሽልማቱን አወድሰዋል
  • በግጥምና በስዕል 1ኛ የወጡ 100ሺ ብር ይሸለማሉ

    ዳሸን ቢራ የአገሪቱን የኪነ ጥበብ ዘርፍ ለማሳደግ ያግዛል በሚል ያዘጋጀው የኪነ ጥበባት ውድድር ሽልማት (Dashen Arts Award) ግማሽ ሚሊዮን ብር በነገው ዕለት ለአሸናፊዎች ያከፋፍላል፡፡ በግጥምና በስዕል ዘርፍ ከ1-3  የወጡ ተወዳዳሪዎች ከ100 ሺ ብር እስከ 50 ሺ ብር ይሸለማሉ ተብሏል፡፡
በግጥም፣ በስዕልና ቅርፃ ቅርፅ ሲካሄድ በቆየው ውድድር 356 ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ሰዓሊያንና ቀራ    ፂያን ማኅበር፣ ከዜማ ብዕር ሴቶች የሥነ-ፅሑፍ ማኅበርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጥበባት ኮሌጅ የተውጣጡ ዳኞች በሰጡት ዳኝነት ያሸነፉ ተወዳዳሪዎች ነገ ከ10 ሰዓት ጀምሮ በሚሌኒየም አዳራሽ እንደሚሸለሙ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በግጥም ዘርፍ ከተወዳደሩት 157 ተሳታፊዎች መካከል 29 ተወዳዳሪዎች በስራቸው ብቃት ተመርጠው፣ ከእነዚህ ውስጥ ሦስት አሸናፊዎች የታወቁ ሲሆን 1ኛ የወጣው ተወዳዳሪ 100ሺ ብር፣ 2ኛ የሆነው 75ሺ ብር፣ 3ኛ ደረጃ ያገኘው 50 ሺ ብር ይሸለማሉ፡፡
በሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ 198 ተወዳዳሪዎች ቀርበው 10 አሸናፊዎች የተመረጡ ሲሆን፣ 1ኛ የወጣው 100 ሺ ብር፣ 2ኛው 75 ሺ ብር፣ 3ኛው 50 ሺ ብር የሚሸለሙ ሲሆን ከ4ኛ እስከ 10ኛ የወጡትም የማበረታቻ ሽልማት እንደሚያገኙ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ በሰጡት አስተያየት፤ ዳሸን ቢራ በራሱ ተነሣሽነት ስነጽሑፍን ለመደገፍ እንዲህ ያለውን ሽልማት ማዘጋጀቱ የሚያስመሰግነው መሆኑን ጠቅሰው ሌሎቹም የኩባንያውን አርአያ ሊከተሉ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ “ስነጽሑፍን እያወዳደሩ ሽልማት መስጠት በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ያበረታታል” ሲሉም አክለዋል ዶ/ር ሙሴ፡፡
ዳኞቹ ከደራሲያን ማህበርም እንደተመረጡ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ የፀሃፊዎቹ ማንነት በማይታወቅ መልኩ ስነጽሑፉ ብቻ እንዲገመገም መደረጉን ጠቅሰው፤ ፋና ወጊ የሆነው የዳሸን ቢራ የኪነጥበብና ስነጽሑፍ አጋርነት በሌሎችም ኩባንያዎች መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
የሥነፅሁፍ ምሩቁና የ “የኛ ድራማ ፀሐፊ እስክንድር ሃይሉ በበኩሉ፤ “ዳሸን ቢራ ለግጥም ዘርፍ የሰጠው ክብር፣ ከአለም የጥበብ መድረክ ሊጠፋ ለተቃረበውና በሀገራችንም የመጽሐፍት መደርደሪያ ማድመቂያ ሆኖ ለቀረው የግጥም ዘውግ ትንሣኤ ነው” ሲል አስተያየቱን ለአዲስ አድማስ ሰጥቷል፡፡
ሠአሊ ዘሪሁን የትምጌታ ደግሞ “ሽልማቱ በዚህ ዘመን እንደ እንጉዳይ የፈላውን አርቲስት ሞራል የመስጠት ፋይዳ አለው” ብለዋል፡፡ ሽልማቱ የወጣት ሰአሊያንን መንፈስ የሚያጠናክር በመሆኑ በዳሸን ቢራ ብቻ ሣይሆን በሌሎች ኩባንያዎችም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ሰአሊ ዘሪሁን፤ የሽልማት ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ ብቻ ሣይሆን ወደ ክልሎችም መስፋፋት እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡ የሽልማቱ መጠን ለተሸላሚዎች ቁምነገር ያለው መሆኑን አስተያየት ሰጪው አክለው ገልፀዋል፡፡

Read 1611 times