Saturday, 24 January 2015 12:31

የከተማ አስተዳደሩ የነገው የ “አንድነት” ሠልፍ እውቅና የለውም ብሏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

ፓርቲው ሠልፉን ከማካሄድ ወደ ኋላ እንደማይል አስታውቋል
ፓርቲው በምርጫ ቦርድ ላይ ያቀረበው ክስ ተቀባይነት አጥቷል

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፤ ነገ ሊያካሂደው ያቀደው ሠላማዊ ሠልፍ እውቅና እንደሌለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያስታወቀ ሲሆን፤ ፓርቲው ሠልፉን ከማካሄድ ወደ ኋላ እንደማይል አስታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ እነ አቶ በላይ ፍቃዱ የሚመሩት የአንድነት ቡድን “የሠላማዊ ሠልፍ መስፈርትን ስለማያሟሉ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አላገኘም” ብለዋል፡፡ ፓርቲው ሠልፉን የሚያካሄድባቸውን ቦታዎች በአግባቡ ባለመጥቀሱና በሠልፉ ላይ የሚንፀባረቁ መፈክሮች ባለማቅረቡ ሠልፉ እውቅና ማግኘት እንደማይችል ሃላፊው ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ሌላኛው የአንድነት ፓርቲ አመራር ቡድን የእነ አቶ በላይ ቡድን ሊያካሂድ ያሰበው ሠልፍ እንዳይፈቀድ የሚጠይቅ ማመልከቻ ተፈራርመው ለአስተዳደሩ ማስገባታቸውን ሃላፊው ጠቁመው፤ በነዚህ ምክንያቶች በከተማዋ የትኛውም አካባቢ ሰልፍ ማካሄድ እንደማይቻል አስገንዝቧል፡፡
በእነ አቶ በላይ ፍቃድ የሚመራው አንድነት፤ ነገ አካሂዳለሁ ብሎ ባቀደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ፓርቲው ያልተከፋፈለና አንድ መሆኑን በመጠቆም ምርጫ ቦርድና ሚዲያዎች ፓርቲው እንደተከፋፈለ አድርገው የሚያቀርቡትን መረጃ በመቃወም አባላቱ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ሲያስተላልፍ ሰንብቷል፡
ፓርቲው ሠላማዊ ሠልፉን ለማካሄድ ያሰበው አዲስ አበባን ጨምሮ በደብረማርቆስ፣ በጂንካ እና በሸዋሮቢት ከተሞች መሆኑን የጠቆሙት የፓርቲው አመራሮች፤ በአዲስ አበባ የሚካሄደው መነሻውን ቀበና ከሚገኘው የፓርቲው ፅ/ቤት በማድረግ፣ በፒያሳ በኩል በኢትዮ ኩባ ወዳጅነት አደባባይ ላይ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ፓርቲው በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ በከፍተኛው ፍ/ቤት የፍትሃ ብሄር ክስ ባለፈው አርብ ጥር 8 ቀን 2007 መመስረቱን ያስታወቀ ቢሆንም እስከ ትናንት ድረስ ክሱን ተቀብሎ የሚያስተናግደው ችሎት ማጣቱን የፓርቲው የህግ ባለሙያ አቶ ገበየሁ ይርዳው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በቦርዱ ላይ የቀረበው የፍትሃብሄር ክስ ምርጫ ቦርድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም የተካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት እንዲቀበል፣ ጠቅላላ ጉባኤው የመረጠውን ፕሬዚዳንት ተቀብሎ እንዲያፀድቅ እንዲሁም የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ እንዲቀበል የሚጠይቅ እና ሚዲያዎች በፓርቲው ላይ በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ በሩን የከፈተው ቦርዱ በመሆኑ፣ በጉዳዩ ላይ የማስተባበያ መግለጫ እንዲያወጣና ፓርቲው ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ሲጠራ የደረሰበትን በመቶ ሺህ ብር የሚቆጠር  ኪሳራ ቦርዱ እንዲከፍል የሚጠይቅ መሆኑን ጠበቃው አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው አርብ መዝገቡን የተቀበለው ችሎት፤ ለሃሙስ ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በቀጠሮው እለት ጉዳዩን የመመልከት ስልጣን እንደሌለው ገልፆ መዝገቡን ወደ ሌላ ችሎት መምራቱን የጠቀሱት የህግ ባለሙያው አቶ ገበየሁ፤ ችሎቱ መዝገቡን እየተቀባበሉ የማየት ስልጣን የለንም የሚል ምላሽ እንደሰጧቸውና ክሱ ተቀባይነት ማጣቱን እንዳረጋገጡ አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል እነ አቶ በላይን ሲቃወሙ የነበሩትና ለብቻቸው ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው ነበር የተባሉት አቶ አየለ ስሜነህ ሃሙስ እለት ወደ ፓርቲው መመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 3685 times