Saturday, 10 January 2015 09:55

ውዝግብ ከጦፈ፣ ምርጫ ደርሷል ማለት ነው!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)

•    ዓለም ከኛ ምርጫ ብዙ የሚማረው አለ እየተባለ ነው
•    የፖለቲካ ቋንቋ ለፀሎት አይመችም እኮ! (ለሃይማኖት አባቶች)
•    ምርጫ ቦርድ በ“ሆደ ሰፊነት” እየተንቀሳቀስኩ ነው አለ  

    እስቲ በአገራችን ምርጫ መቃረቡን የሚጠቁም ምልክት ከሚከተሉት ምርጫዎች ውስጥ ለመምረጥ ሞክሩ:-
ሀ) የሰከነ ክርክር ለ) ማራኪ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሐ) የጦፈ ውዝግብ መ) ሆደ ሰፊነት
 (በነገራችን ላይ በዘንድሮ የምርጫ ሂደት “ሆደ ሰፊነት” የሚለውን ቃል በብቸኝነት በመጠቀም ምርጫ ቦርድ ሪከርድ ሰብሯል!) እናስ…መልሱን ምን አላችሁት? እርግጠኛ ነኝ አትስቱትም፡፡ ለነገሩ --- “ፍሬሽ ካድሬ” (የድል አጥቢያ አርበኛ ለማለት ነው!) ካልሆነ በቀር “ሀ”ን፣ “ለ”ን እና “መ”ን ማንም ሊመርጥ አይችልም፡፡ በተለይ ደግሞ እንደኔና እንደናንተ ተራ ተርታ የሆነ ዜጋ መልሱ “ሐ” መሆኑ ጨርሶ አይጠፋውም፡፡ (እየኖርነው ነዋ!)
ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድም ደጋግመው “ምርጫውን ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ…” የሚሉት  ወደው እኮ አይደለም፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር እሳት የሆነ ውዝግብ እንደሚፈጠር ስለሚያውቁት ነው፡፡ በአጭሩ “የጦፈ ውዝግብ የምርጫ ሂደቱ አካል” እንደሆነ ሁላችንም እናውቀዋለን - እኛም (ተገዢዎቹን ማለቴ ነው!)፣ ገዢው ፓርቲም፣ ተቃዋሚዎችም፡፡ በእርግጥ የውዝግቡ መንስኤ ማነው የሚለውን ለመመለስ “ሆደ ሰፊ” የሆነ ጥናት ይጠይቃል፡፡ ለምን መሰላችሁ? አንዱ ሌላው ላይ ጣቱን ስለሚሰነዝር እኮ ነው! ሁላችንንም የሚያስማማን አንድ ጉዳይ ግን አለ፡፡ የጦፈ ውዝግብ ከተሰማ ምርጫ መድረሱን እናውቃለን፡፡ (ወይ አለመታደል!)
ይሄ ሳያንስ ደግሞ ሰሞኑን አንድ ነገር በይፋ ሲነገር ሰምቼ ድንግጥ አልኩ፡፡ እንደ እኔ መደንገጥ ካማራችሁ ልነግራችሁ እችላለሁ፡፡ በአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ “ዓለም ከአገራችን ምርጫ ብዙ የሚማረው አለ” ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እኔ የምለው--- ዓለም በውዝግብ የታጀበ ምርጫ ይፈልጋል እንዴ? (ይሄ እኮ መደበቅ ነው ያለበት!) ባይሆን ከውዝግብ ውጭ ሌላ ዓለም ከምርጫው የሚማረው ነገር ካለ በግልፅ ይንገረን፡፡ ያለዚያ ግን የአገር ገጽ ግንባታውን አፈር ድሜ ስለሚያስበላው ጭጭ ብንል ነው የሚያዋጣን (ዝም ማለት ማንን ገደለ!)  
አሁን ለማንኛውም ያዘጋጀኋቸውን ሁለት የሚያሸልሙ ጥያቄዎችን ላቅርብላችሁ፡፡ (ሽልማቱን ምርጫ ቦርድ ስፖንሰር እንደሚያደርገው ይጠበቃል!) በነገራችን ላይ ጥያቄዎቹ ከአዲስ አድማስ ላይ የተወሰዱ የዜና ዘገባዎች ሲሆኑ ሁሉም  በምርጫ ወቅት የተዘገቡ ናቸው፡፡ ከእናንተ የሚጠበቀው ዘገባዎቹ መቼ እንደወጡ መመለስ ወይም መገመት ነው፡፡ ጥያቄ (ዘገባ) 1
“የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና ካድሬዎቹ የአገሪቱን ህግ በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ ምርጫውን ነፃና ሚዛናዊ እንዳይሆን አድርገዋል ሲሉ ነቀፉ፡፡ የምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ፤ ቦርዱ ከማንም ሳይወግን ገለልተኛ ሆኖ ነፃና ሚዛናዊ ምርጫን እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል”
ጥያቄ (ዘገባ) 2
“በምርጫው ወቅት በድምፅ አሰባሰብና ቆጠራ ላይ የማጭበርበር ድርጊቶች መፈፀም አለመፈፀሙን ለማረጋገጥ የመራጮች መዝገብ ፎቶ ኮፒ እንዲሰጠን ጠይቀን ተከልክለናል ሲሉ አንድ የኢዴፓ ተወካይ ገለፁ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ድምፅ የሚሰጡት ሰዎች በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡ መሆናቸውን ማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው ያሉት የኢዴፓ ተወካይ አቶ ሙሼ ሰሙ፤ ስለ ችግሩ መግለጫ አውጥተን ምላሽ አላገኘንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት አንድ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ፤ በጠቅላላ በሀገሪቱ 25ሺህ የመራጮች ሰነድ መኖሩን ጠቁመው የመራጮች መዝገብን ፎቶ ኮፒ ማድረግ የማይቻል ቢሆንም ተቃዋሚዎች በዚህ ስጋት ሊፈጠርባቸው አይገባም ብለዋል፡፡”
ወዳጆቼ፤ ምናልባት ዜናዎቹ የወጡበትን ትክክለኛ ጊዜ (ቀንና ዓመተ ምህረት) መገመት አስቸጋሪ ሊሆንባችሁ ስለሚችል ዘገባዎቹ የወጡት በስንተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ እንደሆነ ከመለሳችሁም ከበቂ በላይ ነው፡፡ (ያሸልማል ማለቴ ነው!) በነገራችን ላይ በየምርጫው ተመሳሳይ ውዝግብ ስለሚኖር ዘገባዎቹም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ (ብትሳሳቱም አይፈረድባችሁም ለማለት ነው!) እስቲ ደግሞ አንድ ቦነስ ጥያቄ ልጨምርላችሁ፡- (የጥያቄ ቦነስ? እንዳትሉ!)
ጥያቄ (ዘገባ) 3
“በግንቦቱ ምርጫ የሚወዳደሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ከህግና ደንብ ውጭ፣ የገዢው ፓርቲ አባላት የተመረጡበት ነው በማለት የተቃወሙ ሲሆን ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ የህዝብ ታዛቢዎችን ህብረተሰቡ ነው የመረጣቸው ብሏል”
እንግዲህ እንዳነበባችሁት… ሦስቱም በምርጫ ውዝግብ ላይ ያነጣጠሩ ዜናዎች ሲሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የተዘገቡ ቢሆኑም ተመሳሳይ ናቸው (የአንድ እናት ልጆች ይመስላሉ!) ለዚህ እኮ ነው “ውዝግብ የምርጫው ሂደት አካል ነው”  ያልኩት፡፡ ይሄ አባባል ግን ለሁሉም አገር ምርጫ የሚሰራ እንዳልሆነ እወቁልኝ፡፡ በአብዛኛው ለአፍሪካ አገራት ነው የሚሰራው፡፡ ለዛሬ ግን ትኩረታችን በራሳችን ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ (“የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች” እንድንባል አንፈልግማ!)   
እኔ የምለው ግን… መቼ ነው የምርጫ ውዝግብና ንትርክ ጠፍቶ ምርጫውን በሰለጠነና በሰከነ መንገድ የምናካሂደው? (በነቢብም በገቢርም ማለቴ ነው!) መቼ ነው የምርጫ ቦርድ ገለልተኛነት በተቃዋሚዎችም ጭምር አመኔታ የሚያገኘው? መቼ ነው የህዝብ ታዛቢዎች የገዢው ፓርቲ ካድሬና አባላት ናቸው የሚል ውንጀላ ሳንሰማ ምርጫው የሚያልፈው? (ውንጀላው ሃሰት መሆኑን ኢህአዴግም ቦርዱም ገልፀዋል!) መቼስ ነው በሚዲያ ድልድል ላይ ቅሬታ የማንሰማው? (ኢህአዴግን አይመለከትም!)
በነገራችን ላይ በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተቃዋሚዎች የሚዲያ ድልድል ላይ የሚያነሱትን ቅሬታ በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ ተቃዋሚዎች ከተመደበላቸው የአየር ሰዓት ውስጥ 40 በመቶውን ብቻ እንደሚጠቀሙበት ጠቁመው ችግሩ ያለው ከራሳቸው ስለሆነ የሚዲያ አጠቃቀማቸውን እንዲያሻሽሉ ምክር ለግሰዋል፡፡ ሰሞኑን በEBC ቃለምልልስ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና በበኩላቸው፤ የተቃዋሚዎች ቅሬታ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው ኢህአዴግም ተቃዋሚዎችም የተመደበላቸውን የሚዲያ የአየር ሰዓት በአግባቡ አይጠቀሙም ሲሉ ተችተዋል፡፡ (ግልፅነት ለዘላለም ይኑር!)
በሚዲያ አጠቃቀም ላይ የቀረበው ትችት በተለይ አሳሳቢ የሚሆነው ግን ለተቃዋሚዎች ነው፡፡ ለምን አትሉም? ገዢው ፓርቲማ ድሮም የሚዲያ ችግር የለበትም፡፡ (ብሔራዊ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያ በእጁ ነዋ!)
እኔ የምላችሁ ግን… መኢአድና አንድነት ሄደው ሄደው ምርጫ ሲደርስ ምን “ቡዳ” በላቸው?! ምንም ቢሆን እኮ በምርጫው መሳተፋቸውን እንፈልገዋለን (ቢያንስ ለምርጫው ሂደት ማማር ሲባል!) እንግዲህ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ፤ ፓርቲዎቹ በውስጣቸው የተፈጠረውን ክፍፍል በህገደንባቸው መሰረት በመፍታት ወደ ምርጫው እንቅስቃሴ እንዲገቡ የመጨረሻ ዕድል መስጠቱን አስታውቋል፡፡ ቀነ ገደቡ ደግሞ ከነገ ወዲያ ያበቃል!
 እውነት የተባለው ክፍፍል በፓርቲዎቹ ውስጥ ተከስቶ ከሆነ እኮ በጣም ነው የሚያሳዝነው፡፡ ሁለት ዋና ተቃዋሚዎች በውስጣዊ ክፍፍል የተነሳ ከምርጫው ሲሰናከሉ ማየት እንኳን ለወዳጅ ለኒዮሊበራል አቀንቃኞችም ያሳዝናል፡፡ የ90 ሚ. ህዝብ ችግር ይፈታሉ ተብለው የሚጠበቁ ፓርቲዎች፤ውስጣዊ ችግራቸውን ለመፍታት “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ካሉማ “ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ” ማለት እኮ ነው፡፡ ከተቃዋሚዎች ጎራ የሚሰማው ግን ሌላ ነው፡፡ “ቦርዱ የሌለ ክፍፍል ፈጥሮ ከምርጫው በሰበብ ተቀናሽ ሊያደርገን ነው” እያሉ ነው፡፡ ለኛ  ሁለቱም ቢሆን ያሳፍረናል እንጂ አያኮራንም፡፡
እንግዲህ ወዳጆቼ፡- ጋዜጣው ለህትመት እስከገባበት የመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ሽልማቱን ስፖንሰር የሚያደርግ ባለመገኘቱ (ምርጫ ቦርድን ጨምሮ!) ጥያቄዎቹን እኔው ራሴ ልመልሳቸው ተገድጄአለሁ፡፡ ለነገሩ መልሱ ራሱ የሽልማት ያህል ስለሆነ አያስቆጭም፡፡
እናላችሁ… በምርጫ ውዝግብ ላይ ያተኮሩት ሁለቱ የመጀመሪያ ዘገባዎች የወጡት የዛሬ 15 ዓመት ነው - ግንቦት 5 ቀን 1992 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ እትም ላይ (በ2ኛው አገራዊ ምርጫ ወቅት ማለት ነው!) ግን እኮ በዘንድሮ ምርጫ የወጡ ዘገባዎች ናቸው ቢባልም ማንም ሃሰት ነው ብሎ አይከራከርም፡፡ በመልክም በቅርፅም በይዘትም አንድ ናቸዋ! እንደ ቦነስ የቀረበው ሦስተኛው ጥያቄ ደግሞ ዘንድሮ ታህሳስ 18 ቀን 2007 ዓ.ም የወጣ የምርጫ ውዝግብ ዜና ነው፡፡
በነገራችን ላይ የሁለቱን ፓርቲዎች ጉዳይ በተመለከተ ምርጫ ቦርድ ባሳየው “ሆደ ሰፊነት” ተደምሜአለሁ፡፡ ተቃዋሚዎች ግን የሆድም የምህዳርም ጥበት እንጂ ሰፊነት አላየንም ባይ ናቸው፡፡ የሆኖ ሆኖ … አሁን ለምርጫ ቦርድና ለገዢው ፓርቲ የማቀርበው አንድ የህዝብ ጥያቄ አለኝ፡፡ (አደራ -- ማን የህዝብ ተወካይ አደረገህ እንዳትሉኝ!) በየምርጫው ከባባድ ንትርክና ውዝግብ እየተነሳ የአገራችን ምርጫ በየጊዜው መሻሻል አሳይቷል የሚባለው በምን ስሌት ነው? እንግዲህ ምርጫ ሲባል ተቃዋሚዎችንም ይጨምራል ብዬ ነው፡፡ በውዝግቦቹ ላይ ተወያይቶ መፍትሔ መስጠት ያቃተው ለምንድን ነው? (“የሮኬት ሳይንስ” አስመሰልነው እኮ!) የሰለጠኑ አገራት የሚያካሂዱት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እኛ ጋ ለምን አሻፈረኝ አለ? (ምርጫ ሂደት መሆኑ አልጠፋኝም!) ብቻ -- ብዙ መልስ የሚሻ ጥያቄ ይጠብቀናል --
ይሄ ሁሉ ችግር እንዳለ ሆኖ፣ ምርጫ ቦርድ ለእነመኢአድ ችግራቸውን እንዲፈቱ ሁለተኛ ዕድል የሰጠበት ምክንያት አስደምሞኛል፤ “በሆደ ሰፊነት --- የዲሞክራሲ ዕድገቱን ለማጐልበትና ከጀርባቸው ብዙ ህዝብ አለ በሚል ነው” ብሏል፡፡ ተቃዋሚዎች ባይቀበሉትም  እኔ ግን ሰበቡን  ወድጄለታለሁ፡፡ (ለመውደድ እኮ ስሜት በቂ ነው!)
ምናልባት… ኢህአዴግና ቦርዱ ለምርጫ ውዝግቡ ተቃዋሚዎችን ተጠያቂ አድርገው “ከደሙ ንፁህ ነን” ሊሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ (መብታቸው ነው!) እኛም ይሁንላቸው ብለን እንቀበላቸው፡፡ ለውዝግቡ መፍትሔ ማምጣት ባለመቻላቸው ግን ሁሉም ተጠያቂዎች ናቸው - ቦርዱም፣ ኢህአዴግም፣ ተቃዋሚዎችም፡፡ የምንናፍቀው የሰለጠኑ አገራት የምርጫ ሂደት (ኒዮሊበራሎች ቢሆኑም ማለት ነው!) የሚመጣው በሶስቱም ወገኖች ፍላጐትና ቁርጠኝነት ብቻ ነው፡፡ (ኢህአዴግ ቦርዱ ላይ መለስተኛ ቅሬታ እንኳ ሲያቀርብ መስማት አልናፈቃችሁም?!)
እናላችሁ…መጀመሪያ ላይ ባየናቸው የዜና ዘገባዎች መሰረት፤ ዘንድሮ ሊካሄድ በታሰበውና በ92 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ መካከል ብዙ ልዩነት የለም - ሁለቱም ውዝግብ መገለጫቸው ነው (የጊዜ ሂደት ያልፈታው የምርጫ ችግር በሉት!) ይሄንንም ፈርዶብን ነው ብለን ትተነው ነበር፡፡ አንዳንድ የማይመስሉ አስተያየቶች እየሰማን ግን ተቸገርን፡፡ ምን መሰላችሁ? “ዓለም ከኛ ምርጫ የሚማረው ብዙ ነገር አለ” እየተባለ እኮ ነው፡፡ (ዓለም ከኛ የማይማረው ምን ይሆን?) የሚገርመው ደግሞ የምርጫ ህጉ የተቀረፀው የበርካታ የዓለም አገራት የምርጫ ህግና ተሞክሮ ተገምግሞና ተቀምሮ መሆኑን የቦርዱ ሃላፊዎች ደጋግመው ነግረውናል፡፡ (ዘነጉት እንዴ?) እናላችሁ… ከዓለም የኮረጅነውን የምርጫ ተመክሮ እንዴት ነው መልሰን ለዓለም የምናስኮርጀው? (ያውም ውዝግብ ጨምረንበት!)
ለማንኛውም ግን  ለ5ኛው አገራዊ ምርጫ ተዋናዮች በሙሉ ልብና ሆደሰፊነትን ይስጥልን፡፡ ምርጫው የእውነትም ሰላማዊ፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ያዋጣ፡፡ የሃይማኖት አባቶችም ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትተው በፀሎት ይትጉልን፡፡ (የፖለቲካ ቋንቋ ለጸሎት አይመችም እኮ!)

Read 3178 times