Saturday, 10 January 2015 10:09

ከልጅነት ፍቅር አንዲት ጠብታ

Written by 
Rate this item
(20 votes)

(በእውቀቱ ስዩም)

በሰላላው መንገድ
የትየለሌ እግር፣ እንደ ሊጥ ባቦካው
ጸአዳ ጣትሽን ፣ጉድፍ እንዳይነካው
ማጡን እየዘለልሽ
ዳጥ ዳጡን እያለፍሽ
ጤዛ የወረረው ዛፍ እየተደገፍሽ
ትንሽ ስትመጭ
ብዙ ስታዘግሚ
ሁለቴ ተራምደሽ፣ አስሬ ስትቆሚ...
ለተደናገረው ፣መንገድ ስትጠቁሚ
የተላከ ሕጻን ፣አስቁመሽ ስትስሚ…

እኔ ስናፍቅሽ
እኔ ስጠብቅሽ
እንደ ጉድ ተውቤ
ላማልልሽ ጥሬ
በጆንትራ ዘይቤ
ጠጉሬን አበጥሬ
ጅማት እያጠበቅሁ፣ጅማት እያላላሁ
የገዛ ከንፈሬን ፣ቀርጥፌ እየበላሁ፡፡
ስጠብቅሽ በጣም
ምስልሽ ነው እንጂ አካልሽ አልመጣም፡፡

ባይኖቼ ስፈልግ
መስኮት እከፍትና
ሌላ ነው የሚያልፈው ፣በሰፊው ጎዳና
ያው ገጣባ አህያ፣ያቻት ድኩም በቅሎ
በግ እየጎተተ፣አለፈ ቆለኛ
ቅርጫት ያጎበጣት ፣ሚስቱን አስከትሎ
ያውና ድሀ አደግ ፣መንገድ ዳር የተኛ
የተጎነጎነ፣የሣር አምባር መስሎ፡፡
ባይኖቼ ሳማትር ፣መስኮት እከፍትና
ሌላ ነው የሚያልፈው፣ በሰፊው ጎዳና፡፡

ሁሉም ተለውጦ
ያ ገጣባ አህያ፣ ጸጉር አቆጥቁጦ
ያች ድኩም በቅሎ ፣ሰጋር ፈረስ ቀድማ
ቆለኛው ሰውየ፣ ሙክት በጉን ሽጦ
ለሚስቱ ነጭ ሻሽ ፣ለሱ ሸራ ጫማ
በትርፉ ሸምቶ
ሁሉም ከሄደበት ፣ቀንቶት ተመልሶ
ሁሉም ከድቀቱ፣ በወግ ተፈውሶ
እኔ ብቻ ቀረሁ፡፡
መንገድሽ ረዝሞ፣ ባሳብ እያሳጠርሁ፡፡
አንቺን እየናፈቅሁ
አንቺን እየጠበቅሁ
ጅማት እያላላሁ፣ ጅማት እያጠበቅሁ፡፡

Read 5833 times