Saturday, 17 January 2015 11:11

በቀን 1.9 ሚ ጠርሙስ ቢራ የሚያመርተው ሄኒከን (ዋልያ) ቢራ ፋብሪካ ተመረቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(11 votes)

በቅርቡ ሄኒከን ቢራ ማምረት ይጀምራል

በዓለም ታዋቂ የሆነው ሄኒከን ቢራ ፋብሪካ ከሁለት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረውን ሄኒከን (ዋልያ) ቢራ ፋብሪካ ከትናንት በስቲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ አገልግሎት ጀመረ፡፡በአዲስ ዓመት ለሙከራ ወደ ገበያ የገባውና በቢራ ጠጪዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኘው ሄኒከን (ዋልያ) ቢራ ፋብሪካ በሰዓት በሁለት መስመር በእያንዳንዱ 40 ሺህ ወይም 80 ሺህ ጠርሙስ፣ በቀን ደግሞ ከ1.9 ሚሊዮን ጠርሙስ ቢራ በላይ እንደሚያመርት ታውቋል፡፡በአቃቂ ክፍለ ከተማ በቂሊንጦ በ343 ካ.ሜ ላይ የተሰራው ፋብሪካ ለመገንባትና ለመሳሪያዎቹ ግዢ 110 ሚ ዩሮ የወጣ ሲሆን ሄኒከን-ኢትዮጰያ በ2004 ዓ.ም የገዛቸውን የበደሌና የሐረር ቢራን እንዲሁም ዋልያን ቢራን ጨምሮ 1.5 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር (150 ሚሊዮን ቢራ ጠርሙስ) በማምረት በኢትዮጵያ ትልቁ ቢራ አምራች ፋብሪካ እንደሆነ የሄኒከን-ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚ/ር ጆሃን ዶየር ገልፀዋል፡፡
ሄኒከን-ኢትዮጵያ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ መለያው የሆነውን ሄኒከን ቢራን እንዲሁም ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ሌሎች ቢራዎች በመጥመቅ በአገሪቷ እያደገ የመጣውን የቢራ ፍላጐት እንደሚያሟላ አስታውቋል፡፡ሄኒከን-ኢትዮጵያ ለበደሌና ለሐረር ቢራ ፋብሪካዎች ግዢ እንዲሁም ለዋልያ ፋብሪካ ግንባታ በአጠቃላይ 310 ሚሊዮን ዩሮ ኢንቨስት ያደረገ ሲሆን ለ280 ዜጐችም የሥራ እድል ፈጥሯል፡
የአካባቢው ገበሬዎች የተሻሻለ የቢራ ገብስ እንዲያመርቱ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና አስፈላጊ ድጋፍ ለማድረግ ወስማማታቸውን የገለፁት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ በኢትዮጵያ ሥራ ከጀመሩ ሁለት ዓመት ብቻ ቢሆንም፣ ለ6000 ገበሬዎች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን፣ ከሁለት ዓመት በኋላ 20,000 ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸውን በመደገፍ 20,000 ሜትሪክ ቶንስ የቢራ ብቅል ገብስ ለማግኘት ማቀዳቸውን አስረድተዋል፡፡በዚሁ ጊዜ ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ባደረጉት ንግግር የውጭ ኢንቨስትመንት ፖሊሲያችን ግልፅ መሆኑን ተረድታችሁ በአገራችን መዋዕለ ንዋያችሁን ማፍሰሳችሁና የቢራ ብቅል ገብስ ለማምረት ከአካባቢው ገበሬ ጋር መስማማታችሁ የሚደነቅ ስለሆነ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፈ ሁሉ ይደረግላችኋል ብለዋል፡፡

Read 7846 times