Saturday, 24 January 2015 12:33

በፋናው የውይይት መድረክ ተቃዋሚዎች ምርጫ ቦርድን ተችተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)
  • አቶ አስራት ጣሴ ብለው መድረኩን ረግጠው ወጥተዋል
  • በቦርዱ ላይ የሚቀርቡ ውንጀላዎች በህግ ሊያስጠይቁ ይችላሉ ተብሏል
  • “መድረክ” የስነ ምግባር ደንቡን ልፈርም እችላለሁ ብሏል

   ፋና ብሮድካስቲንግ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ባለፈው ረቡዕ በሸራተን አዲስ ሆቴል የግንቦቱን ምርጫ አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ያልሆኑ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድን አሰራር ሲተቹ፣ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በፓርቲዎች ገንዘብ ክፍፍል ላይ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
“5ኛው ሃገራዊ አጠቃላይ ምርጫ ፍትሃዊ ዲሞክራሲያዊ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የባለድርሻ አካላት ሚና” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ኢዴፓ፣ ኢህአዴግና መድረክ የሃገሪቱን የምርጫ ሂደት የዳሰሰ ነው ያሉትን ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
በፓርቲዎቹ የቀረበው ፅሁፍ ከተጠናቀቀ በኋላ በፅሁፉ ላይ አስተያየትና ጥያቄ እንዲያቀርቡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በተጋበዙበት ወቅት የአንድነት ፓርቲ ተወካይ አቶ አስራት ጣሴ፤ በምርጫ ቦርድና በውይይቱ አዘጋጆች ላይ ያላቸውን አስተያየት ከሰነዘሩ በኋላ ፓርቲያቸው በሁለት አመራሮች መወከሉን በመቃወም ጉባኤውን ጥለው ወጥተዋል፡፡
“አሁን ያለው ምርጫ ቦርድ ፈፅሞ የኢትዮጵያን ምርጫ ማካሄድ አይችልም” ሲሉ ኃይለቃል የተናገሩት አቶ አስራት፤ ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም፣ ተአማኒነት የለውም ብለዋል፡፡ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ምርጫ ቦርድና ሬዲዮ ፋና በህጋዊ መንገድ የተመረጠን የአንድነት ፕሬዚዳንት ባለመቀበል ፓርቲውን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው ሲሉም ከሰዋል፡፡ በምርጫ ቦርድ ላይ የሰላ ትችት የሰነዘሩት አቶ አስራት፤ ምርጫን በሚያህል ጉዳይ ለምንድን ነው የምንቀልደው? በማለት ጉባኤውን ጠይቀዋል፡
በውይይት መድረኩ ላይ አስተያየት እንዲያቀርቡ እድሉ የተሰጣቸው በዲ-አፍሪክ ሆቴል ተደርጓል በተባለው የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ በፕሬዚዳንትነት መመረጣቸውን የገለፁት አቶ ትዕግስቱ አወሉ በበኩላቸው፤ አቶ አስራት የሚያከብሯቸውና የሚያደንቋቸው የትግል አጋራቸው መሆናቸውን ጠቅሰው “እኔ የተመረጥኩት በ2004 ዓ.ም በፀደቀው የፓርቲው ደንብ ነው፤ እሳቸው ያሉበት አመራር ደግሞ በ2006 ወጥቷል በተባለውና ባልፀደቀው ደንብ ነው የተመረጡት” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በአሁን ሰዓት የአንድነት ህጋዊ አመራር ነን ብለን ነው የምንቀሳቀሰው በማለት አቶ ትዕግስቱ አክለዋል፡፡
የአቶ አስራት ጣሴ ጉባኤውን አቋርጦ መውጣት በመድረኩ አዘጋጆችና በአንዳንድ ተሳታፊ ፓርቲ አመራሮች የተተቸ ሲሆን የፋና ብሮድካስቲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዱ ይመስል ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግርም፤ ጣቢያው “ለድምፅ አልባዎች ድምፅ መሆን” የሚል አላማ እንዳለው ጠቁመው፣ በዚህ መሰረት የትኛውም ሚዲያ አክብሮ ሊያስተናግዳቸው ላልፈለጋቸው ለእነ አቶ ትዕግስቱ ሃሳባቸውን የሚገልፁበትን እድል እንዳመቻቸላቸውና በቀጣይም ይህን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ሌላው በውይይት መድረኩ ላይ ጎልቶ የወጣው በቅርቡ ዘጠኝ ፓርቲዎች “ትብብር” በሚል መደራጀታቸውን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ “አደረጃጀቱን አላውቀውም፤ ህጋዊ አይደለም” ማለቱን ተከትሎ የተከሰተው ውዝግብ ሲሆን የትብብሩ አባል ፓርቲዎች ተወካዮች፤ ምርጫ ቦርድ በህግ ያልተሰጠውን ስልጣን ከየት አምጥቶ ነው ትብብሩ ህጋዊ አይደለም የሚለው? የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል - ቦርዱ በግንባር፣ በቅንጅት፣ በውህደት ደረጃ ያሉ አደረጃጀቶችን ብቻ የመቆጣጠር ስልጣን እንዳለው በመጥቀስ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፌራ በበኩላቸው፤ “በህግ ያልተከለከለ ነገር እንደተፈቀደ ይቆጠራል” የሚለው አስተሳሰብ ጥያቄውን እንደፈጠረ ጠቅሰው፣ አደረጃጀቱ በትብብር ስም መግለጫ ማውጣት፣ ደብዳቤ መፃፍ አይቻልም ነው ያልነው እንጂ ፓርቲዎች መተባበራቸው አይጠላም ብለዋል፡፡
የኢህአዴግ ተወካይ አቶ ደስታ ተስፋው በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “በኢህአዴግ አይን ትብብር አይጠላም፤ ትብብሩ ለምን አላማ ነው? የሚለው ግን አጠያያቂ ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም አቶ ደስታው ኢህአዴግ በዚህ ምርጫ በስነ ምግባር ተወዳድሮ አሸናፊ ለመሆን መዘጋጀቱን፣ ለአባላቱም ተከታታይ የስነ ምግባር ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙ አንዳንድ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ በቅርቡ በምርጫ ቦርድ ቀመር ወጥቶለት ለፓርቲዎች እንዲከፋፈል በተደረገው ገንዘብ ላይ ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረንስ ም/ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው፤ ቦርዱ ለፓርቲዎች ያከፋፈለው ገንዘብ እንደሚያንስና ለምንም ስራ ሊያውሉት እንደማይችሉ ጠቁመዋል፡፡ ለፓርቲዎች የተከፋፈለው ገንዘብ በግለሰብ ደረጃ ከ250-500 ብር ብቻ ሊደርስ የሚችል ነው ያሉት አቶ ሽፈራው፤ በዚህ ገንዘብ ምንም መንቀሳቀስ አይቻልም፣ ይታሰብበት ብለዋል፡፡ የኢትየጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፤ ምርጫውን የጋራ እናድርገው፣ ብሄራዊ መግባባት እንፍጠር ያሉ ሲሆን ሬዲዮ ፋና ይህን መሰሉን የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን አድንቀዋል፡፡ የቅንጅት ሊቀመንበር አቶ አየለ ጫሚሶም በሁሉም ፓርቲዎች መካከል መቻቻል እንዲኖርና ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ “የስነ ምግባር ደንቡን ያልፈረሙ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ለመወያየት አለመቻላቸው ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ፓርቲዎች አዋጅ ሆኖ የወጣን ህግ ፈርሙ መባላቸው ትክክል አይደለም፤ ፈርሙ ከተባለም መድረኩ እንዲስተካከል የሚፈልጋቸው አንቀፆች ከተስተካከሉ የስነ ምግባር ደንቡን እንፈርማለን” ብለዋል፡፡ በውይይቱ የተሳተፉ የጋራ ም/ቤቱ አባል ፓርቲዎች፤ መድረክና ሌሎች ፓርቲዎች ደንቡን ፈርመው እንዲቀላቀሏቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የህግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አስመላሽ ወ/ስላሴ በበኩላቸው፤ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ በምርጫ ቦርድ ላይ የሚያቀርቡት በመረጃ ያልተደገፈ ውንጀላ በህግ ሊያስጠይቃቸው እንደሚችል አሳስበዋል፡፡ “ምርጫ ቦርድ ኢህአዴግ ነው፤ የሚለው ዘመቻ በህግ የሚያስጠይቅ ነው” ብለዋል፤ አቶ አስመለሽ፡፡
“ቦርዱ ኢህአዴግ ቢሆን ኖሮ ለፓርቲዎች ከሚሰጠው ገንዘብ ላይ ኢህአዴግ ማግኘት ከነበረበት 20 በመቶ አይቀንስም ነበር” ያሉት አቶ አስመላሽ፤ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ እነዚህ ውንጀላዎች መቆም አለባቸው ብለዋል፡፡ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና በበኩላቸው፤ ቦርዱ ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ አደረጃጀት ፈጥሮ፣ ለዓለም ተሞክሮ በሚሆን ደረጃ ነፃ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት ገለልተኛ አይደለም የሚሉት ውንጀላዎች ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል፡፡ በጉባኤው ላይ መንግስትን ወክለው ሃሳባቸውን የሰነዘሩት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ እውነቱ ብላታ፤ የመወዳደሪያ ሜዳው ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል እንዲሆን መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመጠቆም በውጭ ኃይሎች ምርጫው እንዳይረበሽ በንቃት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  


Read 2933 times