Saturday, 24 January 2015 13:53

የቦብ ማርሌ ሐውልት ከሁለት ወር በኋላ ይቆማል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በድምፃዊ ዘለቀ ገሰሰና በአቶ አዲስ ገሰሰ የተሰራው የታዋቂው የሬጌ አቀንቃኝ የቦብ ማርሌ ሐውልት ከሁለት ወር በኋላ በሚደረግ ታላቅ ሥነ-ስርዓት እንደሚቆም አዘጋጆቹ ገለፁ፡
ድምፃዊ ዘለቀ ገሰሰ ለአዲስ አድማስ እንደተናገረው፤ ሐውልቱ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በነበሩት አቶ አርከበ እቁባይ በተሰየመውና ገርጂ ኤምፔሪያል ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው የቦብ ማርሌ አደባባይ ላይ ለማቆም ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም የዳግማይ ትንሳኤ ዕለት በሚደረገው ታላቅ ኮንሰርትና የሀውልት ማቆም ሥነ-ስርዓት ላይ ሪታ ማርሌን ጨምሮ የቦብ ማርሌ ሁለት ልጆች እንደሚገኙና ልጆቹ በኮንሰርቱ ላይ እንደሚዘፍኑ ተገልጿል፡፡
ቀደም ሲል ሃውልቱ በሚከበረው የቦብ ማርሌ የልደት በዓል ወቅት እንዲቆም ታስቦ የነበረ መሆኑን የተናገረው ድምፃዊ ዘለቀ ገሰሰ የቦብ 70ኛ ዓመት የልደት በዓል በጃማይካ ኪንግስተን ከተማ እንዲከበር በመወሰኑና የቦብ ቤተሰቦችም ለበዓሉ ወደ ስፍራው በማምራታቸው ፕሮግራሙ ተሰርዞ ለዳግማይ ትንሳኤ እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ የቦብማርሌ 70ኛ ዓመት የልደት በዓል ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ድምፃዊው ጨምሮ ገልጿል፡፡  

Read 3172 times