Saturday, 24 January 2015 12:42

“ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የተከለከለ…”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ከረማችሁሳ!
በዓላቱ በሰላም አለፉ! በበዓላት ቀናት የሚታይብንን ፈገግታና ደስታ ለሁለም ቀናት ያድርግልንማ!
ስሙኝማ…ህዝቤ ይገለብጠው የለ እንዴ! መቼም ‘አንደኛ’ የምንወጣባቸው ነገሮች እየበዙ አይደል…ከዚህ በፊት እንዳወራነው ትንሽ ቆይቶ በ‘ሲፑም’ ዓለምን ባናስከነዳ ምን አለ በሉኝ፡፡ (“ልጆቼን የማበላው አጣሁ፡፡ ወር ላይ የምመልስልህ አንድ ሁለት መቶ ብር አበድረኝ…” የሚለው ሰው አዲስ ‘ብራንድ’ ቢራ በመጣ ቁጥር “…ተጋፍቶ የሚጠጣው ከየት አምጥቶ ነው!” ምናምን አይነት ጥያቄ መጠየቅ ትተናል፡፡ ልክ ነዋ…አይደለም እኛ ሳይንስም እኮ ገና ያልደረሰባቸው ብዙ ነገሮች አሉ!)
ይቺ ከተማ እኮ እንደ ድሮ በልደታና በአቦ ሳይሆን…ወሩን ሁሉ ‘ሲፕ’ ቤቶቹ ጢም እያሉ የሚጠጣባት ከተማ ሆናለች!
ስሙኝማ…መቼም ‘የቢራዎች ፍልሚያ’ እየተጧጧፈ ነው፡፡ (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምን አለ በሉኝ የቢራ ዋጋ ‘እንደዛኛው ዘመን’ በጠርሙስ ብር ከስሙኒ ምናምን ባይገባ፡፡ አሀ…እነኚህ አዳዲስ የሚባሉት ፋብሪካዎች ሁሉ ገበያ ሲገቡ እንዴት አድርገን ነው ያንን ሁሉ ጠጥተን የምንጨርሰው!)
አሁን፣ አሁን አብዛኞቹ ዝግጅቶች ስፖንሰር የሚደረጉትና፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የሚተላለፉት አብዛኞቹ ማስታወቂያዎች የቢራዎቹ ናቸው፡፡ እሰይ… እንኳንም ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችን እንደዚሀ ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶች በዙልንማ! ግን አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ሲበዙ… አለ አይደል…እነኚህ ነገሮች በአእምሮ ያልበሰሉት ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮች ያሳስባችኋል፡፡ አለ አይደል… ‘ቢራ መጠጣት’ አይነት ነገሮች ‘የደስታ ጥግ’ ተደርገው ሲቀርቡ ዕድሜያቸው ያልደረሱ ህጻናት አእምሮ ላይ የተሳሰቱ መደምደሚያዎች እንዳይፈጥሩ የማስታወቂያዎቹ አቀራረብ ይታሰብባቸውማ! ስልጣኔያችን በዝቶ  የሰማንያ ምናምን ዓመት አያትም፣ የዘጠኝ ዓመት የልጅ ልጅም እኩል ቁጭ ብለው እስከ እኩለ ሌሊት ቴሌቪዥን የሚያዩባት አገር መሆኗ አይረሳማ፡፡
እኔ የምለው…የቢራን ነገር ካነሳን አይቀር… ‘ከ18 ዓመት በታች የማይሸጥ’ የሚለው የሆነ ነገር የሚጎድለው አይመስላችሁም! አለ አይደል…ማተኮር ያለበት ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች… እነሱ ገዙትም ማንም ገዛው ‘መጠጣት እንደማይችሉ’ ነው፡፡ እናላችሁ…በዚህ በበዓላት ሰሞን በከተማው ብዙ ቦታዎች ያያነው ነገር ቢኖር አሥራዎቹን ያላገመሱ ልጆች ተሰብስበው ሲጠጡ ነው…ያውም አላፊ አግዳሚው እያያቸው! በቀደም ሰብሰብ ብለው ‘የሎዋን ሲገጩ’ ያየናቸው ታዳጊዎች… አለ አይደል… የሁሉም ታላቅ የሆነችው አሥራ አምስት ዓመት ቢሆናት ነው፡፡
እኔ የምለው…የዘንድሮ ወላጅ…አለ አይደል…የሆነ ‘ፈርስት አሜንድመንት’ ምናምን ነገር ያለው ይመስላል፡፡ የልጆቻቸውን ነፃነት ምናምን የሚገድብ ህግ ‘ማውጣት’ አይችሉማ! ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን…አለ አይደል…ዘንድሮ በርከት ያሉ ወላጆች በልጆቻቸው አስተዳደግ ላይ ያላቸው አዎንታዊ ተሳትፎ እየቀነሰ ነው ይባላል፡፡ በቃ… የሚበሉትና የሚጠጡት ካቀረቡላቸው፣ ካሽቀረቀሯቸው፣ ለፈለጉት ነገር ሁሉ ገንዘብ ከሰጧቸው የወላጅነት ግዴታቸውንና ኃላፊነታቸውን የተወጡ ይመስላቸዋል፡፡
ስሙኝማ…የተሳትፎ ነገር ካነሳን አይቀር…“በስፖርት ዋናው ነገር መሳተፉ ነው”… የምትባል ነገር አለች፡፡ ይሄ እንግዲህ ያኔ ስፖርት ፈረንካ በማያመጣበት ዘመን ነው፡፡ ዘንድሮ…ልጄ…ያውም በጦቢያ ኳስ… “እከሌ አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ ብር ተሸጠ…” የሚባልበት ዘመን ደረስን አይደል! (እንትና… እስቲ የእግር ኳስ ‘ኤጀንትነት’ ምናምን ሞክርማ፡፡ “ምናለ አንድዬ እንደው አንድ ጊዜ ገንዘቡን ዝርግፍ ቢያደርግልኝ…” ስትል የከረምከው ሊሳካልህ ይችላላ!)
ስሙኝማ…የእግር ኳስ ነገር ከተነሳ አንድ ግርም የሚለኝ ነገር አለ…እግር ኳስ ተጫዋቾች ሜዳ ሲገቡ ሲጸልዩ ታዩዋቸዋላችሁ፡፡ የምር…‘ለውሳኔ’ እኮ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሀ…ሁሉም… “ዛሬማ ጉድ አታደርገኝም!” እያለ የሚገባ ከሆነ ለማን ‘ሊፈረድ’ ነው፡፡
ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ገና ሜዳ ሲገባ አራት፣ አምስት ጊዜ የሚያማትበው ተጫዋች ሀያ ደቂቃ ሳይሞላ የተጋጣሚውን ተጫዋች እግር ‘ቀልጥሞ’ ቀይ ካርዱን ይከናነባል፡፡ እኔ የምለው…“እንደው ደህና አድርጌ የምቀለጥመው እግር አመቻችትሀ አቅርብልኝ…” ብለው ነው እንዴ የሚለማመኑት!
እናላችሁ…ኮሚክ ነገር እኮ ነው…ስንኮርጅ እንኳን አያምርብንም፡፡ ‘ሰለጠኑ’ ብለን እየኮረጅናቸው ያሉ አገሮች እኮ ወጣቶቻቸውን ለመከላከል መአት ‘መጠበቂያ’ ህጎች አሏቸው፡፡ ህጎች በወረቀት የሰፈሩ ብቻ ሳይሆኑ በተግባርም የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ “አሥራ ስምንት ዓመት ላልሞላቸው ታዳጊዎች መጠጥ አቅርበሀል…” ተብሎ የተጠየቀ ሰው አለ!  “ዕድሜሀ ሳይደርስ መጠጥ ስትጠጣ ተደርሶብሀል…” ተብሎ የተጠየቀ ታዳጊ አለ!
እናላችሁ…የአሥራ አምስት ዓመት ህጻናት የአስተማሪዎቻቸውን ‘የበጀት ጉድለት የሚሞሉባት’ አገር እየሆነች ነው፡፡
ለሁሉም ወላጆች በዓለም ቆንጆዎቹ ልጆች የእነሱ ልጆች ብቻ ናቸው፡፡ እናማ…የሚያጠፉት ይወደድላቸዋል፡፡ የሌላ ሰው ልጅ ሲያጠፋ ግን... አለ አይደል… “ምናለ ቢቆነጥጡት! ምናምን ይባላል፡፡ የራሳቸው ልጆች ሲያጠፉ ግን...“ቢያጠፋስ ምናለበት፣ ልጅ አይደለም እንዴ…” ምናምን ይባላል፡፡ እናማ…ዘንድሮ ነገሮችን የእኛ ልጆች ሲፈጽሟቸውና የሌሎች ልጆች ሲፈጽሟቸው የሚሰጣቸው ትርጉሞች የተለያዩ  ናቸው፡፡
ክብርና ምስጋና ልጆቻቸውን በተገቢው ስነ ስርአት ላሳደጉና ለሚያሳድጉ ወላጆች!
ስሙኝማ…መቼም በምንም ባህል ስለ አማቶች መአት ነገር ይባላል፡፡ እንደውም ከብዙ ትዳሮች መፍረስ ጀርባ ‘የአማቶች እጅ’ አለበት ይባላል፡፡ ባህር ማዶ ያሉት ወገኖቻችን ግን ከአማቶች ጋር ፍቅር የያዛቸው ነው የሚመስለው፡፡ ልክ ነዋ…ስንትና ስንት እናቶች ወልድው፣ አሳድገው፣ “ያውልህ ውሰዳት…” ብለው ሰጥተው በማረፊያቸው ጊዜ እንደገና የልጅ ልጅ “አሳድጉ…” እየተባሉ አይደል እንዴ የሚሄዱት!
የአማቶች ነገር ከተነሳ ይቺን ስሙኝማ…
ሰውየው ለጓደኛው እያማከረው ነው፡፡
“እባክህ ጭንቀት ይዞኛል፡፡”
“ምነው፣ ደህና አይደለህም እንዴ!”
“እኛ በሌለንበት አማቴን ጠላፊዎች ወሰዷት፡፡ 30,000 ዶላር ክፈሉ አሉን፡፡”
“አሀ… 30,000 ዶላር ከየት አመጣለሁ ብለህ ነው የተጨነክኸው!”
“እሱ አይደለም ያስጨነቀኝ፡፡”
“ታዲያ ምንድነው?”
“ገንዘቡን ካልከፈላችሁ መልሰን ቤት እናመጣታለን ስላሉኝ ነው፡፡”
አሪፍ አይደል! ስለ አማቶች ጭማሪ…
ባል ሆዬ ከሚስቱ ተጣልቶ ለጓደኛው እያማከረው ነው፡፡ “እናቴ ቤት እሄዳለሁ አለችኝ፡፡ እኔም… ዛቻ ነው፣ ቃል መግባትሽ ነው ብዬ ጠየቅኋት፣” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም “ምን ልዩነት አለው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ባል ሆዬ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ወደ እናቷ ተመልሳ የምትሄድ ከሆነ ይህ ቃል መግባት ማለት ነው፡፡ እናቷን እኛ ቤት የምታመጣ ከሆነ ግን ዛቻ ነው…”  አለና አረፈው፡፡
የአማቶች መብት አስጠባቂ ማህበር ነገር ይቋቋምልንማ!
እናላችሁ…ስለ ልጆች አስተዳደግ የምር መታሰብ ያለበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ስለ ልጆቹ መጻኢ ህይወትና ስለነገው ህብረተሰብም ማሰቡ መልካም ነው፡፡ ልጆችን የሚያሳስቱ ነገሮች እየተበራከቱ ባሉበት ሰዓት ወላጆች ከልጆቻቸው ትንሽ ሻል ብለው ማሰብ የሚኖርባቸው አይመስላችሁም!
ይቺን ስሙኝማ…ህጻናት ወንድምና እህት እየተጫወቱ ነው፡፡ እናማ… እህትየው ብቻ ነች የምትጮኸው፡፡ ወንድሟ ምንም ነገር አይተነፍስም፡፡ እናትየውም… “ማሚቱ፣ አንቺ ብቻ ለምን ትጮሂያለሽ! እሱም አንዳንዴ ይናገር እንጂ…” ትላታለች፡፡ ህጻኗ ምን ብትል ጥሩ ነው… “እኔ አንቺ ነኝ፣ እሱ ደግሞ አባዬ ነው…”  ብላት አረፈች፡፡ በቃ ለእሷ የእናት ሥራ አባት ላይ መጮህ፣ የአባት ሥራ ደግሞ ዝም ብሎ ማዳመጥ ሆኗላ! አባት እኮ ዝም ብሎ የሚያዳምጥ እያስመሰለ በሆዱ ይሄኔ ስንትና ስንት እርግማን አውርዶባታል! “እኔ ሚስት አገባሁ ብዬ… ለካስ ያገባሁት ምላስና ሰንበር ነው!” ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ….
እኔ የምለው…“አጅሬ፣ እያስመሰልክ የልብህን ትናገራለህ!” ያላችሁኝ ወዳጆቼ…አልገባኝም፡፡ እንዴት ነው ነገሩ…“እንደ ሰዉ አንተም ታስመስላለህ…” “አስመሳይ ነህ…” ምናምን እያላችሁኝ ከሆነ… አለ አይደል…እስቲ ‘ስታተሴን’ መለስ ብዬ አየዋለሁ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ወይ ‘ማስመሰል!’
እናማ…ልጆች ወደተሳሳተ መንገድ ከመሄድ የሚጠብቃቸው ህጎች በተግባር ላይ ይዋሉማ! “ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የተከለከለ…” የሚሉ አይነት ህጎች ‘ባዶ ቃላት’ መሆናቸው ቢበቃ አሪፍ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3578 times