Print this page
Saturday, 17 January 2015 11:10

ዳሽን ቢራ በቀን 300 ሚሊዮን ጠርሙስ ቢራ አመርታለሁ አለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

ዳሽን ቢራ ፋብሪካ አ.ማ በደብረ ብርሃን ከተማ እያሠራ ያለው ማስፋፊያ በቅርቡ ሥራ ሲጀምር በቀን 300 ሚሊዮን ጠርሙስ ቢራ ወይም 3 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ቢራ እንደሚያመርት የፋብሪካው ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ፡፡
 ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መክበብ ዓለሙ ዘመንፈስ በዚህ ሳምንት በጽ/ቤታቸው ስለዳሽን አርት አዋርድ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ በገበያው ውስጥ የሚታየውን የዳሽን ቢራ እጥረት ለመቅረፍ ምን እየሠሩ እንደሆነ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ በደብረብርሃን ከተማ እየተሠራ ያለው ማስፋፊያ ፋብሪካ፣ በቴክኖሎጂው በአፍሪካ የመጀመሪያውና የማምረት አቅሙም በጣም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፋብሪካው በመጪው መጋቢት ሥራ ሲጀምር በቀን 2 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር በማምረት ጀምሮ እስከ 3 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ስለሚደርስ ያኔ እጥረቱ ይቃለላል ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የቢራ ጠመቃ ልምድና እውቀት ያላቸው የቢራ ጠማቂዎች ወደ ገበያው መግባታቸውን የጠቀሱት አቶ መክብብ፤ ምርታቸውን በስፋትና በጥራት በማቅረብ፣ የደንበኞችን ፍላጐት በማወቅና በመመለስ እንዲሁም በጥሩ መስተንግዶ በአሸናፊነት ለመወጣት እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ሲጀምር ከነበረበት 200 እና 300 ፐርሰንት ዕድገት መጨመሩን የገለጹት ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ 300 ሄክቶ ሊትር በማምረት ጀምሮ ሁለት ጊዜ ባደረገው ማስፋፊያ አሁን የሚያመርተው አንድ ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ቢራ በሙሉ እንደሚሸጥ ገልፀዋል፡፡

Read 4069 times