Saturday, 17 January 2015 11:09

ስማችን ያለበት ኮካ ኮላ ለገበያ ቀርቧል

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ምሽት ብዙዎች በጉስቶ ሬስቶራንት የተደረደሩ የኮካ ኮላ ምርቶችን አተኩረው ሲመለከቱ ያስተዋለ ግር ሊሰኝ ይችላል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ሁሉም በኮካ ጠርሙሶች ላይ የሚፈልገው የራሱን ስም ነበር፡፡ ምክንያቱም ኮካ ኮላ የተለመዱ የኢትዮጵያውያን ስሞች የታተመባቸው ምርቶች ማቅረቡን ይፋ ያደረገበት ምሽት ነው፡፡
በእርግጥ ታዳሚው ሁሉ (ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተው ነበር) የየራሱን ስም አግኝቷል ማለት አይደለም፡፡ የተወሰኑ የተለመዱ ስሞች ተመርጠው ነው የታተሙት፡፡ ለዚህ ነው ብዙዎች በእልህ ስማቸውን ሲፈልጉ ያመሹት፡፡ የተወሰኑት ፈልገው አግኝተዋል፡፡ ያላገኙትም ግን መፅናኛ አላጡም፡፡
የሚስት ወይም የባል፣ የፍቅረኛ አሊያም የልጆች ወይም የዘመድ ወዳጅ ስሞች ያሉባቸው የኮካ መጠጦችን አግኝተዋል፡፡
እኔ ራሴ ስሜ ያለበት ኮካ ማግኘት ካልቻሉት መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ ሆኖም የባለቤቴ፣ የእናቴና የቅርብ ወዳጄ ስሞች ያሉባቸው ሦስት የኮካ ኮላ ምርቶችን በማግኘቴ ፈንድቄአለሁ፡፡ የበለጠ የፈነደቅሁት ደግሞ ኮካውን ለባለ ስሞቹ ሳጋራቸው ነው፡፡ኮካ የጀመረው አዲሱ የገበያ ትውውቅ ዘመቻም “Share A Coke” የሚል ነው፡፡ የኮካ ኮላ ኢትዮጵያ ብራንድ ማናጀር አቶ ምስክር ሙሉጌታ እንደተናገሩት፤ 200 የወጣቶችና 200 የአዋቂ ኢትዮጵያውያን ስሞችን በመለየት የአዋቂዎቹ ስሞች 1.5 ሊትር በሚይዘው “ከበር ቻቻ” ላይ የታተሙ ሲሆን የቀሩት 200  ስሞች ደግሞ 0.5 ሊትር በሚይዘው “ሽር-ሽር” የኮካ ጠርሙሶች ላይ ታትመዋል፡፡
በኮካ ምርት ላይ ከታተሙት ታዋቂ ስሞች መካከል “ሳባ”፣ “አበበ”፣ “ሃያት”፣ “ቦንቱ”፣ “ዊንታ”… ወዘተ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡ የግለሰብ ስሞች የሰፈሩባቸው የኮካ ምርቶች በአገር አቀፍ ደረጃ በገበያ ላይ የዋሉ ሲሆን በዋና ዋና ማከፋፈያዎች፣ በሱቆች፣ በሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ለሽያጭ እንደቀረቡ ተገልጿል፡፡
የኮካ ኮላ የገበያ ትውውቅ ዘመቻ በአህጉር ደረጃ (በመካከለኛው፣ በምስራቅ፣ በምዕራብና ደቡብ አፍሪካ) በመካሄድ ላይ ሲሆን ይሄም በገበያው ላይ በጐ ተፅእኖ እንደሚፈጥርና የኮካን “ደስታን የማጋራት” ዓለም አቀፋዊ እቅድ እንደሚያጠናክርለት ይጠበቃል ብሏል - ኩባንያው በመግለጫው፡፡ ኩባንያው እንደ ፌስ ቡክ ወይም ትዊተር ያሉ የማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዲሁም ሌሎች አሳታፊ የማስታወቂያ መድረኮችን በመጠቀም፣ ደንበኞች የመረጧቸው ስሞች እንዲታተምላቸው ማዘዝ ብቻ ሳይሆን ኮካን የመጋራት አይረሴ የደስታ ቅፅበቶች ላይ ያተኮሩ መልእክቶችን፣ ፎቶዎችን ወይም ቪዲዮዎችን እንዲጋሩ የሚያስችል መሆኑ ታውቋል፡፡


Read 4453 times