Saturday, 17 January 2015 11:03

የጉዞ ማስታወሻዬ

Written by  ነቢይ መኮንን-
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው የጀመርኩትን የጉዞ ማስታወሺያዬን የሁለተኛውን ክፍል ለማቅረብ ባለመመቸቱ ሳናከታትለው ቀርተናል፡፡
ጉዳዩ:- (1) የአሶሳ ጉዞዬን
     (2) የካይሮ ጉዞዬን ማቅረብ ነው፡፡ ተያያዥነት ያላቸው ሁለት ጉዳዮች ናቸው፡፡
አንዳንዴ ውጤቱ ከምክንያቱ ይቀድምና ብዕርን ያነቃዋል፡፡ ጊዜና ድርጊት እንዳይጣረስ Anachronistic እንዳይሆን ያለኝ ሥጋት እንደተጠበቀ ሆኖ ሦስተኛው ጉዳይ የመነጨው እንዲህ ነው፡፡  
      (3) ከካይሮ መልስ  ለካይሮው ልዑክ ዶ/ር አሸብር የምሣ ግብዣ ማድረጋቸውና የጉዳዩ ፍሬ - ነገር ምን ነበር? (ይሄ እጅግ የቀረበው ጉዳይ ነውና ከመነሻዬ በጣም እንዳይርቅ በመስጋት፤ ለዛሬ መግቢያዬ ላርገውና (ልክ ነብሳቸውን ይማርና ጠ/ሚኒስትር መለስ አንዳንዴ ያደርጉት እንደነበር ከመጨረሻው ጥያቄ ልጀምር እንደሚሉት፣ ከመጨረሻው አጀንዳ ተነስቼ ወደ ትላንቱ እሄዳለሁ፡፡ ጉዳዩ እንዳይለዝዝ (News Worthiness or Currency implication እንዳያጣ) ብዬ ነው፡፡ ከዚያ ወደ አሶሳው እጓዛለሁ፡፡
ከካይሮ ጉዞ መልስ ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም ዶ/ር አሸብር ቤት የምሣ ግብዣ ለካይሮ ተጓዦቹ ሁሉ ተደረገ፡፡ ከሞላ - ጐደል ሁሉም ተጓዦች መጥተዋል፡፡ ቤተ - መንግሥት አከል ቤት ነው፡፡  ዶ/ር አሸብር - Formalን (መንግሥታዊ እንደማለት) ተልዕኮ Informal ለማድረግ ነው - እንደ እድር፣ እንደ ቤተሰብ ስብሰባ ለማድረግ ነው፤ ግብዣውን ያዘጋጀሁት ብለዋል፤ የተከበሩ አቶ አባዱላንና፣ በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር መሃመድ ኢድሪስን እንዲሁም የተከበሩ ልዑካኑን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ፡፡  
በዚሁ ምሣ ዝግጅት ወቅት አባዱላ - “ደጋግመን እንደተናገርነው የዚህ ልዑክ ምርጫ (Composition) ባጋጣሚ ይሁን፤ ወይም ሁሉም ህዝብ ቢመረጥ እንደዚያ  ይሆናል አላቅም፡፡ አብረን የተጓዝነው ቡድን ለራሴ በጣም አርክቶኛል”
መከላከያም፣ ፓርላማም … ሆነን ብንሄድ ሳንካ አይጠፋውም፤ አንዱ አልጋ ላይ ሲቀር፣  ጫማዬን ልሠር፣ አንዱ ሻንጣዬን ሲል አይሳካም ነበር፡፡
68 ሰው ሆነን ስንጓዝ ግን አንድም ቀን ምንም ነገር አላጋጠመንም፡፡
ሌላው ደሞ ይሄ ሁሉ ሰው ምንም ዓይነት ያሳብ ልዩነት ሳይፈጠር ዕውነትም የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት አገር ወዳድ ነው? የሚለውን አይቼበታለሁ! በአግባቡ ለግብፅ መልዕክቱን አስተላልፎ፣ በአግባቡ ተመልሶ፣ በአግባቡ ደግሞ ለኢትዮጵያ መንግሥት ፓርላማ ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡  
በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር መሀመድ ኢድሪስንም We consider you as our member we’ll develop our relation for the future – Thank you very much. (እንደኛው አካል ነው የምናያችሁ፡፡ ወደፊትም ዝምድናችንን እናጠናክራለን)
***
ዶ/ር አሸብርም ለአምባሳደሩ ያላቸውን አድናቆት ሲገልፁ፤ You were travelling with us by bus everywhere – you were so close. (ከእኛ ጋር በሄድንበት ሁሉ በአውቶብስ ሲጓዙ ነበር - በጣም ቅርባችን ነበሩ) ብለዋል፡፡
አምባሳደር መሀመድ ኢድሪስ በበኩላቸው፤
“ግብፅን ለቃችሁ ስትመለሱ ብቸኝነት ተሰምቶኝ ነበር፡፡ እጅግ ልብ የሚነካ ተመክሮ ነበር፡፡ ዕውነተኛ ስሜታችንን በጥቂት ቀናት ውስጥ እንድንገልፅ ያገዘን ጉዞ ነበር፡፡ እዚያ ከእናንተ ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር ነበርኩ፡፡ ስትመለሱ አጣኋችሁ፡፡ ህዝቡ እዚያ በመሄዳችሁ ደስታውን ገልጧል፡፡ ይሄ ነገር መቀጠል አለበት፡፡ ይሄን የተቀጣጠለ ስሜት ዘላቂ ማድረግ አለብን፡፡ እንዲህ ያለው የጋራ ስሜት እያለ ለምን ወደ ሌላ አቅጣጫ መሄድ ይታሰባል? የጋራ እሳቤያችንን ማጠንከር፣ ልዩነት ካለን መፍታት ነው ያለብን” ብለዋል፡፡
አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ የዶ/ር አሸብርን ቤት ስፋት በማድነቅ፤ “ተወካዮች ም/ቤት አንዳንዴ እዚህ ቢሰበሰብ ጥሩ ነበር” በማለት ታዳሚውን አስፈግገዋል፡፡ ቀጥለውም፤  “ካይሮ ጉብኝታችን ጥሩ ነው … successful ነበር፤በካይሮ የኢትዮጵያ አምባሳደር መሐመድ ድሪርና በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር መሐመድ ኢድሪስ እንደ ነቢዩ መሐመድ የተከበሩ ሁለት መሀመዶች ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡” ብለው በተጨማሪ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ የታዳሚውን የጭብጨባ አፀፋም አግኝተዋል! ምሉዕ በኩለሄ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ እንደ ዶ/ር አሸብር እኛም  እንደ አቅም እናደርጋለን፡፡ ይሄ ግሩፕ ባይለያይ ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ብናገር ስራዬ ማስታወቂያ ነውና አስከፍላችኋለሁ” በማለት አዋዝተው “የራሷ ፊደልና ታሪክ ያላት ታላቋ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!” በማለት ንግግራቸውን ጨርሰዋል፡፡
*        *       *
በተከታታይ ወ/ሮ እምወድሽና ተዋናይ ደበሽ ተመስገን፤ ዶ/ር አሸብርን ግብዣውን በማድረጋቸው አመስግነዋል፡፡ አርቲስት ደበሽ፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንን በመጥቀስ “በድላችሁ ላይ አትተኙ” የሚለውን አባባል አስምሮበታል፡፡
ዶ/ር አረዳ በበኩላቸው፤ አጠራሩን ስለማልችልበት “በጠቅላላው የተከበራችሁ እላለሁ” ብለው ነው ታዳሚውን ሰላም ያሉት፡፡
የፖለቲካው ዓለም ለየት ያለ መሆኑን ተምሬያለሁ
Celebraition ማድረግ ሁሉም ይወዳል፡፡ የምፈራው አንኳር የሆኑ ጭብጦችን እንዳንረሳ ነው፡፡ ላይ ላዩን ሄደን እንዳንቀር - ግብፆች ለኛ መጨነቃቸውን እናስብ - ማረጋገጫ ስጡን ብለዋል፤ ትልቅ ሆምወርክ (የቤት - ሥራ) አለን፤ ያቺን component ጠንከር አድርጎ ሲነገር በጋዜጣም ሆነ በሬዲዮ አልሰማሁም
የፕሬዚዳንት ቢሮ ውስጥ የተካሄደው ስብሰባ ያለ ካሜራ መሆኑ እንደ ልብ ለመናገር ጥሩ ነበር፡፡ ሀቅ ለመናገር፣ ላለመጨነቅ፣ ይመቻል፡፡
ስለኛ ስብስብ እንዳለ ይቀጥል በሚለው አልስማማም፡፡ እንደገና ታይቶ መሻሻልና መቀጠል አለበት - አርብ ማታ ተጠርቶ እሁድ ቅዳሜ ተዘጋጅቶ፣ ሰኞ ሄዶ የዲፕሎማሲ ስብሰባ ይቀጥል ዓይነት እንዳይሆን ይታሰብበት” ያሉ ሲሆን፤ more celebration ሳይሆን more target oriented ይሁን፡፡ (ብዙ ድግስ ሳይሆን ብዙ ዓላማ - ተኮር) ብለዋል፡፡
የፕሮግራሙ መሪ ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ ግን - ካሜራዬን መሳሪያዬን ቤተመንግስት ደጃፍ ጥዬ በመግባቴ ዶ/ር አረጋ ባሉት አልስማማም፡፡ ከሚመለከታቸው ጋር ጦርነት ገጥሜበታለሁ -”  ብሏል፡፡ ሳምሶን በመቀጠል፤ “ወደኛ አገር የመጡት ልዑካን ታሪካቸውን የሚያሳዩ ማቴሪያሎች ይዘው ነው የመጡት፤ እኛ ባዶ እጃችንን ነው የሄድነው፤ አንዳንዶቹን ግብፃውያን ስጠይቃቸው፤ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አያውቁም፤ ያ በጣም አናዶኛል፡፡” ሲል ቅሬታውን ገልጧል፡፡  
*        *      *
ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን
“ይሄ ጉዞ ጅምር በመሆኑ appreciate መደረግ አለበት፡፡ ዶ/ር አረጋ ያነሱትን እጋራለሁ፡፡ የትም ቦታ ስለኢትዮ-ግብፅ በየደረጃው ማስረዳት አለብን - ስብሰባ ላይ ብቻ መሆን የለበትም
ልዑካኑ ለሴቶች ያደረጉትን እንክብካቤ አድንቀው Self Respect ያለው ሰው ሌላውን ማክበር ይችላል፤
ለሴቶችና ለአባቶች ክብር በተገቢው ሰዓት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
Simplicity ነገርን አለማካበድ ያስፈልጋል፡፡ ሚኒስትርም ሆኑ፣ አፈጉባኤም ሆኑ ፓርላማም ሆኑ ሰዎች ናቸው፤ የእኛ አገልጋዮች ናቸው”
ከሃይማኖት አባቶች አንዱም የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል፡፡ እሳቸውም -
1ኛ/ በሚገባ ግዙፍ የሆኑ ውጤቶችን አይተናል
2ኛ/ ፕሬዚዳንቱ ከእኛ ጋር አንድ መሆናቸውን ያሳዩበት ነው ያሉ ሲሆን፤
ለውጥ ለማምጣት ለወለደችን ምድር ታማኞች መሆን አለብን፡፡ ለራሳችንም ታማኞች ልንሆን ይገባል - እነዚህን ስናደርግ ራዕያችን ዕቅዳችን ስራ ላይ ይውላል፡፡ ሊያድግ ይችላል፤ የቀደሙት አንድ ተናጋሪ ዘመን መጣልን ብለዋል፡፡ ዘመን ሰውን አይለውጠውም፤ ሰው ነው ዘመንን የሚፈጥር፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልቦና ይሰጠዋል” ብለዋል!
ከሰሜን ሸዋ መንዝ ማህል ሜዳ - ከጉዋሣ ቀዝቃዛ ተራራ (3700 ሜትር) ብርድና ጉም ወርጄ አዲሳባ ስመለስ አንዲት ግጥም ፅፌ ነበር፡፡ “ደሞ መጣሁ አዲሳባ” የምትል፡፡
ደሞ መጣሁ አዲሳባ
ደሞ መጣሁ አዲሳባ
አስብቶ አራጅ ሳቅ ላረባ!
ከትሁት ጣራ ወርጄ፣ ከሰማይ ጠረፉ ጓሣ
ከዚያ ከሰላም ጫፍ ጠገግ፣ ከዚያ እርጥበት የጉም ዕንባ
ለአዲስ ርኩቻ ቆባ
በዕውቀት ስም የወሬ አላባ
በዕውነት ስም ሃሳዊ ካባ
አስብቶ - አራጅ ሳቅ ላረባ
ደሞ መጣሁ አዲሳባ!
    ተፈጥሮ የለ ቅብ ብቻ
ጧት ማታ ሩጫ ርኩቻ
የአርቲፊሻል መቀነቻ
ደሞ ላዲስ ጣር ዘመቻ
ለከተማ ከበር - ቻቻ
አስብቶ - አራጅ ሳቅ ላረባ
ደሞ መጣሁ አዲሳባ!!
የአዲሳባ ወጣ ገባ ህይወት የታክሲ፣ የመኪና፣ የሰው ግፊያ፤ ከጓሣ ሲመለሱ ያፍናል፡፡ ለዚያ ነው ግጥሟ የመጣችልኝ፡፡
በወከባዋ አዲሳባ ውስጥ ገና ከመግባቴ ብዙም ሳልቆይ አሶሳ ተጋበዝኩኝ፡፡ ስለ ዐባይ ከፃፍኳቸው ግጥሞች አንዱን ላነብ ነው፡፡ ለዚህ ጉዞ የያዝኩት ግጥም ግን አዲስ ነበር፡፡ “እዚህ ደማም! እዚያ ተማም!” የሚል ነው፡፡
በትምርተ - ጥቅስ ውስጥ ያስቀመጥኩት፤ ፀጋዬ ገብረመድህን ስለ ዐባይ የፃፈው የእሳት ወይ አበባ ግጥሙ ውስጥ ያገኘኋት ውብ መስመር በመሆኗ ነው፡፡ ከሌላ ገጣሚ የተወሰደን ቃል በትምህርተ - ጥቅስ ውስጥ ማስቀመጥ ቢያንስ ጨዋነት ነው ብዬ ነው፡፡
“ሰላም ልበል ዐቢይ ዐባይ፣ ሰላም ልበልህ ሰላም
“እዚህ ደማም! እዚያ ተማም!”
ደራሲው በሥነ - ቃሉ
እዚህ ደማም እዚያ ተማም፣ ብሎሃልና በውሉ
ገዢ - መሬት አለ እንዲሉ
ገዢ -ውሃችን ነህ ማለት፣ የኔም ቃል ነው እንደ ባህሉ፡፡
እንደኔ ፊደል አትፈድል
እንደኔ ቃል አታበቅል
መፍሰስ ብቻ ነው ያንተ ዕድል
አገር ማራስ ነው ያንተ ድል!...
…የውሃ ቡጥ የወንዝ ዕንቡጥ
በየልቡ እንዲቀመጥ
ከእንግዲህ መስኖህ እኛ ነን፣ ያንተ አቅም ነው  የእኛ ቀን ቁርጥ!
መንገዳችን እንዳይጠምም፣ እንዳይሆንብን ያፋፍ ድጥ
አብረኸን ሁን ዐቢይ ዐባይ፣ ብርሃን ዐይንህን ግለጥ!
…ዐባይ ዛሬስ፤ ዐቢይ ዐባይ
ይኸው ፈሰስክ እትብትህ ላይ!
እያለ የሚወርድ ግጥም ነው ግጥሜ - ልክ እንደ ዐባይ! ግድቡ ላይ ለሚካሄደው የኪነ ጥበብ ምሽት ላነብብ ያሰብኩት ግጥም ነበር፡፡ ግድቡ ጋ ምን ተፈፀመ?
(ይቀጥላል)

Read 2571 times