Saturday, 24 January 2015 12:28

እነ አቶ ማሙሸት አማረ በምርጫ ቦርድ ላይ ክስ ለመመስረት ተዘጋጅተናል አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

         የፓርቲውን ውስጥ ችግር በሁለት ሳምንታት ውስጥ በጠቅላላ ጉባኤ እንዲፈታ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ እድል የተሰጠው መኢአድ፤ ጉባኤውን እንደማያካሂድና ቦርዱ የተዛባ ውሳኔ በመስጠት ከምርጫ የሚያስወጣው ከሆነ በፍርድ ቤት ክስ ለመመስረት መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ፓርቲው ትናንት በፅ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አሁን በፓርቲው ፅ/ቤት ሆነው እየመሩ ያሉት እነ አቶ ማሙሸት አማረ፤ በፓርቲው ደንብ መሰረትና ምርጫ ቦርድ ባረጋገጠውና አባላት በተሟሉበት ምልአተ ጉባኤ የተመረጠ በመሆኑና ይህ በድጋሚ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም በተካሄደው 2ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተረጋገጠ በመሆኑ፣ ለሶስተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ እንደማይችል ገልጿል፡፡ምርጫ ቦርድን ፍላጐት ለማሟላት በሁለት ወር ውስጥ ሁለት ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱን የጠቆሙት የፓርቲው አመራሮች፤ ቦርዱ ግን የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ የተካተተበትን ሪፖርት ተቀብሎ ውሳኔ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም ብለዋል፡፡“ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ያልተገባ አካሄዱን እንዲያስተካክል አጥብቀን እንጠይቃለን” ያለው ፓርቲው፤ ከቦርዱ ጋር በተለያየ ጊዜ የተለዋወጣቸውን የደብዳቤ መልእክቶች እንዲሁም የጠቅላላ ጉባኤውን ሰነዶችና ቦርዱ ደብዳቤዎችን አልቀበልም ማለቱን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን በመያዝ ወደ ፍርድ ቤት አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡“ቦርዱ በመኢአድ ላይ ያልተገባ ትንኮሳና ከስልጣኑ በላይ በፓርቲው ላይ አደጋ ለመፍጠር መሞከሩ ለማንም አይበጅም” ያለው ፓርቲው፤ ቦርዱ በፓርቲው የውስጥ ጉዳይ ከተሰጠው ስልጣን በላይ ጣልቃ ገብቷል ሲል ተቃውሟል፡፡የፊታችን ማክሰኞ ምርጫ ቦርድ ለመኢአድና አንድነት የሰጠው የሁለት ሳምንት የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቅ ሲሆን ምናልባት ቦርዱ አሁን ያለው አመራር ይቀጥል የሚል ውሳኔ አሳልፎ ፓርቲው ወደ ምርጫ እንዲገባ የሚፈቀድ ከሆነ፣ ወደ 334 በሚደርሱ የምርጫ ጣቢያዎች ፓርቲው እጩዎቹን ለማስመዝገብና ወደ ምርጫው በአፋጣኝ ለመግባት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀም የእነ ማሙሸት አመራር አስታውቋል፡፡በሌላ በኩል ፓርቲው በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች በአባላቱ ላይ እስርና እንግልት እየተፈፀመባቸው መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል፡፡

Read 2050 times